Former Somali regional president Abdi Omer Mohammed


ዋዜማ ራዲዮ- በልደታ ከፍተኛ ፍርድቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ (ዓርብ) የቀረቡት የቀድሞው የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ኢሌ “ ፍትህ አገኛለሁ የሚል እምነት የለኝም ከአቃቤህግ በላይ ፍርድ ቤቱ ነው እየከሰሰን ያለው…..” ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። ከዛሬ ጀምሮ ከጠበቆች ጋር ያለኝን ስምምነት አቋርጫለሁ ብለዋል፡፡


ረፋዱ ላይ በከፍተኛ አጀብ በልደታ ከፍተኛ ፍርድቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት የመጡት የቀድሞው የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ መሀመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) ና በመዝገቡ ያሉ ተከሳሾች በፌደራል ፖሊስና በማረሚያ ቤት ወታደሮች ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገባቸው ወደ ችሎት ገብተዋል፡፡ ዳኞች ከተሰየሙ በውኃላ መዝገቡ የተቀጠረው በ 1ኛ ተከሳሽ አቶ አብዲ መሀመድ ዑመር(አብዲ ኢሌ) ላይ በአማራጭ የቀረበው ክስ እንዲሻሻልና በ43ኛ ተከሳሽ ዘምዘም ሀሰን ላይ በጾታ ጋር ክሱ ላይ ወንድ ተብሎ የቀረበው እንዲሸሻል ነበር ፡፡

አቃቤ ህግ የተሻሻለውን ክስ ለተከሳሾች ካደረሰ በኀላ ችሎቱ የተነበበ ሲሆን መቃወሚያ አንዳላቸው የተጠየቁት የተከሳሽ ጠበቆች የ1ኛ ተከሳሽ ጠበቆች መቃወሚያ እንደሚያቀርቡ ለፍርድ ቤት የተናገሩ ሲሆን የ43ኛ ተከሳሽ ተከላካይ ጠበቃ መቃወሚያ የለኝም ስላሉ ዘምዘም የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰተዋል “ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛ አይደለሁም” ሲሉ በአስተርጉዋሚ በኩል የተናገሩ ሲሆን ወደ መቀጫቸው ከተመለሱ በኋላ በኃላ ጮክ ብለው እያለቀሱ ችሎቱ ለደቂቃዎች ተቐርጦ ቆይቶ ነበር ፡፡


የአብዲ ኢሌ ጠበቃ አቶ ሀይለማሪያም ተመስገን አቤቱታ እንዳላቸው ለችሎቱ ተናግረው እድል የተሰጣቸው ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ንግግራቸውን ሳይጨርሱ አስቁሞ “ ይህ አቤቱታ መቅረብ ያለበት አሁን አይደለም ብሎ ሲያቋርጣቸው 1ኛ ተከሳሽ አብዲ ኢሌ እጃቸውን አውጥተው “በ እኔ ላይ የተለየ ጫና ነው ያለብኝ፣ ጠበቆቼ እንዲናገሩ አይፈቀድም ፤ የመናገር መብታችን ተዘግታል እዚህ መጥተን አቃቤ ህግ እና ዳኞች የምትሉትን ነው ሰምተን የምንሄደው” ሲሉ በብስጭት ተናግረዋል “በዚህ ሂደት ፍትሀዊ ፍርድ እናገኛለን ብለን አናምንምም አንጠብቅምም ከዛሬ ወዲህ ጠበቃ የለኝም ውሌን አቐርጫለሁ እኔም አልናገርም….” ብለዋል


ዳኞች ተከሳሽ በችሎት እምነት ሊኖራቸው እንደሚገባና ፍርድ ቤቱ ሙሉ በሙሉ ነፃ እንደሆነ ተናግረው ችሎቱ ተከሳሾች እንዲናገሩ እድል እየሰጠ የፍርድ ቤቱን የፍርድ ቤቱን የስራ ቋንቋ ለማይችሉ ከ ኢቢሲ (ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን )አበል እየከፈለ አስተርጓሚ አስመጥቶ እየሰራ ያለው ትክክለኛ ፍትህ ለመስጠት ነው ብለዋል::


የአንደኛ ተከሳሽ ጠበቃ አቶ ሀይለማሪያም “ፍርድ ቤቱ ተናግረን ሳንጨርስ ያስቆመናል፤ የደንበኞቻችን ቅሬታ የኛም ቅሬታ ነው ፤ አቤቱታችንን ተናግረን እንድንጨርስ ይፈቀድልን” ብለዋል ጠበቃው አያይዘውም “ነሀሴ 1 ቀን 2011 በሪፖርተር ጋዜጣ ድረ-ገፅ ላይ የወጣው የውሸት ዜና ደንበኛዬ በማረሚያ ቤት በጥርጣሬ እንዲታይ አድርጎብኛል የጋዜጣው አዘጋጅ ቀርቦ እንዲያስረዳ ትእዛዝ ይሰጥልን” ሲል ጠይቋል:: ሪፖርተር አብዲ ኢሌን ከእስር ቤት ለማስመለጥ የተደራጀ ሀይል አዲስ አበባ ውስጥ መያዙን ዘግቦ ነበር።


ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን በፅሁፍ በፅህፈት ቤት በኩል አያይዘው እንዲያቀርቡ ትእዛዝ የሰጠ ሲሆን ነሀሴ 13 /2011 መቃወሚያቸውን ሲያቀርቡ ትዕዛዝ ይሰጣል ብሏል፡፡
ጠበቃቸው በበኩላቸው “ ደንበኛዬ ጠበቃ አለልፈልግም ያሉት ስሜታዊ ሆነው በመሆኑ ተገናኝተን መነጋገር ስላለብን ጊዜው አጭር ነው ስለሆነ ቀን ይቀየርልን ብለዋል፡፡


በድጋሚ አቶ አብዲ እጃቸውን አውጥተው “ ሚዲያው ውሸት የጀመረው ገና ከመጀመሪያው እስር ቀኔ ነው፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎች ስሜ እየጠፋ ነው፡፡ አንዴ ሰው ገደለ ፤አንዴ ሊያመልጥ ነው እያሉ በዘዴ እኔን ለመግደል ነው” ሲሉ ዳኞች ለነሀሴ 13 መቃወሚያ ለመቀበል ትእዛዝ ሰተናል ብለው ሲነሱ አቶ አብዲ ድምፃቸውን ከፍ አርገው “ምንም መቃወሚያ የለኝም አላቀርብም ጠበቃም የለኝም “ ብለዋል፡፡[ዋዜማ ራዲዮ]