METEC former boss Geb. Kinfe Dagnew

ዋዜማ ራዲዮ- የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው የትራክተር ግዢን በተመለከተ ለቀረበባቸው ክስ መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓም ለመጀመርያ ጊዜ የተከሳሽነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡


ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሙስና ጉዳዮች ችሎትም ቃላቸውን ሙሉ ቀን ሲያዳምጥ መዋሉን ችሎቱን የተከታተለችው የዋዜማ ሪፖርተር ዘግባለች፡፡


ከዚህ ቀደም ጥር 21 2011 ዓ.ም ከሳሽ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ “በትራክተር ግዥ የደረሰ 319.4 ሚሊየን ብር ኪሳራ አለ” በማለት ተፈፀመ ያለውን የወንጀል ድርጊት በዝርዝር የሚያስረዳ ክስ መስርቶ ምስክሮቹን ሲያሰማ ቆየይተቷል፡፡


በቀረበባቸው ክስ ላይ ዛሬ የተከሳሽነት ቃላቸውን የሰጡት ሜ/ጀ ክንፈ ኮርፖሬሽኑ የመንግስት የልማት ድርጅት ሆኖ ሲመሰረት ጀምሮ የነበረውን ጉዞ እና ሲሰራበት የቆየውን ፖሊሲ አስቀድመው በዝርዝር ለዳኞች አስረድተዋል፡፡


ቀጥለውም የቀረበባቸውን እያንዳንዱን የክስ ሀሳብ እያነሱ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
አቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ ላይ “የገበያ ጥናት ሳይደረግባቸው የተገዙ ትራክተሮች በመሆናቸው ሊሸጡ አልቻሉም” በሚል የቀረበውን የክስ ሀሳብ ያስታወሱት ሜጀነራሉ “ሜቴክ የግል ባለሀብት አይደለም! ስለዚህ የገበያ ጥናት ሲደረግ የትኛውን ምርት ባመርት ከፍተኛ ትርፍ አገኛለሁ ተብሎ ሳይሆን እንዴት ነው ሀገሪቱን በልማት መጥቀም የምችለው ተብሎ ነው፡፡ አዎ የገበያ ጥናት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን የተደረገው ጥናት የምርቱን ዋጋ እና ገበያ ላይ የሚቀርብበትን እንዲሁም ተወዳዳሪ አቅራቢዎች የሚሸጡበትን ዋጋ ነው፡፡” በማለት አስረድተዋል፡፡


አክለውም ናዝሬት ትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ በሜቴክ ስር ከመሆኑ በፊት ባሉት 10 አመታት 6 ሺህ ትራክተሮችን ብቻ አምርቶ ወደ 50 ሚሊዮን ብር ገደማ እዳ እንደነበረበት የገለፁት ክንፈ ዳኘው ፋብሪካውን በተረከቡ አንድ አመት ተኩል ጊዜ ውስጥ 15 ሺህ ትራክተሮች ተመርተው 7ሺህ 5መቶ የሚሆኑት ለገበሬው መሸጣቸውን ገልፀዋል፡፡


“ከደምበኛ ከፍተኛ ዋጋ አገኛለሁ ወይ ከሚል እይታ የተሰራን የገበያ ጥናት ልናየውም አንፈልግም ምክንያቱም መንግስት ሀገሪቱን ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ብሎ ላወጣው ፖሊሲ እንዲያግዝ የተቋቋመው ሜቴክ አላማው ማትረፍ አይደለም፡፡” ብለዋል ተከሳሹ፡፡


ሌላው ግልፅ ጨረታ ስላለመደረጉ የሚገልፀውን የአቃቤ ህግን የክስ አካል በተመለከተ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
በሜቴክ የግዢ መመርያ መሰረት “የኮንትራት ግዢ ሲደረግ ዋና ዳየይሬክተሩ ካላፀደቀ በቀር በግልፅ ጨረታ ይደረጋል” የሚል አንቀፅ እንዳለ አንስተዋል፡፡ በመሆኑም “አንቀፁ ዋና ዳይሬክተሩ በልዩ ሁኔታ ያለ ጨረታ ግዢ የሚፈቅዱበት ስልጣን እንዳላቸውም የሚደነግግ ነው፡፡ ከዚህ የትራክትር ግዢ እየተባለ ከቀረበው ጉዳይ አንፃር ደግሞ የተገዛው ትራክተር ሳይሆን የትራክተሩን አካላት እና ቴክኖሎጂውን ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ግዢ ሲደረግ ደግሞ ከዲዛይን ጀምሮ ላይሰንስን እና ብራንድንም የሚያካትት ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ አቅራቢዎች በረጅም ጊዜ ሽያጭ ሊያገኙ የሚችሉትን የሚያሳጣ ነውና ጨረታ ይውጣ ቢባል ዋጋው ከፍ ያለ እና የሀገሪቱ አቅም የማይፈቅደው ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህም ነው የኮንትራት ግዢ ተመራጭ ያደረግነው፡፡” በማለት አስረድተዋል፡፡


ሌላው “ምንም አይነት ስፔስፊኬሸን (መስፈርት) ሳያወጡ ግዢ ተከናወነ” የሚለው የክሱ አካል ሲሆን ለዚህ ምላሽ የሰጡት ሜ/ር ጀነራሉ “እኛ ስፔስፊኬሽን (መስፈርት) እናወጣለን ነገር ግን ለአቅራቢዎቹ አንሰጣቸውም ምክኒያቱም ስፔስፊኬሽን የዲዛይን አካል በመሆኑ እኛ በሰጠናቸው መሰረት ከተሰራ ጠቅላላ የምርት ሂደታቸውንም ነው የሚቀይሩት ያ ደግሞ ዋጋው እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ እኛ ከያዝነው ስፔስፊኬሽን ጋር የሚቀራረበውን ነው የምንመርጠው፡፡” ብለዋል፡፡
ሌሎችም የክስ ሀሳቦችን በዝርዝር እያነሱ ቃል የሰጡ ሲሆን “ፍርድቤት ጥፋተኛ ናችሁ ብሎ ሳይወስንብ በቴሌቭዥን መወንጀላችን የእኛን ስም ለማጠልሸት የተደረገ ፕሮፓጋንዳ ነው” ብለዋል፡፡


በ2.2 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል የተመሰረተው ሜቴክ በ8 አመታት ውስጥ ብቻ ማለትም እስከ 2010 ዓም ድረስ 22 ቢሊዮን ብር መድረሱን የገለፁት ተከሳሹ “በ2010 በተሰራው የኦዲት ሪፖርት አንድም የጠፋ ገንዘብ እንደሌለ ተቀምጧል” ብለዋል፡፡ ይህ ሪፖርትም በገንዘብ ሚኒስትር እና በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ጭምር እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡


በተለይ የቴክኖሎጂ ግዢን በተለከተ ሜቴክ የሄደበት መንገድ እና አሰራሩ ልክ እንደሆነ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት መናገራቸውን የገለፁት ሜ/ጀ ከንፈ ዳኘው “ትክክል እንደሆነ ከመደገፍ በተጨማሪም ግዥው እኛ ባልነው መልኩ እንዲከናወን መመርያ እና አቅጣጫም ሰጥተውናል” ብለዋል፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ምላሽ ይኖራቸው እንደሁ ላቀረብነው ጥያቄ ምላሽ አላገኘንም።


በመጨረሻም “አንድም ሰው አምስት ሳንቲም እንኳን ሊሰጠኝ የዳዳ የለም:: እኔም ልወሰድኩም” ያሉት ሜ/ጀነራሉ “ለዚህም ምክኒያቴ የምወደው ህዝብ እና ሀገር አለኝ ፣ ከዚህ ባለፈም ገንዘብ ብፈልግ እንኳን በስርቆት አላመጣም፣ የምርምር እና የዲዛይን ሰው ነኝ አቅም አለኝ፡፡” ብለዋል፡፡


ችሎቱ የተከሳሽነት ቃላቸውን ካዳመጠ በኋላ ለእሳቸው መከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡ የግዢ ባለሞያን የምስክርነት ቃል መስማቱን ቀጥሏል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]