Amare Aregawi and Mimi Sibhatu
Amare Aregawi and Mimi Sibhatu

(ዋዜማ ራዲዮ) -ጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባው አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ “የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት” (ፕሬስ ካውንስል) መመስረቱ ይፋ ተደርጓል። አመራሩን የተረከቡት ወገኖች መንግስት በካውንስሉ ምስረታ ጣልቃ ባለመግባቱ የተሰማቸውን ደስታም ገልጸዋል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደሚጠቁሙት ደግሞ ጉዳዩ ከብዙዎች በምስጢር እንዲያዝ ተደርጎ ምስረታው ዕውን የሆነው የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ “ከተመረጡ” የሚዲያ ባለቤቶች ጋር በጥድፊያ ባከናወኑት ድርጅታዊ ሥራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

[ዳንኤል ድርሻ ያዘጋጀውን መዝገቡ ሀይሉ በድምፅ ያቀርበዋል]

በሊቀ መንበርነት የተመረጡት አቶ አማረ አረጋዊ “ከአስር አመት በፊት መንግስት አንድ የሚዲያ ሕግ አውጥቶ ነበር። አንዱ አንቀጽ የሚዲያ ካውንስል ይቋቋም የሚል ነበር። በጊዜው የሚዲያ ሰዎች ተሰብስበን እባክህን መንግስት አንተ አታቋቁም ራሳችን እናቋቁማለን በማለት ይህን አንቀጽ ሰርዝልን አልን። መንግስትም ጥያቄያችንን ተቀብሎ፣ እናንተ የምታቋቁሙ ከሆነ ሰርዤዋለሁ አለ። ባለፉት አስር አመታት በሄድነው ሂደት ይህቺ የመንግስት ቃል ተከብራ ዛሬ ለማቋቋም በቃን። በዚህ አጋጣሚም መንግስትን እናመሰግናለን” ሲሉም ተደምጠዋል።
በካውንስሉ ምስረታ ያልተደሰቱ ጥቂት የማይባሉና በመንግስት ደጋፊነት የሚታሙ ጋዜጠኞች፣ የኦንላይን ሚዲያ ባለቤቶች፣ ብሎገሮችና “የጋዜጠኛ ማሕበራት” ተወካዮች “ካውንስሉ የሚዲያ ባለቤቶች እንጂ የፕሬስ ካውንስል አይደለም” በማለት ሌላ የፕሬስ ካውንስል ለማቋቋም እንደሚገደዱ ከመናገር አልፈው በዚሁ ጉዳይ ላይ ለመምከር የስብሰባ ጥሪ አሰራጭተዋል፡፡ ጉዳዩን ከረፈደ የደረሱበት የሚመስሉት እነኚሁ የጋዜጠኛ ማሕበራትና መሪዎቻቸው “ባለድርሻ አካላት በቤሉለበት የአመራር ምርጫው ቀደም ብሎ በተሰራ የቡድን ስራ እንዳይፈፀም” የሚል መማጸኛ በማቅረባቸውም ተሰምቷል።

በሠንደቅ ጋዜጣ በታተመ አንድ ጽሑፍም ላይ “አሁን በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ የተደረገውን የስልጣን ሽግሽግ ተገን በማድረግ የሀገሪቷን መገናኛ ብዙሃን ለመቆጣጠር የሚደረግ ሩጫ የሚያስከፍለው ዋጋ ምትክ አልባ ነው” የሚል ማስፈራሪያ መሰል ቃል እስከ ማቅረብ መደረሱም በአቶ ጌታቸው ረዳ መሪነት የተከወነውን የፕሬስ ካውንስሉን ድብቅ አመሰራረት የሚያጋልጥ ፍንጭ ኾኖም ተወስዷል ፡፡

በምርጫው ማሳረጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት አቶ ጌታቸው ረዳ ከፕሬስ ካውንስሉ ተጠቃሚው መንግስት ጭምር መሆኑን በመግለጽ ለካውንስሉ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል፡፡

የፕሬስ ነጻነት መብት ተደንግጓል በሚባልባቸውም አገራት “የፕሬስ ካውንስል” መመስረት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በተለመደውም አስራር ፕሬስ ካውንስል ከየትኛውም ወገን በሚዲያ ላይ የሚቀርቡ አቤቱታና ስሞታዎችን በመፈተሽ መፍትሔ ለማፈላለግ የሚሰራ ነው። ይህ ማለት ግን ጋዜጠኛው ወይም ዋና አዘጋጁ በፍርድ ቤት እንዲቀጣ የማድረግ ሥልጣን ይኖረዋል ማለት አይደለም። ካውንስሉ ከዚህም አልፎ መገናኛ ብዙሃንን የተመለከተ ጥናትና ምርምር ከማድረግ አንስቶ ሚዲያን የሚመለከቱ የፖሊሲ ጉዳዮችን ፈትሾ ለፓርላማ እስከ ማቅረብ ሊጓዝም ይችላል፡፡

በሌሎች አገራት እንደሚታየው ከኾነ፤ የፕሬስ ካውንስል አባላት የሚኾኑት የሕግ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች፣ የዲጂታል ሕትመትና ኢንተርኔት ጸሐፊዎች፣ ብሎገሮችና የድረ ገጽ ሚዲያ አባላት ጭምር ናቸው፡፡ እንደ ዴንማርክ ያሉ አንዳንድ አገራት በአብዛኛው ለካውንስሉ አመራርነት የሕግ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞችን ሲመርጡ፣ አውስትራሊያን የመሳሰሉቱ ደግሞ ከ24 የፕሬስ ካውንስል አባላት አስር የሚደርሱት ፈጽሞ ከሚዲያ ጋር ግንኙነት የሌላቸው በጎ ፈቃደኞች ናቸው።
በኢትዮጵያ ፕሬስ ካውንስልን የመመስረት እንቅሰቃሴ የተጀመረው ሰሞኑን እየተለጸ እንዳለው ከአራት ዓመት በፊት አልነበረም፡፡ የፕሬስ ካውንስል ምስረታ ጥንስስ የተጣለው በ1990ዎቹ መጀመሪያ በእነ አቶ ክፍሌ ሙላት፣ በፈቃዱ ሞረዳ፣ ዘገየ ኃይሌ እና ሲሳይ አጌና ይመራ በነበረው የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማሕበር (ኢነጋማ) አማካይነት ነበር፡፡ ማኅበሩ ለፕሬስ ካውንስል መሰረት የሚሆን ነው ያለውን የሥነ ምግባር ደንብ አዘጋጅቶ ለአባላቱ ከማሰራጨት ባሻገር፣ እንደነ ዶክተር ኃይሉ አርአያ በመሳሰሉ ምሁራን አስተባባሪነት የፕሬስ ካውንስል መማክርትን የመመስረት እንቅስቃሴ ተጀምሮ እንደነበር ይታወቃል። ይሕን መሰሉ እንቅስቃሴ ግን ብዙም ሳይሔድ በነበረበት ተጽዕኖ ምክንያት ከዳር ሳይደርስ ቀርቷል።
ከዚህ በኋላ ነበር የያኔው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር በረከት ስምኦን ባልተጠበቀም ባልተገመተም ኹኔታ ቀደም ሲል የነጻው ፕሬስ ወዳጅ እንደነበሩ የሚነገርላቸውንና የሕግ ባለሙያውን አቶ ሽመልስ ከማልን ከጎናቸው አሰልፈው የፕሬስ ካውንስል ለማቋቋም የመጡት። አቶ ሽመልስ ከሕግ ባለሞያነታቸው በተጨማሪ ኒሻን የምትባል አንድ የግል ጋዜጣ ያዘጋጁም ነበር።

አቶ በረከት በ1995 ዓም ይሕን ካውንስል የማቋቋም ጉዳይ ለማስተዋወቅ በግዮን ሆቴል ስብሰባ አድርገው ነበር። ማስታወቂያ ሚኒስቴር በጠራው በዚሁ ስብሰባ ላይ ድምጻቸው እንዳይሰማ ክልከላ የተጣለባቸው የኢነጋማ ፕሬዚዳንት ክፍሌ ሙላት ተቃውሟቸውን ካሰሙ በኋላ ሁሉም የማሕበሩ አባላት ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸው የቀሰሰቀሰው ዓለም አቀፍ ተቃውሞ መንግስት የፕሬስ ካውንስሉን ሐሳብ እንዲያዘገይ እንዳስገደደውም ይነገራል፡፡

የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ማሕበር በመንግስት ጫና ምክንያት እንቅስቃሴው ከተገታና በምርጫ 97 ማግሥት ነጻ ጋዜጦች በመንግስት ከተዘጉም በኋላ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለቤቶች ምክር ቤቱን ለመመስረት ተንቀሳቅሰው ነበር፡፡ ይኹንና ለምስረታው ወጪዎች መሸፈኛ ይሆን ዘንድ ከዩኔስኮ ተገኝቷል የተባለ ገንዘብ ጉዳይ የፈጠረው ውዝግብና በአደራጆቹ አቶ አማረ አረጋዊ እና ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ መሐከል የነበረው የተለያየ አቋም በአስተባባሪዎቹ መካከል ከነበሩ ሌሎች አለመግባባቶች ጋር ተደምሮ የተፈለገውን የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ለመመስረት ሳይቻል ጉዳዩ ለዓመታት እንዲዘገይ ኾኗል፡፡

ሰሞኑን በነበረው ምስረታ ላይ ቅሬታ እንዳለባችው ከሚነገርላቸው ሚዲያዎች መካክል የአውራምባ ታይምስ ድረ ገጽ አዘጋጅ ተቃውሞውን በገለጸበት ጽሁፉ አሁንም ለካውንስሉ ድጋፍ ከዩኤንዲፒ ገንዘብ መገኘቱን ጠቁሞ ነበር። ይኹንና የፎርቹን ባለቤት አቶ ታምራት ወልደ ጊዮርጊስ በሰጠው ምላሽ ከየትኛውም ወገን ምንም አይነት የገንዘብ ድጋፍ አልተገኘም ሲል ጉዳዩን አስተባብሏል፡፡
ጉዳዩን የተከታተሉ ምንጮች እንዳስረዱት እና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “ወቅታዊ ፕሮግራም” ላይ እንደታየውም ስብሰባውን በመስራችነት የተካፈሉት አስራ ዘጠኝ ተወካዮች ብቻ ነበሩ። ተወካዮቹም የተውጣጡት ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ)፣ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ማስ ሚዲያ ኤጀንሲ፣ ከኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማኅበር፣ ከፎርቹን ጋዜጣ፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ከሸገር ኤፍኤም ሬዲዮ፣ ከዛሚ ኤፍኤም ሬዲዮ፣ ከካፒታል ጋዜጣ፣ ከሪፖርተር ጋዜጣ፣ ከናሽናል ኮንስትራክሽን መጽሔት፣ ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ጋዜጠኞች ማኅበር፣ ከዋቢ አሳታሚዎች ማኅበር፣ ከሀ እስከ ፐ መጽሔት፣ ከኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር፣ ከኢትዮ ቻናል ጋዜጣ፣ ከቁም ነገር መጽሔት፣ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ እና ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተወከሉ ነበሩ፡፡
የስብሰባው ተሳታፊዎች የነበሩትን ሚዲያዎች ማንነትና የፕሬስ ካውንስሉን አወቃቀር በመመልከትም የካውንስሉን ነጻነት የት ድረስ እንደኾነ የሚገምቱም ብዙዎች ናችው። በአስመራጭነት የተሰየሙት የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር ተወካይ ጋዜጠኛ ዮናስ ተሾመ፣ የዛሚ ኤፍኤም ሬዲዮ ወኪል ወ/ሮ ሚሚ ስብሃቱና የፎርቹን ባለቤት ጋዜጠኛ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ ነበሩ። ለጉዳዩ ቅርበት ያለቸው ምንጮች እንደሚጠቁሙትም ለረጅም ጊዜ ካውንስሉን ሲያደራጁ የቆዩት አቶ ታምራት እና ወይዘሮ ሚሚ አስመራጭ እንዲኾኑ የተደረጉበት ምክንያትም በምርጫው መወዳደር እንዳይችሉና የካውንስሉንም መሪነት ለሌሎች አሳልፈው እንዲሰጡ ታስቦ ነው የሚል ግምታቸውንም ይገልጻሉ፡፡

ከአስራ ዘጠኙ ድምጽ ሠጪዎች መካከል ለካውንስሉ አመራርነት የተጠቆሙት ሠባት ሰዎች ነበሩ። ከነዚህ መካከል ሁለቱ ማለትም የፕሬስ ኤጀንሲ እና የሴት ጋዜጠኞች ማኅበር ተወካዮች ሲቀሩ ሌሎቹ አምስቱ ለአመራርነት ተመርጠዋል፡፡ እነኚህም ተመራጮች መዓዛ ብሩ (ከሸገር ኤፍኤም ሬዲዮ)፣ መሠረት አታላይ (ከኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር)፣ አማረ አረጋዊ (ከሪፖርተር ጋዜጣ)፣ አብርሃም ገብረመድኅን (ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን)ና ታምራት ኃይሉ (ከቁም ነገር መጽሔት) ናቸው፡፡

ቀድሞውንም ቢኾን እንዲህ ባሉ የመደራጀት ጅማሬዎች ላይ እጁን ማስገባቱ አይቀርም የሚባለው ኢሕአዴግ፤ የመንግስት የፕሮፓጋንዳ መስሪያ ቤቶች ከኾኑት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ የመጡ ኃላፊዎች በአስመራጭነትም በተመራጭነትም ትልቅ ሚና የተጫወቱበት ይህ የፕሬስ ካውንስል ማንነት ከመንግስት ተጽዕኖ ነፃ ሊኾን እንደማይችል ለብዙ ታዛቢዎች የማያጠራጥር ነው፡፡

የስፖርት ጋዜጠኞችን ወክሏል የተባለው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከፍተኛ ሹም ዮናስ ተሾመ ለፕሬስ ካውንስሉ አስመራጭ መሆኑ፣ ሌላኛው የኢብኮ አመራር አብርሃም ገብረመድኅን የካውንስሉ ዋና ጸሐፊ ሆኖ መመረጡ ና የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ ተወካይ አቶ ሡልጣን መሐመድ ኑር ለአመራሩ በዕጩነት መቅረባቸው እዚህ ላይ የሚጠቀስ ነው።