ዜማ ራዲዮ- ከሌሎች የገበያ ምርቶች በተለየ የሲሚንቶና የብረታብረት ምርት ለተገልጋዩ ለመድረስ የዋጋና የአቅርቦት ችግር ገጥሞታል። የሚቀጥሉት ስድስት ወራት በሀገሪቱ ግንባታ ማካሄድ እጅግ ፈታኝ እንደሚሆን ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ይጠቁማል። የገበያና የአቅርቦቱን ሁኔታ በተመለከተ በርካታ ባለድርሻዎችን አነጋግረናል። ገበያውንም ተዟዙረን ተመልክተናል። አንብቡት

ቀድሞውንም የተዳከመ አቅም

በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ካላቸው አጠቃላይ የማምረት አቅም 48 በመቶውን ብቻ ነው እያመረቱ የሚገኙት፡፡

ዋዜማ የሲሚንቶን የገበያ ሁኔታ ለማወቅ በቅርቡ በአዲስ አበባ ተዟዙራ ባደረገችው የገበያ ዳሰሳ፣ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከ930 እስከ 1 ሺህ 100 ብር ድረስ ዋጋ እየተሸጠ እንደሚገኝ ተረድታለች። ሆኖም በስሚንቶ ገበያ ላይ የተፈጠረውን ቀውስ ይበልጥ እንዲባባስ ያደረገው ግን፣ በገበያው ላይ የሚታየው ከፍተኛ የምርት እጥረት እንደሆነ የንግድ ሱቅ ባለቤቶች እና ተጠቃሚዎች ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በስሚንቶ አከፋፋይነት እና አቅራቢነት ግንባር ቀደም በሆኑት ጎጃም በረንዳ እና መገናኛ አካባቢ በሚገኙ መደብሮች ውስጥ፣ ሲሚንቶ አከፋፋይ ነጋዴዎች እንደተናገሩት ከመጋቢት የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ከፍተኛ የምርት እጥረት አለ። ዋዜማም ባደረገችው ዳሰሳ የስሚንቶ መደብሮቻቸው ባዶ መሆናቸውን አረጋግጣለች፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት 20 ሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች መካከል፣ በአሁኑ ወቅት በገበያው ውስጥ ያሉት ስሚንቶዎች የዳንጎቴ ሲሚንቶ እና ኢትዮ ሴሜንት ብቻ ናቸው፡፡ ዳንጎቴ ከ100 ኩንታል በላይ ለሚገዙ አንድን ኩንታል ከ930 ብር ጀምሮ የሚሸጥ ሲሆን፣ ኢትዮ ሲሜንት ደሞ እስከ 950 ብር ድረስ ይሸጣል። ሁለቱም የሲሚንቶ ምርቶች በችርቻሮ ዋጋ ሲሸጡ ግን፣ ዋጋቸው ከ980 እስከ 1 ሺህ ብር ድረስ እንደሚደርስ ዋዜማ ተመልክታለች።

በሲሚንቶ የገበያ ትስስር እና የችርቻሮ ዋጋ በቀጥታ የሚመለከተው የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር ሚንስቴር ድዔታ ሀሰን ሞዐሊም  መስሪያ ቤታቸው ፍትሃዊ የስሚንቶ ምርት ሥርጭት እንዲኖር እና ተገልጋዮች ያለ ምንም አድልዖ ምርቱን እንዲያገኙ ጥረት እያደረገ መሆኑን እና ሁለት ጊዜ  ከስሚንቶ አምራቾች እና አከፋፋዮች ጋር እንደተወያየ ተናግረዋል። 

ከብዙ ውይይቶች በኋላ የስሚንቶ ዋጋ በነጻ ገበያ እንዲመራ የተወሰነ መሆኑን የገለጡት ሀሰን፣ ሆኖም በሕዝቡ ላይ አላስፈላጊ ጫና በሚፈጠርበት በማንኛውም ሰዓት ግን መስሪያ ቤታችን ጣልቃ ገብቶ ገበያውን የማረጋጋት ሥልጣን አለው ብለዋል።

ዓለማቀፍ የአቅርቦት ቀውስ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ ባወጣው አዋጅ ቁጥር 12፣ 62/14 መሠረት የሲሚንቶ ምርትን በሚመለከት ከአምራቾች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው መንግሥታዊ ተቋማት አንዱ የማዕድን ሚንስቴር ነው። 

ዋዜማ በጉዳዩ ዙሪያ ሚንስቴሩን ጠይቃለች። ፋብሪካዎች ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ስሚንቶ እንዳያመርቱ ያደረጓቸው ግንባር ቀደም ምክንያቶች የኤሌክትሪክ ኃይል በበቂ ሁኔታ አለማግኘታቸው እና የድንጋይ ከሠል እጥረት እንደሆነ ይገልጻል። 

ኢትዮጵያ ለስሚንቶ ምርት መሠረታዊ ግብዓት የሆነውን ድንጋይ ከሠል ከውጭ ለማስገባት በዓመት 300 ሚሊዮን ዶላር እንደምታወጣ የገለፀው መስሪያ ቤቱ፣ ማዕድን ሚንስቴር የአገሪቱን ተፈጥሮ ሃብት ተጠቅመው አገር ውስጥ ምርቱን ለሚያመርቱ አካላት ማምረቻ ቦታ ሰጥቷል። 

ማዕድን ሚንስቴር ጥር 5፤ 2014 ዓ፣ም በ6 ቢሊዮን ብር ካፒታል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከ8 ወር እስከ 1 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ድንጋይ ከሰል እናመርታለን ካሉ  ስምንት ኩባንያዎች ጋር ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል፡፡ 

ዋዜማ ስለ ችግሩ ያነጋገረቻቸው በስሚንቶ እጥረት ሳቢያ የጀመሩትን ሕንጻ ለመጨረስ የተቸገሩት አቶ አማኑዔል ግርማ፣  “ሕንጻው ተገንብቶ የማገኘውን ትረፍ ማሰብ ካቆምኩ ቆይቻለው። የግንባታ እቃዎች ዋጋ ንረት ፍጹም ተስፋ አስቆራጭ በመሆኑ፣ ሥራ ለማቆም ወስኛለሁ። አሁን የጨነቀኝ የቀጠርኳቸው የቀን ሠራተኞች ዕጣ ፋንታ ነው” በማለት የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ ንረት በቀን ጉልበታቸው የሚያድሩ ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ምን ያህል እየጎዳ እንደሆነ ያብራራሉ።

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአንድ  ሲሚንቶ ፋብሪካ የገበያ ክፍል ሃላፊ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ድንጋይ ከሰል የምታስመጣው ከዩክሬን እንደነበር ገልጠው፣ ሆኖም ግን አሁን ዩክሬን ጦርነት ላይ በመሆኗ ፋብሪካቸው ቀደም ሲል የነበሩትን ግብዓቶች በሙሉ አሟጦ ጨርሶ ምርት ካቆመ አንድ ወር እንዳለፈው ተናግረዋል።

ብርቅየው ብረት 

ሌላኛው መሠረታዊ የግንባታ ግብዓት ብረት ክፍተኛ የዋጋ ንረት እንዳሳየ ተመልክተናል።

ዋዜማ ከብረት አከፋፋዮች እና ቸርቻሪዎች ባገኘችው መረጃ፣ አንድ የአገር ውስጥ ፌሮ ከመጋቢት መግቢያ ጀምሮ በአማካይ ከ100 እስከ 300 ብር ጭማሪ አሳይቷል።

የአገር ውስጥ ፌሮብርየቱርክ ፌሮብር
ባለ 8560.00ባለ 8711
ባለ 10870ባለ 101,590
ባለ 121,240ባለ 121,875
ባለ 141,750ባለ 142,175
ባለ 162,240ባለ 162,475
ባለ 203,600ባለ 204,425

ኢትዮጵያ ውስጥ ለበር ስራ የሚውሉት የብረት ዓይነቶች ኤልቲዜድ ባለ 38 እና ባለ 28 ሲሆኑ፣ እያንዳንዳቸው ባለቸው ውፍረት ልክ ዋጋቸው ይለያያል። ዋዜማ ባደረገችው የገበያ ዳሰሳ ኤልቲዜድ በመጋቢት መግቢያ የነበረው ዋጋ፤

  • ባለ 38 በ0.8ሚሊ ሜትር ውፍረት – ከ500- 550 ብር ይሸጥ የነበረው 1200 ብር፣
  • ባለ 38 በ1ሚሊ ሜትር ውፍረት– 800 ብር ይሸጥ የነበረው 1250 ብር
  • ባለ 38 በ1.2 ሚሊ ሜትር ውፍረት – 900 ብር ይሸጥ የነበረው ከ1500- 1600 ብር
  • ባለ 28 በ0.8 ሚሊ ሜትር ውፍረት በፊት ከነበረው ዋጋ 300 ብር ጭማሪ በማሳየት 800 ብር ሲሸጥ በተመሳሳይ ዋጋ ጭማሪ በ 1.2 ሚሊ ሜትር ውፍረት 1ሺህ 100 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡

ሌላኛው ክፍተኛ የገበያ ፍላጎት ያለው ላሜራ ነው።1 ሺህ 200 ብር ሲሸጥ የነበረው ልሙጡ ላሜራ ከእጥፍ በላይ ጨምሮ 4 ሺህ 500 ብር ሲሸጥ፣ ባለ 1.4 ሚ.ሜ ውፍረት ያለው ሸካራ ላሜራ ደሞ ከ1 ሺህ ብር ተነስቶ 5 ሺህ 100 ብር ገብቷል። ሸካራ ላሜራ በ2 ሚ.ሜ ውፍረት ከ1 ሺህ 400 እስከ 1 ሺህ 600 ብር ይሸጥ ነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን 6 ሺህ ብር እየተሸጠ ነው፡፡

ሚስማር ከ5 ቁጥር እስከ 12 ቁጥር ድረስ በኪሎ 480 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ዘገባ በተሰራበት ወቅት ግን 900 ብር በኪሎ እየተሸጠ እንደሆነ መረዳት ተችሏል።

የቤት ክዳን ቆርቆሮ በአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ለገበያ ሲቀርብ ካለፈው 1 ወር ጀምሮ ከ180 እስከ 520 ብር ሲሸጥ እንደቆየ እና በየቀኑ የአንድ መቶ ብር ጭማሪ እያሳየ እንደሆነ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የቆርቆሮ መደብር ባለቤቶች ተናግረዋል።

ቆርቆሮ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዕለት ድረስ የሚከተለው የገበያ ዋጋ ነበረው፤

ባለ 28- 1 ሺህ 400 ብር

ባለ 30- 1 ሺህ 200 ብር

ባለ 32 – 975 ብር

ባለ 35-  420 ብር

ኢትዮጵያ ብረትን ለማምረት የሚያስችላትን ጥሬ እቃ ሙሉ ለሙሉ ከዩክሬን እንደምታስገባ ዋዜማ ከማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ እና ኢንዱስትሪ ምርምር እና ልማት ማዕከል ጋር ባደረገችው ቆይታ መረዳት የቻለች ሲሆን፣ ከዩክሬኑ ጦርነት በፊትም የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ትልቅ ችግር እንደነበር የማዕከሉ ኮምንኬሽን ሃላፊ ፊጤ በቀለ ተናግረዋል፡፡

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት ከአጠቃላይ የሀገሪቱ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የምንዛሪም የማምረት አቅማችንንም በእጅጉ የተዳከመ እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ የዘርፉ ባለሀብቶች። 

በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ እና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ አምራች ድርጅቶች ያላቸውን አቅም ተጠቅመው ቢያመርቱ፣ በዓመት 11 ሚሊዮን ቶን ብረትን ማምረት እንደሚችሉ ይገመታል። ይህም ወደ ገንዘብ ሲቀየር 385 ቢሊዮን ብር ነው። 

ዘርፉ ያለበትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ በዘርፉ የተሠማሩ ድርጅቶች ርስበርስ እንዲተጋገዙ የማስተሳሰር ሥር እየተሠራ  የገለጡት ፊጤ፣ በጥሬ እቃ ምክንያት ምርታማታነቸው ለቀነሰባቸው አምራቾች ደሞ አንዱን ጥሬ እቃ ለአንዱ ግብዓት አድርገው እንዲጠቀሙ መስመሮች ዘርግተናል በማለት ገልጸዋል።

ከ15 ዓመት በላይ እድሜን ያስቆጠረው ዋሊያ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ቱርክ ከሚገኝ ድርጅት ጋር በጥምረት እየሰራ ሲሆን፣ ድርጅቱ ጥሬ እቃዎችን በዋናነት ከዩክሬን በመግዛት ያቀርብለታል። 

በዓለማቀፍ ገበያ የብረት እና የማጓጓዣ ዋጋ በእጥፍ እንደጨመረ እና ጥሬ ዕቃ ለማቅረብ ቃል የገቡ ኩባንያዎች ውል እየሰረዙ እንደሆነ የዋልያ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ባደግ ከበደ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

በዩክሬኑ ጦርነት ሳቢያ ቱቦላሬ (አር.ኤች.ኤስ) የተባለው ጥቅል ብረት ባለፉት ሦስት ሳምንታት ብቻ በዓለማቀፍ ገበያ ዋጋው 40 በመቶ ጨምሯል።አጠቃላይ በአገር ውስጥ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋገት እና ለመቆጣጠር መንግሥት ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት የተውጣጣ አንድ ግብረ ኃይል አቋቁሟል። [ዋዜማ ራዲዮ]