ERCAዋዜማ ራዲዮ- በግብር ጉዳይ ላይ ‘ከደንበኞቻችሁ ጋር በማበር’ ሒሳብ ትሰውራላችሁ በሚል ተደጋጋሚ ማስፈራሪያ፣ ዛቻና ክስ እየቀረበባቸው እንደሆነ የተናገሩ የሒሳብ አዋቂ ባለሞያዎች መንግሥት ‘ታጋሽ በመሆኑ’ እንጂ በአንድ ጀንበር አፋፍሶ ሊያስራቸው እንደሚችል በመንግሥት ሹመኞች በተደጋጋሚ እየተነገራቸው እንደሆነ ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡
በአገሪቱ በሕጋዊ መንገድ የሒሳብ ሥራ ፈቃድ ወስደው የሚሠሩት እነዚህ ባለሞያዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዋና ኦዲተርና በፋይናንስ ደኅንነት መሥሪያ ቤቶች በየጊዜው ‹‹እንመካከር›› በሚል እየተጠሩ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል፡፡ “የማትተባበሩን ከሆነ ፍቃዳችሁን መሠረዝ ብቻ ሳይሆን እስር ቤት ነው የምንወረውራችሁ” ተብለናል በተረጋጋ ሁኔታ ሥራችንን እንዳንሰራ እየተደረግን ነው›› ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ባለሞያዎች እንደሚናገሩት አንዳንድ ጊዜ የመንግሥት ሰዎች ‹‹ከገቢዎች ነው›› በሚል በግል ስልካችን ጭምር እየደወሉ ‹‹የደንበኞቻችንን ሕየወት የተመለከቱና ምስጢራዊ የሒሳብ ሰነዶችን እንድናቀብል፣ የሒሳብ ስወራ ያካሄዳሉ ተብለው የሚጠረጠሩ ድርጅቶችን የሚመለከቱ ተያያዥ መረጃዎችን ቅጂ በድብቅ እንድናመጣ ጫና እያደረገብን ነው ይላሉ፡፡ ‹‹እኛ የደንበኞቻችንን የሒሳብ መግለጫ በምስጢር የመያዝ ግዴታ አለብን፡፡ በሚመለከተው አካል አግባብ ባለው መንገድ ስንጠየቅ ደግሞ ሄዶ የማስረዳት ኃላፊነት አለብን፡፡ ተቀባይነት ያላቸው የሂሳብ አያያዝ መርሆችንና የኦዲት ስታንደርዶችን እስከተከተልን ድረስ የድርጅት ምስጢር አውጡ ብሎ ማስፈራራት ግን ከመንግሥት አይጠበቅም›› ይላሉ፡፡
“የሒሳብ ባለሞያ ማለት የደንበኛው የሒሳብ ጠበቃ ማለት ነው፡፡ ሕግ እስካልተላለፍን ድረስ ደንበኛችን ያልተገባ ግብር እንዳይከፍሉ መጠበቅ የኛ ድርሻ ነው፡፡ ይህ እንደወንጀል ለምን ይታያል?” ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
ብዙዎቹ አሁን በሥራ ላይ ያሉ የሒሳብ አዋቂዎች ቀደም ብለው በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተቀጣሪ የነበሩ ከመሆኑ አንጻር በግል ፍቃድ አውጥተው መሥራት ሲጀምሩ ከቀድሞ ባልደረቦቻቸው የጥቅም ትስስር ፈጥረው እንደሚሆን ስለሚታመን ከፍተኛ ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ በተለይም መንግሥት አሁን በሥራ ላይ ያሉ የሒሳብ አዋቂዎች ገቢዎችና ጉምሩክ ዉስጥ ያለን የአሠራር ክፍተት በመጠቀም ግብር የመሰወር አቅም ፈጥረዋል፣ ለቀድሞ ባልደረቦቻቸው እጅ መንሻ በመስጠትም ደንበኞቻቸውን መክፈል ከሚገባቸው ግብር ነጻ ያደርጓቸዋል›› ብሎ በጽኑ ያምናል፡፡ ከፍተኛ ነጋዴዎችና የቢዝነስ ድርጅቶች የሒሳብ ሠራተኞችን ሲቀጥሩ ቀድሞ በገቢዎችና ጉምሩክ ዉስጥ ይሠሩ ለነበሩና ልምድ ላካበቱ ባለሞያዎች ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡
መንግሥት የሂሳብ አዋቂዎችን ብቻ ሳይሆን የትልልቅ ነጋዴዎችን ስልኮች በመጥለፍ የስለላ ስራ ይሰራል፡፡ አሁን በዋና አቃቢ ሕግ መሥሪያ ቤት፣ በፋይናንስ ደኅንነትና በገቢዎችና ጉምሩክ የሂሳብ ደኅንነቶች በኩል ስልካቸው ተጠልፎ 24 ሰዓት ከፍተኛ ክትትል እየተደረገባቸው ያሉ ከ200 በላይ ከፍተኛ ነጋዴዎች እንዳሉ እንሚያውቅ ለዋዜማ የተናገረ አንድ የቀድሞ የገቢዎችና ጉምሩክ መሥሪያ ቤት ባልደረባ ‹‹የንግዱን ማኅበረሰብ በዚህ መንገድ አለቅጥ ማሸበር ዞሮ ዞሮ አገሪቱን ነው የሚጎዳው›› ይላል፡፡ በቅርቡ ወደ እስር ቤት ሊጋዙ የሚችሉና ስማቸው ጥቁር መዝገብ ላይ የሰፈረ ነጋዴዎች ስማቸውን ከጥቁር መዝገብ ለማስፋቅ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር እንደሚጠየቁ እንደሚያውቅ፣ ስማቸውን ካስፋቁ በኋላም ለተወሰኑ ቀናት ከአገር ወጥተው እንዲሰነብቱ እንደሚደረግ ለዋዜማ አብራርቷል፡፡
‹‹እውነት ለመናገር ፍትሀዊ አሰራር የለም፣ በተመሳሳይ ወንጀል ዉስጥ ያሉ ሰዎች ከፊሎቹ ሲታሰሩ ሌሎች ከገዢው ፓርቲ ጋር ባላቸው ቅርበት የተነሳ ብቻ ክስ እንዲቋረጥላቸው ይደረጋል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመንግሥት ላይ እምነት እያጣ በመምጣቱ የአቅሙን ያህል በአገሪቱ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ እንኳ ይሸማቀቃል፡፡ ሰዎች ግብር ደስ እያላቸው እንዲከፍሉ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ዜጎችን መፍጠር መቆም አለበት››ሲል ሀሳቡን ያጠቃልላል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለግል ኦዲተሮችና ለሂሳብ አዋቂዎች የሞያ ብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የመስጠት፣ የማደስና የመሠረዝ ስልጣን ይዞ ቆይቷል፡፡ በአገሪቱ ከ600 በላይ የሂሳብ አዋቂዎችና የኦዲተር ሥራ የሚሰሩ ድርጅቶች ይገኛሉ፡፡ ለነዚህ ድርጅቶች የፍቃድ ማደስ ሥራ ከጥር 2007 ጀምሮ በአዋጅ ለተቋቋመው የኦዲቲንግና ሂሳብ ቦርድ ተላልፏል፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ከተፈቀደላቸው የሂሳብ አዋቂዎች ጋር ተከታታይ ስብሰባዎች ተከናውነዋል፡፡ የመሥሪያ ቤቱ የሕግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ባልደረባ ለተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎች እንደተናገሩት በ‹‹3ቱ የመ ሕጎች›› ካልሰራን እናንተን ከማሰር የሚመልሰን የለም ሲሉ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡ የ ‹‹3ቱ መ›› ህጎች መማማር፣ መመካከርና መጠያየቅ ናቸው፡፡