B. General Kinfe Dagnew former head of METEC

ዋዜማ ራዲዮ- በትራክተር ግዥ ለደረሰ የ319.4 ሚሊየን ብር ኪሳራ ክስ የተመሰረተባቸው ሜ/ጀ ክንፈ ዳኘው እና ሌሎች የሜቴክ ባለስልጣናት የአቃቤ ህግን ማስረጃ እንዲከላከሉ ተበየነ፡፡

የ57 አመቱ የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የቀድሞ ዋና ሀላፊ ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው እና ሌሎች የኮርፖሬሽኑ የቀድሞ ባለስልጣናት እንዲሁም ባለሀብቶች ህዳር 3 ቀን 2011 ዓም ለመጀመርያ ጊዜ ችሎት ቀርበው ጥር 21 ቀን 2011 ዓም የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ መመስረቱ ይታወቃል፡፡

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ በቀድሞ አጠራሩ 15ኛ ወንጀል ችሎት በአሁኑ ደግሞ 3ኛ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ጉዳያቸውን ሲከታተል ቆይቷል፡፡

የአቃቤ ህግ ክስም በጥቅሉ ለአዳማ እርሻ መሳሪያዎች ኢንዱስትሪ ያለጨረታ ከተገዙ ትራክተሮች ጋር በተያያዘ 319,475,287 ብር ኪሳራ ደርሷል በማለት የሚያስረዳ ነበር፡፡

ሰባት ክሶችን በውስጡ የያዘው መዝገቡ የብረታ ብረት እና ኢንጅነሪንግ የቀድሞ ሀላፊ ሜ/ጀ ክንፈ ዳኘውን ጨምሮ 5 የኮርፖሬሽኑ የቀድሞ ሀላፊዎች እና 3 በግል ስራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦችን ያካተተ ነው፡፡

እነዚህም የቀድሞ ዋና ዳይሬክተሩን ሳይጨምር ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዲ፣ የአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ማርኬቲንግ ሰፕላይ ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት ጉድያ፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ጎይቶም ከበደና በግል ሥራ ላይ ነበሩ የተባሉት አቶ ቸርነት ዳና፣ እሌኒ ብርሃንና አቶ ረመዳን ሙሳ ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ክደው እመነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ አቃቤ ህግ ማስረጃዎቹን እንዲያቀርብ እና ምስክሮቹን እንዲያሰማ ተፈቅዶለት ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ ከ20 በላይ ማስረጃዎችን ተመልክቶ እና እና 12 ምስክሮችን  ሰምቶ ከመረመረ በኋላም ሁሉም ተከሳሾች የአቃቤህግን ማስረጃ ይከላከሉ በይኗል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]