• የኢትዮጵያ የአንድ ወር የምግብ ዘይት ፍጆታ ግን 86 ሚሊዮን ሊትር እንደሆነ ይገመታል
  • የዘይት ምርት ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች መንግሥት በየካቲት ወር 250 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ፈቅዷል

ይህን ዘገባ ካዘጋጀንበት አንድ ሳምንት በኋላ የምግብ ዘይት ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ተረድተናል። በሀገሪቱ ያለውን የዘይት ገበያ ቀውስ በዝርዝር የተመለከትንበትን ዘገባ እንድታነቡ እንጋብዛለን። ዋና አዘጋጁ

ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ  የምግብ ዘይትን አምርተው ለተጠቃሚዎች ከሚያቀርቡ ሰባት ግዙፍ ፋብሪካዎች መካከል በአሁኑ ሰዓት የዘይት ምርታቸውን ለገበያ እያቀረቡ የሚገኙት አምስት ፋብሪካዎች ብቻ መሆናቸውን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስትር ደኤታ ሀሰን መሐመድ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ 

ዘይትን አምርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ በንግድ እና ቀጠናዊ ትብብር ሚንስቴር መስሪያ ቤት ተመዝግበው ለማኅበረሰቡ ከሚያቀርቡት ፋብሪካዎች በበለጠ፣ የምግብ ዘይት አስመጭነት ፍቃድ ወስደው ዘይት የሚያከፋፍሉት በብዛትም ሆነ በተደራሽነት እንደሚበልጡ ዋዜማ ከሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የሰበሰበቻቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህም ባለሀብቶች ፋብሪካ ከፍተው ዘይት ከማምረት ይልቅ ከውጪ ሀገር እያስመጡ ወደ መሽጡ እንዲያዘነብሉ አድርጓቻዋል። 

የዘይት አስመጪነት ፍቃድ አውጥተው በሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የተመዘገቡ እና የሱፍ እና የአኩሪ አተር ድፍድፍ ከውጪ በማስገባት አገር ውስጥ አጣርተው ወይም ሙሉ ለሙሉ ያለቀለትን የምግብ ዘይት ምርት ለገበያ የሚያቀርቡ አስመጪዎች ብዛታቸው 2 ሺህ 945 እንደሆኑ የዋዜማ ምንጮች ይገልጻሉ።

በየዕለቱ እየጨመረ እንጂ ባለበት ረግቶ የማይቆየው የምግብ ዘይት ዋጋ ባሁኑ ወቅትባለ 5 ሊትሩ የታሸገ ዘይት በችርቻሮ መሸጫ ሱቆች ከ680 እስከ 700 ብር እየተሸጠ ይገኛል። በማከፋፈያ ማዕከላት ደረጃ ሲከፋፈል ደሞ ከ660 እስከ 680  ብር ይሸጣል። በሌላ በኩል በአምራቾች ተመርቶ ሳይታሸግ የሚሸጠው የሱፍ ዘይት በሊትር 140 ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ዋዜማ ባደረገችው የገበያ ዳሰሳ መረዳት ችላለች፡፡

የታሸገ የዘይት ምርት ዋጋን በሚመለከት 1 ሊትር 160 ብር፣ 2.7 ሊትር 273 ብር እንዲሁም 3 ሊትር በ395 ብር በገበያ ላይ እየተሸጡ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ የአንድ ወር የምግብ ዘይት ፍጆታ ግን 86 ሚሊዮን ሊትር እንደሆነ ይገመታል።

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የድፍድፍ የምግብ ዘይት ዋጋ ካለፈው ወር ጀምሮ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ ቢመጣም፣ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ግን ዋጋው የኅብረተሰቡን ገቢ ያገናዘበ እንዲሆን እና የአቅርቦት መቆራረጥን ለመቆጣጠር ዘይትን በሸማች ማኅበራት እና በመንደር ሱቆች ለማከፋፈል እንደሆነ  ሚንስትር ደዔታ ሀሰን ለዋዜማ ገልጸዋል። 

አምስተኛው ዙር የምግብ ዘይት ሥርጭት በቅርቡ እንደሚጀምር ሚንስትር ደዔታው የጠቀሱ ሲሆን፣ በዚሁ ዙር 10 ሚሊዮን 500 ሺህ ሊትር ዘይት ለኅብረተሰቡእንደሚሰራጭ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የዘይት ዋጋ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ ዓለም ዓቀፍ የነዳጅ ዋጋ መጨመር እና የኮንቴነር ኪራይ ዋጋ መናር በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ለምግብ ዘይት ዋጋ ማሻቀብ ዓለም ዓቀፍ ተጽዕኖዎችን እንደ ዋና ምክንያትነት የሚጠቅሱት ሀሰን፣ የሕገወጥ ደላሎች መበራከት፣ በየቦታው ያላግባብ የተቀመጡ ኬላዎች መብዛት እና ኬላዎቹ የሚጥሉት ቀረጥ የዘይት ዋጋ ጭማሪው በኅብረተሰቡ ላይ ጫና እንዲፈጥር እንዳደረጉ ይናገራሉ። ሀሰን አክለውም፣ ሚንስቴር መስሪያ ቤታችን እነዚህን ችግሮች በቀላሉ እና በፍጥነት መቅረፍ ባይችል እንኳ ለመቆጣጠር እየሰራ ነው ብለዋል።

ንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር ዘይት እና ዘይት ነክ ምርቶችን በሚመለከት በሦስት ዘርፎች ፍቃድ ይሰጣል። በዚህም መሠረት በላኪነት ስም ፍቃድ የተሰጣቸው እና የፍቃድ መለያ ቁጥራቸው 66131 የሆነ 549 የግል ድርጅቶች እና ግለሰቦች ይገኙበታል። ሆኖም ዋዜማ ከሚንስቴሩ ባገኘችው መረጃ እነዚህ ድርጅቶች እና ግለሰቦች እስካሁን ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አሳይተው አያውቁም።

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በመለያ ቁጥር 31114 የመዘገባቸው የምግብ ዘይት አምራችነት ፍቃድ የሰጣቸው እና በሥራ ላይ የሚገኙት ደሞ 860 ግለሰቦች እና ድርጅቶች ናቸው፡፡ እነዚህም ዘይትን ባለቸው አነስተኛ ቦታ በመጭመቅ እና በማምረት ለተጠቃሚዎች የሚያቀርቡ እንደሆኑ ለመረዳት ተችሏል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አየተመረቀው እና አገር ዓቀፍ የዘይት ፍጆታውን ከግማሽ በላይ ለመቅረፍ እንዲሁም በተመጣጣኝ ዋጋ ወደ ኅብረተሰቡ ለማቅረብ ቃል በመግባት የተጀመረው ዲ.ደብሊው ኢንዱስትሪያል የምግብ ዘይት ኮምፕሌክስ የሙከራ ሥርጭቱን ቢያካሂድም ሙሉ ለሙሉ ግን ምርቱን ገና ለገበያ አልቀረበም፡፡ 

የዲ ደብሊው ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ የገበያ ትስስር ክፍል መሪ የሆኑት አልአዛር አሕመድ ምርታቸው እስከዛሬ  ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ያልሆነበትን ምክንያት ለዋዜማ ሲያብራሩ፣ በዋናነት ካስቀመጧቸው ምክንያቶች ውስጥ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ መንግሥት ጥሎት በነበረው እገዳ ሳቢያ ዘይቱን ለማጣራት ከውጭ የሚገቡ ኬሚካሎች በወቅቱ አለመድረሳቸው፣ የጥሬ እቃ እጥረት እንዲሁም ከገበሬው እህሉን ለመሰብሰብ ብዙ ጊዜ መፍጀቱ ይገኙበታል። ሚንስትር ደዔታው አያይዘውም፣  “በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ግን ምርቶች ሙሉ ለሙሉ  ለተጠቃሚዎች መድረስ ይጀምራሉ” ብለዋል።

የዘይት ድፍድፍን ከተለያዩ አገራት አስመጥተው፣ አጣርተው እና አሽገው በማቅረብ በአገር ዓቀፍ ደረጃ ገበያ ላይ ተወዳደሪ ከሆኑት ድርጅቶች መካከል አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ድርጅት፣ የዘይት ምርት እና ዋጋው ከነዋሪው ገቢ ጋር አለመመጣጠኑ ከዓለም ዓቀፉ የዘይት ዋጋ ጭማሪ ጋር እንደሚያያዝ ለዋዜማ ተናግሯል።

ዋናዎቹ ችግሮች ግን በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው “የኢትጵያ ብር ዶላርን የመግዛት አቅሙ ማሽቆልቆሉ” እና “ባሳለፍነው ወር አስመጭ እና ላኪዎች ያላቸውን የውጪ አገር ገንዘብ እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ብሄራዊ ባንክ ያወጣው መመሪያ ነው” ሲሉ ለዋዜማ አብራርተዋል፡፡

ብሄራዊ ባንክ የውጪ ገንዘብ አጠቃቀምን በሚመለከት በተከታታይ ካወጣቸው መመሪዎች ውስጥ የመጨረሻው መመሪያ ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ የተላለፈው መመሪያ ነበር። በመመሪያው መሠረት ግለሰቡ ካለው 100 ፐርሰንት የውጭ ገንዘብ 70 በመቶውን ለብሄራዊ ባንክ ገቢ እንዲያደርግ የሚያዝ ሲሆን፣ 10 በመቶውን ተቀማጭ የሚሆንበት ፣ የተቀረው 20 በመቶው ብቻ የግለሰቡ እንዲሆን የሚያዝ ነው፡፡

ሚንስትር ደዔታ ሀሰን በበኩላቸው፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በሚመለከት የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት የዘይት ምርት ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች መንግሥት በተያዘው የካቲት ወር 250 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ፈቅዷል፤ ይህም ችግሩን ያቃልለዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን በማለት መንግሥት ያስቀመጠውን መፍትሄ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]