PM Hailemariam Desalegn- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በትናንትናው ዕለት በፖሊስ ታስረው ችሎት እንዲቀርቡ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ የጸረ-ሙስና ጉዳዮች ችሎት ትዕዛዝ ያወጣባቸው በሙስና ክስ ላይ በመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በበይነ መረብ ግንኙነት ዘዴ በርቀት ሆነው ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ እንዲፈቅድላቸው ባለፈው ጥር 30 ለችሎቱ በጽሁፍ ባስገቡት አቤቱታ ጠይቀዋል።

ኃይለ ማርያም የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ የታዘዙት እና በበይነ መረብ በርቀት ልመስክር ሲሉ አቤቱታ ያቀረቡት፣ በቀድሞው የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ላይ ከትራክተሮች ግዥ ጋር በተያያዘ ለተመሠረተው የሙስና ክስ ነው። ኃይለ ማርያም ይህንኑ አቤቱታቸውን ለችሎቱ ያቀረቡት፣ የሥራ ቦታቸው ከኢትዮጵያ ውጭ መሆኑን በመጥቀስ ነው።


ካሁን ቀደም ችሎት ቀርበው የመከላከያ ምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ከፍርድ ቤት የደረሳቸው ምንም ዓይነት ትዕዛዝ እንደሌለ በአቤቱታቸው የገለጡት ኃይለ ማርያም፣ ችሎቱ ታስረው እንዲቀርቡ ባለፈው ጥር 5፣ 2014 ዓ፣ም ትዕዛዝ ማውጣቱን የሰሙት ከማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እንደሆነ ጠቁመዋል። ኃይለ ማርያም አያይዘውም፣ ችሎቱ ይህንኑ ተረድቶ ለዛሬ ታስሬ እንድቀርብ ያወጣባኝን ትዕዛዝ ያንሳልኝ በማለት ጠይቀዋል።

ኃይለ ማርያም በሜ/ጀኔራል ክንፈ የሙስና ክስ የመከላከያ ምስክርነታቸው ዙሪያ አቤቱታ ያቀረቡት፣ የመከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡ ችሎቱ ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ካወጣ በኋላ ነው።


የተከሳሾች ጠብቆች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ኃይለ ማርያም ለሚመሩት ፋውንዴሽናቸው የችሎቱን መጥሪያ ወረቀት መስጠታቸውን እና ጸሃፊያቸው መጥሪያውን በኢሜል ለኃይለ ማርያም እንደላኩላቸው ችሎት ቀርበው መናገራቸውን ለችሎቱ አብራርተዋል። ሆኖም ጠበቆቹ ኃይለ ማርያም በበይነ መረብ በርቀት የምስክርነት ቃላቸውን ለችሎቱ ቢሰጡ ተቃውሞ እንደሌላቸው ገልጸዋል።


የተከሳሾች ጠበቆች በጀርመን የቀድሞው የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ሌላኛው የመከላከያ ምስክር አምባሳደር ፍስሃ አስገዶም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ወደ አገር ውስጥ መግባት እንደማይችሉ ጠቅሰው፣ ችሎቱ የምስክርነት ቃላቸውን በበይነ መረብ እንዲሰጡ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ዓቃቤ ሕግ በበይነ መረብ በርቀት በሚቀርቡ ምስክርነቶች ላይ ተቃውሞ ይኖረው እንደሆነ ችሎቱ ላቀረበለት ጥያቄ፣ ተቃውሞ የለኝም ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። ችሎቱም ምስክሮች በበይነ መረብ በርቀት ምስክርነት የመስጠታቸውን ጉዳይ ከፍርድ ቤቱ አስተዳደር ክፍል ጋር ተነጋግሮ በቀጣዩ ሰኞ ውሳኔውን እንደሚያሳውቅ ገልጧል።


ጠበቆቹ በመከላከያ ምስክርነት የጠሯቸው ሌላኛው የመከላከያ ምስክር የቀድሞው መከላከያ ሚንስትር ሲራጅ ፈጌሳ በዕለቱ በአካል ችሎት ተገኝተው እንዲመሰክሩ ቀጠሮ ተይዞ ነበር። ሆኖም ሲራጅ ባጋጣሚ ለሥራ ጉዳይ ከአገር ውጭ በመሆናቸው ችሎቱ ለቀጣዩ ሰኞ እንድናቀርባቸው ይፈቀድልን በማለት ጠበቆች አቤቱታ አቅርበዋል። ችሎቱም አቤቱታውን ካዳመጠ በኋላ የሲራጅን የምስክርነት ቃል በመጭው ሰኞ ለመስማት ቀጠሮ ሰጥቷል።


በሌላ በኩል የመከላከያ ምስክር ሆነው የተቆጠሩት ጡረተኛው የቀድሞው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ሳሞራ የኑስ በትናንቱ ችሎት በአካል ቀርበዋል። ሆኖም የተከሳሾች ጠበቆች ጀኔራል ሳሞራ በሜቴክ የትራክተር ግዥ ዙሪያ ዝርዝር መረጃ ስለሌላቸው ከምስክርነት ዝርዝር ይሰረዙልኝ በማለቱ፣ ችሎቱ ጀኔራል ሳሞራ በአካል በመቅረባቸው አመስግኖ አሰናብቷቸዋል።


ችሎቱ በዕለቱ የተመለከተው ሌላኛው ጉዳይ ሜ/ጀኔራል ክንፈ ዳኘው እና አራት ተከሳሾች የተከሰሱበትን ከመርከብ ግዥ እና ሽያጭ ጋር የተያያዘውን የሙስና ክስ ነበር። በዚሁ የመርከብ ግዥ እና ሽያጭ የሙስና ክስ ላይ በመከላከያ ምስክርነት ለተቆጠሩት የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር እና የአሁኑ የኢጋድ ዋና ዳይሬክተር ወርቅነህ ገበየሁ የፍርድ ቤቱ መጥሪያ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በኩል ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር ተገልጧል። ውጭ ጉዳይ ሚንስቴርም መጥሪያውን ለወርቅነህ ለማድረስ 10 ቀናት ይሰጠኝ ሲል በጽሁፍ ያቀረበውን አቤቱታ ችሎቱ በንባብ አሰምቷል።


በዚሁ የመርከብ ግዥ እና ሽያጭ የሙስና ክስ በመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩት ሌሎች ምስክሮች የቀድሞዎቹ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አምባሳደር ድሪባ ኩማ እና መኩሪያ ኃይሌ ሲሆኑ፣ የተከሳሽ ጠበቆችም ሁለቱ ምስክሮች በሚሰሩባቸው መስሪያ ቤቶች በኩል መጥሪያ እንዲደርሳቸው ችሎቱ ይዘዝልኝ ሲሉ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ጠበቆች በመከላከያ ምስክርነት የቆጠሯቸው አራት የመከላከያ ሚንስቴር.ባልደረባ የሆኑ ምስክሮች ባሁኑ ወቅት እስር ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ መስሪያ ቤታቸው መከላከያ ሚንስቴር ችሎት እንዲያቀርባቸው ችሎቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው አቤቱታ አቅርበዋል።


ችሎቱ በጠበቆች አቤቱታ ላይ ከመከረ በኋላ፣ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ለወርቅነህ ገበየሁ መጥሪያውን ቶሎ እንዲያደርስና መጋቢት 19 በአካል ችሎት ቀርበው እንዲመሰክሩ አዟል። መከላከያ ሚንስቴርም እስር ላይ ያሉትን አራት የመከላከያ ምስክሮች በተመሳሳይ ዕለት ችሎት እንዲያቀርብ ታዟል። አምባሳደር ድሪባ ኩማ እና መኩሪያ ኃይሌ ደሞ በመስሪያ ቤታቸው በኩል የፍርድ ቤቱ መጥሪያ እንዲደርሳቸው ችሎቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። [ዋዜማ ራዲዮ]