Abadula Gemeda, Speaker of the House and OPDO CC member
Abadula Gemeda, Speaker of the House and OPDO CC member

(ዋዜማ ራዲዮ) የአዲስ አበባ የተቀናጀ የጋራ ልማት ዕቅድን በመቃወም ​​በኦሮሚያ ክልል ህዝባዊ አመፅ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እርስ በርስ የሚጣረሱ አቋሞችን ሲያንፀባርቁ ቆይተዋል፡፡ አመፁም ተባብሶ በመቀጠሉ 140 ያህል ንፁሃን ዜጎች በመንግስት ፀጥታ ኃይሎች እንደተገደሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እየገለፁ ነው፡፡ እስካሁን የታየው ሁኔታ የኦህዴድን ክልሉን የማስተዳደር ብቃት የሚፈትን ብቻ ሳይሆን ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት ሰላማዊ ጥያቄዎችን በኃይል መጨፍለቅን ስራዬ ብሎ እንደቀጠለበት አሳይቷል፡፡

ከድሮው በተለየ ህዝባዊ አመፁ የማያባራ መሆኑ ግን መንግስትን ውልውል ውስጥ ያስገባው ይመስላል፡፡ በተለይ የሟቾች ቁጥር በየዕለቱ እየናረ ሲሄድ ዓለም ዓቀፍ ውግዘቱም እየጨመረ መሄዱ ስጋተን ሳያባብስበት እንዳልቀረ በሰፊው ይታመናል፡፡ ለዚህም ይመስላል ሰሞኑን የክልሉ ገዥ ፓርቲ ኦህዴድ የተቀናጀ የጋራ ልማት ዕቅዱ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም መወሰኑን ያስታወቀው፡፡

[ቻላቸው ታደሰ የድምፅ ዘገባ አለው]

ከዚህ ቀደም ከነበሩት የመንግስት አቋሞች ይልቅ አዲሱ ውሳኔ የበለጠ ትኩረት ሳቢ እንዲሆን የሚያደርጉት ምክንያቶች አሉ፡፡ በአንድ በኩል ውሳኔው በተቀናጀው የጋራ ልማት ዕቅድ ዕጣ ፋንታ ላይ የተላለፈ የመጨረሻ ውሳኔ ተደርጎ መቅረቡ ብቻ ሳይሆን ከነባሩ የመንግስት አቋም አንፃር ሲታይ ቢያንስ በዚህ ጊዜ ይሆናል ተብሎ ያልተጠበቀ ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን ውሳኔው በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ዓይነት መሆኑ ብዙ አያጠያይቅም፡፡ በይዘቱ እርስ በርስ የሚጋጩ መልዕክቶችን ያካተተ በመሆኑ ለችግሩ ወጥ እና የማያወላዳ ምላሽ መስጠትም አልቻለም፡፡ ይልቁንስ መንግስት ዕቅዱን ጭራሹን በመሰረዝ እና ለጊዜው አዳፍኖ በማቆየት መካከል እየዋለለ መሆኑን አሳይቷል፡፡

የውሳኔው መንፈስ ላይ ላዩን ሲያዩት ህዝቡ ዕቅዱ ተሰርዟል ብሎ እንዲያምን የተፈለገ ቢመስልም፤ በቋንቋ አጠቃቀሙ ግን “ማስተር ፕላኑ ቆሟል” የሚለው አገላለፅ መካተቱ ከመግለጫው ጀርባ ብልጣብልጥነት እንጂ ፖለቲካዊ ቅንነት እንደሌለ ጠቋሚ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ውሳኔውን ያሳለፈውና መግለጫውን ያወጣው ፓርቲው ኦህዴድ መሆኑም እንዲሁ ትኩረት ሳቢ አድርጎታል፡፡ ኦሮሚያ ክልል ባላዘጋጀውና ባለቤት ባልሆነበት ዕቅድ ዕጣ ፋንታ ላይ የመጨረሻ ብያኔ ሰጭ ሆኖ ብቅ ማለቱ ከህግ አንፃር አስገራሚ እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ ልዩ ፅህፈት ቤት በማቋቋም ከጥንስሱ ጀምሮ የተቀናጀ የጋራ ልማት ዕቅዱን በባለቤትነት ይዞት የኖረው ራሱን በቻለ ህጋዊ ቻርተር የሚተዳደረው የአዲስ አበባ መስተዳድር ነው፡፡

በእርግጥ አዲስ አበባ የሀገሪቱ ዋና ከተማ በመሆኗ፣ አስተዳደራዊ ተጠሪነቷም ለፌደራሉ መንግስት በመሆኑና ዕቅዱም አጎራባች ክልልን የሚነካ መሆኑ ፌደራል መንግስቱ ዋነኛው የዕቅዱ ባለቤት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በህገመንግስቱ አዲስ አበባን ወይም ከተማዋ ከአጎራባች ክልል ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ህግ የማውጣት ወይም የመሻር ስልጣን የተሰጠው ለፌደራሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቻ እነደሆ ተደንግጓል፡፡ ለዚህም ነው የፌደራሉ መንግስት ባለስልጣናት ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩለት የነበረው፡፡ ስለዚህ የኦህዴድ ውሳኔ ህገመንግስታዊ ስለመሆኑ ጥያቄ ያስነሳል፡፡

በሌላ በኩል ዕቅዱ በከተማዋ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖችን የሚያካትት በመሆኑ ክልሉ በዕቅዱ አፈፃፀም ሂደት ባለድርሻ የመሆን መብቱ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ ድሮውንም በደንብ አልታሰበበትም ይሆናል እንጂ ከዕቅዱ ዝግጅት ጀምሮ ተሳታፊ ከመሆን የሚከለክለው ነገር እንዳልነበር የህግ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡

የሆነው ሆኖ ኦህዴድም ሆነ ራሱ የሚመራው መንግስት ድምፃቸውን አጥፍተው ኖረው በድንገት በዕቅዱ ላይ አዛዥ ናዛዥ ሆነው ብቅ ያሉት ህዝባዊ አመፅ ከተቀጣጠለ በኋላ ነበር፡፡

ውሳኔው ያዘለው ተቃርኖ በዚህ ብቻ ቢያበቃ ጥሩ ነበር፡፡ የተቀናጀ የጋራ ልማት ዕቅዱ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ መስተዳድር እና ከፌደራል መንግስቱ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚመለከት ሆኖ ሳለ በክልላዊ መንግስቱ ፋንታ ውሳኔውን ያሳለፈው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ መሆኑ ሌላኛው ፖለቲካዊና ህጋዊ ወለፈንድ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቆመው የኦሮሚያ ክልል የዕቅዱ ዋነኛ ባለቤት አለመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለቤት ነኝ ቢልም እንኳ በኦሮሚያ ክልል ህገመንግስት መሰረት እንዲህ ዓይነት ዓበይት ውሳኔዎችን ማሳለፍ የሚችለው የክልሉ ምክር ቤት (ጨፌ) ብቻ እንጂ ገዥው ፓርቲ ሊሆን አይችልም፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ ኦህዴድ ለምን ይህን አካሄድ መረጠ? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ሌሎች ምክንያቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ኦህዴድ ይህን አካሄድ የመረጠው የዕቅዱ መቆም ወይም መሰረዝ እንደ ፖለቲካዊ እንጂ እንደ ህጋዊ ውሳኔ እንዲታይ ስላልፈለገ ሊሆን እንደሚችል መናገር አይከብድም፡፡

ከጅምሩም ውሳኔው ከክልሉ ምክር ቤት እንዲመጣ ስላልተፈለገ ይሆናል እንጂ ቢታሰብበት ግን ሊሞከር ይቻል ነበር፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ ምክር ቤቱ ውሳኔውን ላይቀበል ይችላል ተብሎ ተሰግቶ ይሆን? ብሎ ማሰብ ግን እምብዛም ውሃ የሚቋጥር አይመስልም፡፡ ምንም እንኳ ክልሉን የሚመራ ድርጅት ቢሆንም ከመርህ አንፃር ግን የኦህዴድ ውሳኔ ፖለቲካዊ ነው፡፡ ስለዚህ ከህገመንግስታዊ መርህ አንፃር ሲታይ አመፁ ከረገበ በኋላ የክልሉ ምክር ቤት የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴን ፖለቲካዊ ውሳኔ በመቀልበስ ለዕቅዱ እንደገና ህይወት ለመዝራት ቢፈልግ የሚያግደው ምንም ነገር አይኖርም፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ከ1997ቱ ምርጫ በፊት ዋና መቀመጫውን ወደ ናዝሬት (ወይም አዳማ) ለማዛወር ከወሰነ በኋላ እንደገና በምርጫው ማግስት በፍጥነት ውሳኔውን በሌላ ውሳ ሽሮ ወደ አዲስ አበባ መመለሱ ፖለቲካዊና ህጋዊ ጥያቄዎች አስነስቶበት ነበር፡፡ ተመሳሳይ ስህተት ላለመድገም የሰሞኑ ውሳኔው በፓርቲው ብቻ ተገድቦ እንዲቆይ የተፈለገ ይመስላል፡፡

በአጭሩ አዲሱ ውሳኔ ኦህዴድ ህዝባዊ አመፁን ሽፋን በማድረግ የዕቅዱን ባለቤትነት ከአዲስ አበባ እንዲረከብ ፌደራል መንግስቱ ዕድል የሰጠው ይመስላል፡፡ ምንም እንኳ ለፖለቲካዊ ፍጆታ ተብሎ የተሰጠ ጊዚያው ዕድል ቢመስልም፡፡ ዋነኛው ባለቤት የአዲስ አበባ መስተዳድር ከህዝባዊ አመፁ መቀስቀስ ጀምሮ ምንም ኮሽታ አሰምቶ አያውቅም፡፡

ፌደራል መንግስቱም በጠቅላይ ሚንስትሩና በሌሎች ባለስልጣናት አማካኝነት ስለ ዕቅዱ አስፈላጊነት ቀን ተሌት ሲሰብክ እንዳልቆየ ሁሉ ከመጨረሻው ውሳኔ ግን ራሱን በማግለሉ ፖለቲካዊ ዳፋውን ሙሉ በሙሉ ኦህዴድ ብቻውን ተሸክሞታል፡፡ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ለህዝባዊ አመፅ እጅ የሰጠ መስሎ መታየት የፈለገ አይመስልም፡፡

እስካሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ በመመርኮዝ አዲሱ ውሳኔ ውዝግቡን በዚሁ ይቋጨው ይሆን? ለሚለው ጥያቄ የተወሰኑ የቢሆን መላ ምቶችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ መንግስት በአመፁ ሳቢያ ያሰራቸውን ፖለቲከኞችና ሌሎች በርካታ ግለሰቦች ከእስር ሊፈታ ይችላል የሚለው አንደኛው አሳማኝ የቢሆን መላ ምት ነው፡፡ ኦህዴድም በደንብ የሚቆጣጠራቸውን ህዝባዊ ስብሰባዎች በማዘጋጀት የማረጋጋት ስራ ሊሰራ ይችላል፡፡ ዓለም ዓቀፉ ግፊት ስላለ እና ህዝባዊ አመፁ ከውሳኔው በኋላም ባለመቆሙ የዚህ መላ ምት የመሳካት ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ መንግስት ይህን ማድረጉ ከተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ወቅታዊ አጀንዳዎችን ለመንጠቅ እንደሚረዳው ይታመናል፡፡

ሌላው በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚኖረው ሁለተኛው የቢሆን መላ ምት ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ህገመንግስታዊ ልዩ ጥቅም በአስቸኳይ በፌደራሉ መንግስቱ እንዲወጣ ተደርጎ በተቀናጀ የጋራ ዕቅዱ ላይ የተነሳውን ህዝባዊ ቁጣ ለማለዘብ መሞከር ነው፡፡ ኦህዴድም በመግለጫው “ልዩ ህገመንግስታዊ ጥቅሙን በህግ በማስወጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እሰጣለሁ” በማለት የዋናው ውሳኔ ማጀቢያ አድርጎ አቅርቦታል፡፡

ውሳኔው በህዝባዊ አመፁ ላይ ወደፊት ስለሚኖረው ተፅዕኖ ግን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ ህዝቡ ተጨማሪ ጥያቄዎችን እያነሳ መቀጠሉ አለመቀጠሉም ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ በድህረ-1997ት ከተከሰተው ህዝባዊ ተቃውሞ እና ከሀገሪቱ አጠቃላይ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ ግን አብዛኛው ህዝብ የተራዘመ አመፅን ለረዥም ጊዜ መሸከም የሚችልበት ትክሻ እምብዛም የማያወላዳ መሆኑን ነው፡፡

በጠቅላላው የተቀናጀ የጋራ ልማት ዕቅዱ ለህዝብ በበቂ ሁኔታ ግልፅ ስላልተደረገ የተፈጠረ ችግር ነው ሲል የነበረው መንግስት በድንገት ጭራሹን ትቸዋለሁ እያለ ነው፡፡ ከጅምሩም አሳታፊነት፣ ግልፅነትና ፍትሃዊነት ጉዳዮችን በደንብ እንዳልመለሰ የሚነገርለት ዕቅድ በውስጡ የያዛቸው መልካም ዕድሎችም አብረው እንዲቀበሩ ሆነዋል፡፡ በዚህ የተረበሸ ፖለቲካዊ መንፈስ ውስጥ ነው እንግዲህ ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ የተጠበቀለትን ልዩ ህገመንግስታዊ ጥቅም የሚመለከት ህግ ለማርቀቅ እየታሰበ ያለው፡፡ ህጉ ምን ዓይነት ዕድሎች ወይም ችግሮች ይዞ እንደሚመጣ በቅርቡ እንደሚታይ ይጠበቃል፡፡