ዋዜማ ራዲዮ – የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት “ሊቀመንበር” ማሙሸት አማረ በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ተይዞ ታሰረ። አቶ ማሙሸት የተያዘው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በገጠመው የጤና እክል ሳቢያ በሰሜን ሸዋ አካባቢ ሸንኮራ ዮሀንስ የተባለ የእምነት ቦታ ፀበል እየተጠመቀ በነበረበት ጊዜ ነው። አስታማሚ ወንድሙም በፀጥታ ሀይሎች ተይዞ ከተወሰደ በኋላ ሁለቱም ያሉበት ቦታ አልታወቀም።

አቶ ማሙሸት በድርጅቱ አባላት በመሪነት ይመረጥ እንጂ በአቶ አበባው መሀሪ የሚመራው የፓርቲው አንጃ በመንግስት ይሁንታ የፓርቲውን ፅህፈት ቤትና ንብረቶች በመቆጣጠር በምርጫ ቦርድ እውቅና ወስዷል።
አቶ ማሙሸት ባለፉት አመታት በተደጋጋሚ እስርና እንግልት የደረሰበት ሲሆን ከአንድ አመት በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ከእስር ሲለቀቅ ጀምሮ በገጠመው የጤና እክል ወደ ህክምናና ፀበል መሄዱን ወዳጆቹ ይናገራሉ።