ዋዜማ ራዲዮ- በኤርትራ አስመራ ከተማ ዛሬ በድንገት በተደረገ የተቃውሞ ስልፍ ተማሪዎችና ፖሊሶች ተጋጩ።
የትምህርት ቤታቸው የቦርድ ዳይሬክተር መታሰራቸውን የተቃወሙ ተማሪዎች በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቢሮ ዳጃፍ ስልፍ ለማድረግ ሲሞክሩ በታጣቂዎች የተኩስ እሩምታ ገጥሟቸዋል።

በግጭቱ ስለደረሰው ጉዳት የታወቀ ነገር የለም። በኤርትራ ይህን መስል ስልፍ ማድረግ ፈፅሞ የማይታስብ ሆኖ ቆይቷል። የቦርድ ስብሳቢው ሀጂ ሙሳ የታሰሩት በታሪኩ ከእስልምና እምነት ጋር የተያያዘው ትምህርት ቤት ሴት ተማሪዎች ሂጃብ እንዲያወልቁ በመንግስት የተሰጠውን ትዕዛዝ ባለመቀበላቸው ነበር። ትምህርት ቤቱ ከሀምሳ አመት በፊት የተቋቋመ ነው።ማክስኞ በተደረገው ስልፍ ላይ ከተማሪዎቹ በተጨማሪ የእስልምና ተከታይ የሆኑ የአስመራ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
ሀጂ ሙሳ የዘጠና አመት አዛውንት ሲሆኑ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያላቸው ናቸው።
በአስመራ የፀጥታ ሀይሎች ምሽቱን ቤት ለቤት በመዞር ቁጥራቸው ያልታወቀ ስዎችን ያሰሩ ሲሆን አንዳድንድ ወጣቶች ከተማዋን ጥለው ሸሽተዋል።
በአሰመራ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የፀጥታ ማሳሰቢያ ያወጣ ሲሆን በመሀል አስመራ በተለያዩ አቅጣጫዎች የተኩስ እሩምታ መሰማቱን ተናግሯል።  ከኤርትራ መንግስት የተሰጠ አስተያየት የለም።