Okello Akway
Okello Akway

(ዋዜማ)- ከሶሰት ሳምንት በፊት በአገር መገንጠል ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉት የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት ኦኬሎ አኳይ ዛሬ ዘጠኝ ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደባቸው፡፡

በደቡብ ሱዳን በነበሩበት ወቅት ከሁለት ዓመት በፊት ተይዘው ለኢትዮጵያ ተላልፈው የተሰጡት አቶ ኦኬሎ ከሌሎች ስድስት ተከሳሾች ጋር በሰኔ 2006 ዓ.ም የሽብርተኝነት ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ክሳቸውን ሲከታተሉ የቆዩት እነ ኦኬሎ መጋቢት 28 በዋለው ችሎት በተጠረጠሩበት “የጋምቤላን ክልል ከፌደሬሽኑ የመገንጠል ሙከራ” ጥፋተኛ ቢባሉም የተከሰሱበት ህግ ከጸረ-ሽብር አዋጅ ወደ ወንጀለኛ ህግ እንዲዛወር ተደርጎላቸው ነበር፡፡

እነ ኦኬሎ ጥፋተኛ የተባሉበት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 241 “የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት” የሚደረግ ወንጀልን የሚዳስስ ነው፡፡ ማንም ሰው “ከፌዴሬሽኑ ግዛት ወይም ሕዝብ ከፊሉ እንዲገነጠል የሚያደርግ ተግባር የፈጸመ እንደሆነ” ከአስር ዓመት እስከ 25 ዓመት ለመድረስ በሚችል ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡ ነገሩ ከባድ ከሆነ ቅጣቱ እስከ እድሜ ልክ እስራት ባስ ሲልም እስከ ሞት ሊደርስ እንደሚችልም በህጉ ተቀምጧል፡፡
አቃቤ ህግ በአንደኛ ተከሳሽ ኦኬሎ አኳይ እና በሁለተኛ ተከሳሽ ዴቪድ ኡጁሉ ላይ ከባድ ቅጣት እንዲተላለፍ ለችሎቱ የቅጣት አስተያየት አስገብቶ እንደነበር የቀኝ ዳኛ ሣሙኤል ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ሁለቱ ተከሳሾች ወንጀል ለመፈፀም በተቋቋመ ቡድን አመራር፣ የደህንነት ዘርፍ እንዲሁም የውጭ ግንኙነት ሃላፊ በመሆን መሳተፋቸውን አቃቤ ህግ በቅጣት አስተያየቱ ላይ አመልክቷል፡፡

አቃቤ ህግ ኦኬሎ እና ዴቪድ ገንዘብ በማሰባሰብ እና አባላትን በመመልመል፣ የቡድኑን አባላት ወታደራዊ ስልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ መሳሪያ በመግዛት፣ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለማግኘት ከኤርትራ መንግስት ጋር እና ከኦነግ እና ግንቦት ሰባት ከተባሉ ቡድኖች ጋር በመደራደር በከፍተኛ አመራርነት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በመዘርዘር ቅጣታቸው በከባድ እንዲያዝ ጠይቆ ነበር፡፡ ሆኖም በድርጊቱ ምንም አይነት የሰውም ሆነ የንብረት ጉዳት ያልደረሰ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በከባዱ እንዲቀጡ የሚለውን የአቃቤ ህግ አስተያየት አልተቀበለውም፡፡

የወንጀል ህጉን አንቀጽ 84 በመጥቀስ ተከሳሾች የወንጀል ተግባሩን የፈፀሙት ቡድን መስርተው በስምምነት መሆኑን እና ይህም በቅጣት ማክበጃነት እንዲያዝለት አቃቤ ህግ በተጨማሪነት ለፍርድ ቤቱ አመልክቶ ነበር፡፡ ይህንን የአቃቤ ህግን የቅጣት ማክበጃ ፍርድ ቤቱ ተቀብሎታል፡፡

ተከሳሾች በበኩላቸው ያቀረቧቸውን ሶስት የቅጣት ማቅለያዎችም በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ተቀባይነት ያገኙት ማቅለያዎች ተከሳሾቹ በምንም አይነት ወንጀል ከዚህ በፊት ተከሰው የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዳልተላለፈባቸው፣ ሁሉም ተከሳሾች የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸው እና የተከሰሱበትም ድርጊት በሙከራ ደረጃ ያለ መሆኑን የጠቀሱባቸው ናቸው፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ማቅለያ እና ማክበጃ ከተመለከተ በኋላ ባስተላለፈው ብይን መሰረት በጋምቤላ ህዘቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋህነን) አመራርነት ተሳትፈዋል በተባሉት ኦኬሎ አኳይ እና ዴቪድ ኡጁሉ የዘጠኝ አመት ፅኑ እስራት ፍርድ አስተላልፏል፡፡ የጋህነን አባል በመሆን የተለያዩ ተሳትፎዎች አድርገዋል በተባሉት እና በክሱ ከሶስተኛ እስከ ሰባተኛ ተዘርዝረው ባሉ ተከሳሾች ላይ ደግሞ የሰባት አመት ፅኑ እስራት ፈርዶባቸዋል፡፡

የሰባት ዓመት ፍርድ የተላለፈባቸው ኦቻን ኦፒዬ፣ ኡማን ኝክየው፣ ኡጁሉ ቻም፣ አታካ ኡዋር እና ኡባንግ ኡመድ የተባሉት ተከሳሾች ናቸው፡፡ ሁሉም ተከሳሾቹ ከማንኛውም ህዝባዊ መብቶቻቸው ለሁለት አመታት እንዲታገዱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡