Biratu Yigezu , former CSS Head

ዋዜማ – የማዕከላዊ ስታስቲክስ አገልግሎት ቀድሞ ኤጀንሲ የነበረው ተቋም ዋና ዳይሬክተርና ሶስት ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ከኀላፊነታቸው መነሳታቸውን ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ስምታለች። 

የመስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር ቢራቱ ይገዙ አስቀድሞ ከሀላፊነታቸው ተነስተው የብልፅግና ፓርቲ አባል የሆኑትና በቅርቡ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገር ቤት የተመለሱት በከር ሻሌ (ዶ/ር) ተመድበዋል። 

በማስከተልም የስነ ህዝብና ቫይታል ስታስቲክስ ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር  አሳልፈው አበራ፣ የብሄራዊ ስታቲስቲስ ማስተባበሪያ ኦፕሬሽን ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አበራሽ ታሪኩ እና የስታስቲክስ ቆጠራዎችና ጥናቶች ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር አማረ ለገሰ ከነበሩበት የምክትል ዋና ዳይሬክተርነት ቦታ መነሳታቸውንና በሌላ የስራ መደብ ገና ያልተመደቡ መሆናቸውን አረጋግጠናል፡፡  

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ቀደም ሲል ከነበረበት የኤጀንሲ ደረጃ ወደ አገልግሎት ደረጃ  እንዲቀየር የተደረገ ሲሆን ተጠሪነቱም ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ቀደም ሲል ተጠሪነቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር (በወቅቱ የኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚ/ር) ነበር።

መስሪያ ቤቱ ሙያዊ ስራዎች ላይ ያተኮረ በመሆኑ ሹመኞች በዓመታት ሂደትና በስራቸው ስኬት በውስጥ ዕድገት ወደ ኀላፊነት የሚመጡበት ተቋም ነው። የበከር ሻሌ ሹመት በድርጅቱ ታሪክ ፖለቲከኛ ሲሾምለት የመጀመሪያው ነው።

አሁን የተነሱት ዋና ዳይሬክተሩና ሦስቱ ምክትል ዳይሬክተሮችም ከስታቲስቲሻንነት ደረጃ በሂደት ወደ ኀላፊነት ደረጃ የደረሱ ነበሩ ፡፡ ከዚህ በፊት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሳሚያ ዘካሪያም (አሁን አምባሳደር) ከስታቲስቲሻን ጀምረው የዘለቁ መሆናቸው ግለ ታሪካቸው ይገልጻል፡፡

ኀላፊዎቹ ስለተነሱበት ምክንያት የተገለፀላቸው ምክንያት የለም። ሌሎች የድርጅቱ ሰራተኞች ግን ተቋሙን በአዲስ አደረጃጀትና የሰው ኀይል ለመምራት ከመንግስት ወገን ፍላጎት በመኖሩ እንደሆነ ግምታቸውን ይናገራሉ። 

እግረ መንገዳቸውንም ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች መመራት ያለበትን ተቋም በፖለቲካ ተሿሚዎች ለመምራት መሞከር አደገኛ አዝማሚያ መሆኑናን መንግስት ልምድና ብቃት ያላቸውን ስዎች ይመድባል ብለው ተሰፋ እንደሚያደርጉ ነግረውናል። 

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ  የቤተሰብ ፍጆታና ወጪ፣ የዋጋ መረጃ፣ የግብርና፣ የቢዝነስ፣ የስነ ህዝብ ጤና፣ የካርቶግራፊ፣ የህዝብና ቤቶች ቆጠራንና ሌሎች ጥናቶችን  ሳይስናሳዊ በሆነ መንገድ የሚያከናውንና የሚያሰራጭ ተቋም ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ሳይንሳዊ የቆጠራ መስፈርቶችን ያሟላው የመጀመሪያው አገር አቀፍ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በግንቦት ወር 1976 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ ሁለተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ በጥቅምት ወር 1987 ዓ.ም፤ ሦስተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ በግንቦት ወር 1999 ዓ.ም የተካሄዱ ሲሆን አራተኛውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ በ2010 ዓ.ም ለማካሄድ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ጽ/ቤት  አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማከናወን ጫፍ ላይ ደርሶ ነበር፡፡  

ይሁንና በሀገሪቱ በነበረው የፀጥታ ችግርና በኮቪድ ሳቢያ ቆጠራው እየተራዘመ በየአስር አመቱ መደረግ የነበረበት ቆጠራ 15ኛ አመቱን መያዙ ይታወቃል፡፡

በ2010 ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ ቆጠራውን ለማከናወን ታቅዶ ከ150ሺህ በላይ ተንቀሳቃሽ ኮምፒውተሮች (አይፓድስ) ተገዝተው ወደ ሀገር ከገቡ በኃላ አስፈላጊው ሶፍትዌሮች ተጭኖባቸው ቆጠራውን ለማድረግ ዝግጀት ከተከናወነ በኃላ ቆጠራው ተራዝሟል። ተገዝተው የተቀመጡት ከ150ሺህ በላይ አይፓዶች ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተከፋፍለዋል፡፡

የማእከላዊ ስታትስቲክስ  በመላው ሀገሪቱ 25 ቅርንጫፎች ያሉትና በአንድ ማዕከል የሚመራና  ጥናትን መሰረት በማድረግ መረጃዎችን ለፖሊሲና እቅድ አውጪዎች፣ ለአለም አቀፍ ኤጀንሲዎች፣ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ተመራማሪዎች የሚያቀርብ ተቋም ነው፡፡  [ዋዜማ]