Teddy Afro
Teddy Afro

በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የመንግስት የአፈና ሰለባ የሆነው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ቴዲ አፍሮ ተዘዋወሮ የመስራትም ይሁን ከአድናቂዎቹ ጋር የመገናኘት ዕድል መነፈጉ ይታወቃል። ከሰሞኑም ለአዲስ ዓመት አቅዶት የነበረው ኮንሰርት ተሰርዟል። በሁኔታው ያዘኑ አድናቂዎቹ ግን ሌላ መላ ዘይደው በዓሉን አሳልፈዋል። የመዝገቡ ሀይሉን ዘገባ አድምጡ

 

ቴዎድሮስ ካሳሁን ወይም ቴዲ አፍሮ ለዘመን መለወጫ አዘጋጅቶት የነበረው የሙዚቃ ኮንሰርት መታጎሉ እልህ ያስገባቸው የአርቲስቱ አድናቂዎች በፌስቡክ የሙዚቃ ድግስ በማዘጋጀት ለቴዲ አፍሮ ያላቸውን አድናቆትና ፍቅር በመግለጽ ምሽቱን ማሳለፋቸው የዚህ ሳምንት መነጋገርያ ኾኖ ነበር።
ከኢትዮጵያ መንግስት ተደጋጋሚ ውዝግብ የሚፈጠርበት ዝነኛው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ የዘመን መለወጫ ኮንሰርቱ መሰረዙን በማኅበራዊ ሚዲያ ባሳወቀበተ ጊዜ ለብዙ አድናቂዎቹ ጉዳዩ የተለመደው የኢትዮጵያ መንግስት በቴዲ አፍሮ ላይ የፈጠረው ሌላ ችግር መኾኑ አላጠራጠረም። ይህንንም ተከትሎ ብዙዎች በፌስቡክና በትዊተር ጽሑፋቸው በክስተቱ ምክንያት የተሰማቸውን ኀዘን ሲገልጹም ተስተውለዋል። ከመንግስት ወገን ለዝግጅቱ ፈቃድ ላለመስጠት እንደምክንያት ቀርበዋል የሚባሉትም ምክንያቶች አሳማኝ አለመኾናቸውም መንግስት ኾነ ብሎ በኮንሰርቱ ላይ ያነጣጠረ መሰናክል መፍጠሩን የሚሸፍኑ አይደሉም።
ይህ ድርጊት ያሳዘናቸው ታዛቢዎችና የቴዲ አፍሮ አድናቂዎች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ስሜት በሚገልጹበት ጊዜ ጋዜጠኛው የትነበርክ ታደለ ይህንኑ ኮንሰርቱን በፌስቡክ የማስቀጠል ሐሳብ ለፌስቡክ ወዳጆቹ አቀረበ። በወዳጆቹ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘውን ይህን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግም ታዳሚዎችን ሲጠራ ቆይቶ የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ሊደረግ በታቀደበት የአዲሱ ዓመት ዋዜማ የቴዲ አፍሮን ሙዚቃ ሲያሰማ አመሸ። ቀድሞውንም የብሮድካስት ጋዜጠኝነት ምሩቅ የነበረው የትነበርክ ፕሮግራሙን በመደበኛ የሬዲዮ ስርጭት አቀራረብ ለማዘጋጀት አልተቸገረም። ቀላል የማይባል የቴዲ አፍሮ አድናቂም ዝግጅቱን ከመከታተሉም በላይ የፌስቡክ ፎቶአቸውን በቴዲ አፍሮ ፎቶ የቀየሩና ስለቴዲ አፍሮ ግጥሞች ለዚሁ በተዘጋጀው የፌስቡክ ገጽ ላይ በጽሑፍ የገለጹም ብዙዎች ነበሩ። ኅብር ሬዲዮም ይህንኑ ፕሮግራም በቀጥታ አስተላልፎት ነበር። ከኅብር ሬዲዮም በተጨማሪ ራሱ የትነበርክ ሚክስለር በሚባል የሞባይል አፕሊኬሽን አማካኝነት በቀጥታ ሲያስተላልፈው የነበረውን ፕሮግራም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተከታትለውታል።
ይህ ሙከራ ብርታት የሰጠው የትነበርክ ከበዓሉም በሁዋላ ስርጭቱን ቀጥሎ ሰንብትቱዋል። ቴዲ አፍሮን ከሚመለከቱ ፕሮግራሞች ባሻገርም ሌሎች የሬዲዮ ፕሮግራሞችን አስተላልፉዋል። የሬዲዮ ጋዜጠኝነቱን ስራ ለመቀጠል ያቅድ ለነበረው የትነበርክ ይህን ሚክስለር የተባለ ፕሮግራም ማግኘቱ ትልቅ ርዳታ አድርጎለታል።
የዚህ ፕሮግራም ስኬት በጊዜው ለቴዲ አፍሮ አድናቂዎች ከሰጠው ደስታ ባሻገርም መንግስት የቴዲ አፍሮን ራስን የመግለጽ ነጻነት ለመገደብ ያደረገውን ክልከላም በመቃወም የተደረገ አጋርነት ማሳያ አንድ ምሳሌ ተደርጎ ተቆጥሩዋል። በመንግስት ለተፈጸመ ድንገተኛ የመብት ጥሰት የተሰጠ አፋጣኝ ምላሽ መኾኑ ለብዙዎች ፕሮግራሙን ለተከታተሉ ሰዎች ግልጽ ነበረ። የፕሮግራሙን ዓላማ በመደገፍም 11 ሺህ ያህል ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የፌስቡክ ገጹን በመታደም እና ስሜታቸውን በጽሑፍ በማጋራት ተሳትፈውበታል። አጋጣሚውም በድረገጽ አክቲቪዝም ለመሳተፍ ለሚያስቡ ሰዎች ድምጻቸውን ሌያሰሙ የሚችሉበትን አንድ መንገድ በማስተዋወቅም አልፉዋል።
በዚህ የቴዲ አፍሮ የአዲስ ዓመት ዋዜማ የፌስቡክ ዝግጅት ላይ ጥቅም ላይ የዋለው Mixlr የተባለው የሞባይል አፕሊኬሽንም ይሁን እርሱን የመሰሉ ሌሎች ፕሮግራሞች የፌስቡክ ገጽ የመክፈት ያህል የቀለሉና ያለብዙ ቁሳቁስ በእጅ ስልክ በመሐቀም ብቻ ማንም ሰው በቀላሉ ሊገለገልባቸው የሚችል መኾኑ ብዙ ሰዎች ይህንን መንገድ ተከትለው በድምጽ ሊሳተፉበት የሚያስችል ነው። ምናልባትም አሁን ፌስቡክን እና ትዊተርን በመሰሉ ማኅበራዊ ድረገጾች በጽሑፍና በምስል እንደሚደረጉ የግለሰብ ጋዜጠኝነት (Citizen Journalism) መሰል አስተዋጽዖዎች አንድ ተጨማሪ መድረክ ሊኾን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቱዋል።
ገዳቢ የብሮድካስት ሕግ ባለበትና የመናገር ነጻነት በሌለባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ዘመናዊው ቴክኖሎጂ ከሚሰጣቸው እድሎች አንዱ ተደርጎም ሊቆጠር ይችላል።