ሰሞኑን ኢሕአዴግን ጨምሮ 107 የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ የአሠራር ስርዓት ቃል ኪዳን ሰነድ ፈርመዋል፡፡ ሰነዱን ታሪካዊ ሲሉ ያሞካሹት እንዳሉ ሁሉ፣ የለም ሀገሪቱ ካለችበት የፖለቲካ ውጥረት አንፃር ሰነዱ ከወረቀት የዘለለ ሚና አይኖረውም ሲሉ የሚከራከሩ አልጠፉም። ቻላቸው ታደሰ የሚከተለውን ፅፏል

PHOTO-FILE

የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ

ዋዜማ ራዲዮ- ሰሞኑን ኢሕአዴግን ጨምሮ 107 የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ የአሠራር ስርዓት ቃል ኪዳን ሰነድ ፈርመዋል፡፡ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም በተናጥል ፈርመዋል፡፡ ፖለቲካ ድርጅቶች ሰነዱ ብዙ ውይይት አድርገውበት ሲያበቁ ስምምነት የደረሱበት እንደሆነም ተነግሯል፡፡ ሰነዱ 20 አንቀጾችን የያዘ ሲሆን ርዕሱም “በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እንዲሁም በተናጥል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሠራር ሥርዓት” ይላል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች መብትና ግዴታ እንዲሁም ርስበርሳቸው ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት ባጭሩ ይዳስሳል፡፡ ሰነዱን የፈረሙ የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ ምክር ቤት እንደሚቋቋሙም ተገልጧል፡፡

ባጠቃላይ የሰነዱ መፈረም ለሀገሪቱ መድበለ ፓርቲ እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ነው እየተገለጸ ያለው፡፡ ከሰነዱ መፈረም በኋላም ሁሉም ፈራሚ ድርጅቶች የተወከሉበት የጋራ ምክር ቤት ለማቋቋም ወስነዋል፡፡ ዘለግ ያለው ምክክራቸው አንዱ የረባ ውጤት ሊባል የሚችለውም ይሄው ነው፡፡ ተቀራርቦ ለመነጋገርም ይሁን ድርጅታዊ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አንድ የተማከለ ተቋማዊ አሰራር መፍጠራቸው በጄ ሊባል የሚገባው ርምጃ ነው፡፡

ይህን ሰነድ መሠረት አድርጎ ሰነዱ አሁን ባለው ይዘቱ ለሀገሪቱ ዲሞክራሲ ግንባታ ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ሰነዱ በይዘቱ ምን ውስንነቶች አሉበት? ተግባራዊነቱስ ምን መሰናክሎች ይገጥሙታል? የሚሉትን ጉዳዮች አንስቶ ማየት ጠቃሚ ይመስለናል፡፡

በርግጥ በ2002 ዓ.ም መንግሥት ሕጋዊ አንድምታ ያለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስነ ምግባር አዋጅ በማጽደቅ ሥራ ላይ አውሎ ነበር፡፡ ሆኖም በዋናነት ገዥው ፓርቲ በዚያው ዐመት ለተካሄደው ሀገር ዐቀፍ ምርጫ በብቸኝነት ነበር የተጠቀመበት፡፡ ምናልባት ያሁኑን የተለየ የሚያደርገው ምርጫ ሳይሆን ምርጫ ነክ ያልሆኑ ጉዳዮችን መሸፈኑ ሊሆን ይችላል፡፡ ባብዛኛው ከሕጋዊነት ይልቅ በድርጅቶቹ ላይ የሞራል ተጠያቂነትን ብቻ ለመጫን ያለመ መሆኑም ከዚህ አዋጅ ይለየዋል፡፡

ሰነዱ ምንም እንኳ በዋናነት የሞራል ድንጋጌ ቢሆንም መሠረታዊ ክፍተቶች እና ውስንነቶች አሉበት፡፡ ብዙ ክፍተቶችን፣ በቁንጽል የቀሩ ድንጋጌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህ ዝግጅት ግን መሠረታዊ፣ ተቋማዊና መዋቅራዊ በሆኑት ላይ ብቻ እናተኩር፡፡

በመጀመሪያ የሰነዱ ርዕስ “በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚኖረውን ግንኙነት እንዲሁም በተናጥል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሠራር ሥርዓት” ነው የሚለው፡፡ መቸም የአሰራር ሥርዓት ሲባል መሠረታዊ መርሆዎችን፣ መደበኛ ወይም ኢመደበኛ ተቋማዊ አሠራሮችን፣ ደንቦችን እና ድንጋጌዎችን ማቀፍ አለበት፡፡ ከብሄር እስከ ርዕዮተ ዜግነት፣ ከክልል እስከ ሀገር ዐቀፍ ሁሉንም ፓርቲዎች ያቀፈ ቃል ኪዳን እንደመሆኑ ፓርቲዎችና ሀገሪቱ አሁን ካሉበት ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም መሆን ይጠበቅበታል፡፡

ሆኖም ሰነዱ “የአሠራር ሥርዓት” ለመባል የሚያበቃ ምሉዕነት አለው ማለት አይቻልም፡፡ በይዘቱም ይሁን በማዕቀፍ ወሰኑ የተሟላ ሰነድም አይመስልም፡፡ ሰነዱ የስነ ምግባር መርሆዎች በሕግ ወንጀል ከሆኑ ክልከላዎች ጋር ተቀላቅለው የሠፈሩበት መሆኑም ሌላው ችግሩ ነው፡፡ የሰነዱ ወሰንም እስከምን ድረስ እንደሆነ ግልጽነት ይጎድለዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ በአዋጁ መሠረት በሚያስቀምጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለመመዝገብ በሂደት ላይ ያሉ ድርጅቶች ሁሉ በቃል ኪዳን ሰነዱ እንደታቀፉ ተጠቅሷል፡፡ ገና በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያልተመዘገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች ግን በጋራ ውይይቱ ተሳታፊ መሆናቸው ገና ከጅምሩም ብዙ ጭቅጭቅ አስነስቶ እንደነበር በወቅቱ ተዘግቦ ነበር፡፡ ያም ሆኖ አሁን እንደታየው ያልተመዘገቡ ድርጅቶች በሂደቱ ከመሳተፍ አልፈው የሰነዱ ፈራሚዎች ሆነዋል፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ገለልተኛ ሆኖ ሊዋቀር መሆኑን የሚናገረው ምርጫ ቦርድ እንዴት ይህን ሊቀበለው ቻለ? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳው፡፡

ከዚህ ይልቅ ማንኛውም ያልተመዘገበ ድርጅት ወደፊት ከቦርዱ የምዝገባ ምስክር ወረቀቱን ሲያገኝ የጋራ ምክር ቤቱ አባል ለመሆን ጠይቆ አባል እንዲሆን የሚፈቅድ አንቀጽ ነበር መቀመጥ የነበረበት፡፡ እንደዚያ ዐይነት አንቀጽ በሰነዱ አልተካተተም፡፡ በሕጉ መሠረት መመዝገብ ያልቻለ ድርጅት ከጋራ ምክር ቤቱ እንደምን እንደሚሰናበትም የተቀመጠ ድንጋጌ ሰነዱ ላይ አይታይም፡፡ እዚህ ላይ አሁን የቃል ኪዳን ሰነዱ ፈራሚ የሆነውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን (ኦነግ) እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ ኦነግ ድሮ በሽግግር ዘመኑ ወቅት ሕጋዊ ድርጅት ስለነበርኩ ድጋሚ አልመዘገብም ብሏል ባለፈው ከምርጫ ቦርድ ጋር በፈጠረው ውዝግብ፡፡ ምናልባት ከዚያ በኋላ አቋሙን ቀይሮ ይሁን አይሁን በይፋ የገለጸው ነገር የለም፡፡

ድርብ ዜግነት የያዙ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች በሰነዱ ረቂቅ ዝግጅት መሳተፋቸው ጥያቄ አስነስቶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ወደፊትም ድርብ ዜግነት ያላቸው አመራሮች በጋራ ምክር ቤቱ ሊወከሉ ይችላሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ እንደገና አከራካሪ ሆኖ መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡

ሌላው ጉዳይ የቃል ኪዳን ስምምነቱ በመንግሥትና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ነው? ወይስ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ብቻ? የሚለውን ጥያቄ ግልጽ አድርጎ አለማስቀመጡ ነው፡፡ የሰነዱ ተፈጻሚነት በተፈራራሚ ፖለቲካ ድርጅቶች እና በአመራሮቻቸው፣ አባላት፣ ተጠሪዎቻቸውና ወኪሎቻቸው ላይ ብቻ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ግን ፖለቲካ ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ጭምር አንቀጾችን አካቷል፡፡ ከመንግሥት የሚጠበቁ ግዴታዎችንም አካቷል፡፡ ሆኖም ፖለቲካ ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት ሊወሰን የሚችለው በምርጫ ቦርድ አዋጆች እና በሌሎች የሀገሪቱ ሕጎች ስለሆነ ሰነዱ ከመንግሥት ይልቅ ከገዥው ድርጅት ጋር፣ ገዥው ድርጅትም ከተቃዋሚዎች ጋር ስለሚኖራቸው መስተጋብር ብቻ መዳሰስ ይገባው እንደነበር ማንሳት ይቻላል፡፡ በርግጥ ስለ መንግሥት የተነሳውም ቢሆን ቁንጽል እንጅ ምሉዕነት ያለው ነገር አይደለም፡፡

ሌላው መጠቀስ ያለበት ችግር መዋቅራዊ የሆኑ የሀገሪቱ ፖለቲካዊና ሕጋዊ ማነቆዎች ሳይፈቱ የቃል ኪዳን ሰነዱን መፈረሙ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ከሥርዓቱ ጥንስስ ጀምሮ ኢሕአዴግም ሆነ መንግሥት ከተቃዋሚ ድርጅቶች ብሎም ጋር ያላቸው መስተጋብር ሚዛኑን ያልጠበቀ፣ ኢፍትሃዊነት ያደላበት እና ተዋረዳዊ የሆነ መስተጋብር ነው፡፡ እናም ኢሕአዴግም ሆነ መንግሥት ነባሩን መስተጋብር ለመቀየር ምን ያህል ተነሳሽነት አላቸው? ወደፊትስ ምን ተጨማሪ አወንታዊ ርምጃዎች ሊወስዱ ይችላሉ? የሚሉ በስጋት የታጀቡ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያደርገናል፡፡ የገዥው ፓርቲ መዋቅር ግን ከመንግሥት መዋቅር ሊላቀቅ ይቅርና ገና ለማላቀቅም ሙከራው አልተጀመረም፡፡ እንዲያውም ከአፋዊ ትርክት የዘለለ ፍላጎትም ያለ አይመስልም፡፡

ይህን የምንልበት ሌሎች አዳዲስ ተጨማሪ ምክንያቶችም አሉ፡፡ ባለፉት ዐመታት ነፍጥ አንስተውም ይሁን ሳያነሱ በስደት መንግሥትን ሲቃወሙ የነበሩ ተቃዋሚ ድርጅቶች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በሰላም እንዲታገሉ የጋበዘው ኢሕአዴግ ነው፡፡ የሰሞኑን የቃል ኪዳን ሰነድ እንዲፈርሙ ጥንስሱን ያቀረበላቸውም ራሱ ኢሕአዴግ ነው፡፡ አንዳች የነጠረ ፍኖተ ካርታ ሳይዝ “ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲ አሻግራታለሁ” የሚለውም ከእነ ጨቋኝ መዋቅሩ ዛሬም ሀገሪቱን እየገዛ ያለው አምባገነኑ ኢሕአዴግ ነው፡፡

በሌላ በኩል በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው በጅምር ለመቅረቱ ዋናው ምክንያት ግን የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች መስተጋብር የሰመረ አለመሆኑ አይደለም፡፡ የተጀመረው ጥረት ከሕገ መንግሥቱ ወደ መሬት ሳይወርድ የይስሙላ ሆኖ የቀረው ገዥው ፓርቲ ስር በሰደዱ መዋቅራዊ፣ ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ማነቆዎች ስለተበተበው እንጅ… አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ከርዕዮተ ዐለም ወይም መደብ ይልቅ በማንነት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸው ማንነትን ዋነኛው የግጭት መነሾ ሊያደርግ እንደሚችል የታወቀ ቢሆንም ተቃዋሚ ድርጅቶች ግን የርስበርስ ግጭት ፈጥረው ሀገሪቱን ለችግር የጣሉበት አጋጣሚ እምብዛም አልታየም ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው እንግዲህ ለዲሞክራሲ ግንባታና መድበለ ፓርቲ ፖለቲካ መዳበር ወደፊትም የመሪነቱን ሚና መጫወት ያለበት ኢሕአዴግ የሚሆነው፡፡

መንግሥት ዜጎችንና ተቋማትን ከፖለቲካ አመጻ፣ ከወንጀል እና ከቢጅላንቴ ወይም ከመንጋ ፍትህ መከላከል እንዳለበት ሰነዱ ግዴታ ጥሎበታል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመላ ሀገሪቱ የመንቀሳቀስ መብት ማስጠበቅ እንዳለበትም እንዲሁ… ሰነዱ በተፈረመ ማግስት ግን የግንቦት 7 ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አንዳርጋቸው ጽጌ በዚያው ሰሞን በክልሎች መንቀሳቀስ በማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፤ መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን ጠርቅሞ ዘግቶታል ሲሉ መውቀሳቸው የሰነዱ አፈጻጸም ወደፊት የሚገጥመውን ችግር ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ሆኗል፡፡

ባጭሩ አልሆነም እንጅ ሰነዱ ተቃዋሚ ድርጅቶች ሥልጣን ከያዘው ፓርቲ ጋር ስለሚኖራቸው ግንኙነት ብሎም ከገዥ ፓርቲ ስለሚጠበቁ የስነ ምግባር ግዴታዎች በተለየ አጽንዖት መስጠት የነበረበት ይመስለናል፡፡ እናም ባሁኑ የዘነዱ ይዘት ኢሕአዴግ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ገዥው ድርጅት አሠራሩን እና ርዕዮተ ዐለሙን እስካልቀየረ ድረስ የጋራ ምክር ቤቱም ስም ብቻ ሆኖ ይቀር እንደሆነ እንጅ የረባ ለውጥ ማምጣት የሚችልበት ዕድል ጠባብ ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው የሰነዱ መፈረም ብቻውን ተቃዋሚ ድርጅቶችን ካሁኑ ጮቤ ሊያስረግጣቸው የማይገባው፡፡

ወደ ተቃዋሚ ድርጅቶች ብቻ ደሞ እንምጣ፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት እንዋሃዳለን ሲሉ የከረሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተባዝተው 107 መድረሳቸው የርስበርስ ግንኙነቱንም ሆነ የሀገሪቱን መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ትርጉም እያሳጣው ይገኛል፡፡ በዚህ ሰዓት ድርጅቶቹ ወደጋራ የቃል ኪዳን ውል የገቡት እንወክለዋለን፤ ማኅበራዊ መሰረታችን ነው በሚሉት ሕዝብ ስም ጭምር ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ግን በሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት ይቅርና ከነመኖራቸውም በሕዝቡ ዘንድ የታወቀላቸው ስለመሆኑ አፋቸውን ሞልተው መናገር የሚችሉ አይደሉም፡፡ እወክልኻለሁ ከሚሉት ሕዝብ ጋር ማኅበራዊ ውል የገቡትም ቢሆኑ ውላቸው በጣም ልል እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡ እናም ለርስበርስ ግንኙነታቸው ቃል ኪዳን ከመግባታቸው በፊት እንወክለዋለን ከሚሉት ሕዝብ ጋር አዲስ ዲሞክራሲያዊ ውል በመግባት ወይም ነባሩን ቢያጠነክሩ ይሻል እንደነበር መናገር ይቻላል፡፡

የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጠ ዲሞክራሲ ባህል የሌላቸው መሆኑም ሌላኛው ጉዳይ ነው፡፡ መቸም ፓርቲዎች ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ ግንኙነት ሊያዳብሩ የሚችሉት መጀመሪያ የውስጠ ዲሞክራሲ አሰራርን ማስፈን ሲችሉ እንደሆነ ዐሊ የሚባል አይደለም፡፡ እናም ውስጠ ዲሞክራሲያዊ አሰራርን መከተል ለሰነዱ ፈራሚዎች እንደ ገዥ መርህ ሊቀመጥላቸው ይገባ ነበር፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰነዱ ፖለቲካ ድርጅቶች ኢመደበኛ ቡድኖችን በተዘዋዋሪ ማደራጀት እና መምራት እንዳይችሉ፣ ለኢመደበኛ ቡድኖች (ቪጅላንቴዎች) ይፋዊ ዕውቅና እንዳይሰጡ፣ በሕግ ባልታወቀ ስም እንዳይጠሩ ወይም የመንጋ ፍትህን በመገናኛ ብዙኻን እንዲያወግዙ በግልጽ አለማድረጉ አንድ ጉድለት ነው፡፡ ይህን የምንለው አሁን በሀገሪቱ ያለው አንዱ ተጨባጭ ችግር እሱ ስለሆነ ነው፡፡ በርግጥ ማንኛውም ድርጅት ከማናቸውም የሃይል አድራጎትና ሁከት እንዲታቀብ ሰነዱ ያዛል፡፡

ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ የምርጫ ቦርድ አዋጆችና ደንቦች ገና ከተሻሻሉ ቃል ኪዳን ሰነዱ መጽደቁ ነው፡፡ በርግጥ ወደፊት ሊሻሻል ይችላል፡፡ ቢሆንም የቦርዱ ማሻሻያ ቢቀድም ኖሮ ሰነዱ ቦርዱ ወደፊት በሚያሻሽለው የፓርቲዎች ስነ ምግባር አዋጅ የሚካተቱ ገዥ መርሆዎችንና አንቀጾችን እንደ ግብዓት መጠቀም ይችል እንደነበር መናገር ይቻላል፡፡

ሰነዱ የስነ ምግባር መርሆዎችን እና የሕግ ጉዳዮችን አጣምሮ የያዘ መሆኑም የማዕቀፍ ወሰኑን የለጠጠው ይመስላል፡፡

በጠቅላላው የቃል ኪዳን ሰነዱ ፖለቲካ ፓርቲዎች በበቂ ሁኔታ መክረውበት፣ ግልጽ እና የተሟላ ሆኖ የወጣ ሰነድ ነው ማለት አይቻልም፡፡ እስካሁን ሲለፋበት የኖረው የቃል ኪዳን ሰነድ ይህ ከሆነ በርግጥም የሚያስተዛዝብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምርጫ ቦርድ ሲጠቀምበት ከነበረው የፓርቲዎች የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ አንጻር ሲመዘን ደሞ ብዙ ጉድለት ነው የሚታይበት፡፡ ከሞራልና ስነ ምግባር አንጻርም ቢሆን የረባ አሳሪ ቃላት አሉት ማለት አይቻልም፡፡ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ