ዋዜማ ራዲዮ- የጦር መሳርያ በመያዝ በሚሊንየም አዳራሽ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ጥቃት ሊያደርስ ነበር የተባለው ሀየሎም ብርሀኔ የሟች ሜ/ጀ ገዛኢ አበራ ጠባቂ ነኝ በማለት በፍርድ ቤት ተከራከረ፡፡


የፌደራል ፖሊስ ከአማራ ክልል “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” ጋር እና በአዲስ አበባ በከፍተኛ የጦር ሰራዊቱ መሪ ላይ ከተፈፀመው ግድያ ጋር በተያያዘ ጠረጠርኳቸው ያላቸውን 6 ግለሰቦች ሰኔ 19 በፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት አቅርቧል፡፡


ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የነበረው ሀየሎም ብርሀኔ የተባለው ግለሰብ ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓም በሚሊንየም አዳራሽ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ለቀድሞ የመከላከያ አባል ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ የአስክሬን ሽኝት በሚደረግበት ወቅት 1 ክላሽንኮፍ ጠመንጃ እና 60 መሰል ጥይቶችን በመያዝ በሽኝት ስነስርዓቱ ላይ በተገኙት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ ጥቃት ሊያደርስ ሲል ነው የተያዘው በማለት ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ተጠርጣሪው ሀየሎም “የሟች ሜ/ጀ ገዛኢ አበራ የግል ጠባቂ ነኝ፣ የገባሁት እንደሚባለው ጥቃት ለማድረስ አይደልም ፤ መሳርያውም የጥበቃ አካል ስለሆንኩ የተሰጠኝ ነው” ሲል ለችሎቱ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡

እሱ ተጠርጥሮ በቀረበበት በዚህ መዝገብ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት ናቸው የተባሉት አቶ መርከቡ ሀይሌ ፣ አቶ ስንታየው ቸኮል እና አቶ ጌድዮን ወንደሰን ተካተዋል፡፡ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ማስተዋል አረጋ እና ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ ተጠርጣሪዎች ተብለው ቀርበዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከሀየሎም ውጪ ባሉት አምስት ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ ያቀረበው አቤቱታ በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር አምባቸው መኮንን ፣ በአማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ እና በክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ ላይ በተፈፀመው ግድያ እና “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” እጃቸው አለበት የሚል ነው፡፡

በተጨማሪም በአዲስ አበባ የተገደሉት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ላይ የተፈፀመውን ድርጊት ከሌሎች ግብረዓበሮቻቸው ጋር በመተባበር እና በመቀናጀት የወንጀል ድርጊቱ ላይ ተሳትፈዋል በማለት ፖሊስ ለችሎት ገልፅዋል፡፡

በጦር መሳርያ በመታገዝ ለፈፀሙት የሽብር ወንጀልም ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለማሰባሰብ በሽብር ህጉ መሰረት 28 ተጨማሪ ቀን እንዲሰጠው ችሎቱን ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡
በአማራ ክልል የተሞከረውን “መፈንቅለ መንግስት” በማቀነባበር እና በመምራት የተጠረጠሩት ብ/ጄ አሳምነው ፅጌ የተገደሉ እና ስርዓተ ቀብራቸው ትናንት በትውልድ ከተማቸው ላሊበላ የተፈፀመ ሲሆን ከእሳቸው ጋር ተባብረዋል በሚል ተጠርጥረው በክልሉ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ቁጥር ከ180 እንደሚበልጥ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

ማስታወሻ፤

ይህ ዜና ሰኔ 21 ቀን ከቀኑ 5 30 ላይ አነስተኛ የፊደልና የአረፍተ ነገር ማስተካከያ ተደርጎበታል።