• ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት ማክበሪያዋ ጃንሜዳን በራሷ ለማልማት ዲዛይን እያዘጋጀች ነው
PHOTO-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በግንባታ ላይ ያለው መስቀል አደባባይ ለአዲሱ ዓመት የደመራ በዓል ዝግጁ እንደሚሆን መንግስት ቃል ገብቶ ነበር። ይሁንና የግንባታ ስራው በታሰበው ጊዜ አልተጠናቀቀም። በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውይይት አድርገዋል። የበዓል አከባበሩንም በተመለከተ አማራጭ ዕቅድ አውጥተዋል። የዋዜማ ሪፖርተር ጉዳዩን ተከታትሎ ይህን ዘገባ አዘጋጅቷል።


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሚያዝያ ወር አጋማሽ ላይ “የመስቀል አደባባይ መዘጋጃ ቤት” ፕሮጀክት ነድፎ መስቀል አደባባይን አፍርሶ መስራት ጀምሯል። ይህ ፕሮጀክት በ2.5 ቢሊየን ብር በጀት ሲሲሲሲ በተባለው የቻይና ስራ ተቋራጭ በድንገት ሲጀመር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ” በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት : የሳይንስና ባህል ድርጅት :ዩኔስኮ :ያስመዘገብኩትና በእየ አመቱ የመስቀል ዳመራ የሚከበርበትን ቦታ ሳያሳውቀኝ አፍርሶ መስራት መጀመሩ ተገቢ አይደለም ” በሚል ቅሬታ ማንሳቷ ይታወሳል።


ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዚሁ ቅሬታዋም የመስቀል አደባባይን የጥንተ ባለቤትነት ጥያቄዋን በመነሻነት አቅርባለች። የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅሬታ ተከትሎ በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የነበሩት ታከለ ኡማ የላኩት ልኡክ ቤተ ክርስቲያኒቱን ይቅርታ ጠይቆ የፕሮጀክቱ ሂደት ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ በክትትል : በአደባባዩ ዲዛይን እንድትሳተፍም ፈቃደኝነቱን አሳይቷል።


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅቱ ፕሮጀክቱ ሲጀመር ለመስቀል ደመራ በአል ይደርሳል ብሎ ነበር። ዋዜማ ሬዲዮም የመስቀል ደመራ በአል ፈርሶ እየተሰራ ባለው የመስቀል አደባባይ ስፍራ እንዴት ይከበር ይሆን ? ስትል ጠይቃለች። በዚሁ ጉዳይም ላይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሀላፊ መጋቤ ካህናት ሀይለስላሴ ዘማርያም ጋር የዋዜማ ሬድዮ ዘጋቢ ቆይታ አድርጓል።


እንደ መስቀል ደመራ አይነት ግዙፍ ስፍራ ያላቸው በአላት ሲከበሩ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በኩል በአሉን የሚያስተባብረው የካህናት አስተዳደር መምሪያ ነው ያሉን መጋቤ ካህናት ሀይለስላሴ ; በ2013 አ.ም የመስቀል ዳመራ በአል አከባበር ዙርያ በዚሁ ሳምንት ማክሰኞ እለት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የቤተ ክህነቱ ልኡክ ውይይት ማድረጉን ገልጸውልናል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል በምክትል ከንቲባ ማእረግ የመንግስታዊ አገልግሎቶች ክላስተር አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ በተገኙበት ነው ውይይቱ የተካሄደው። የቤተ ክርስቲያኒቱ ወኪሎች በዚሁ ስብሰባ ላይ ለከተማው አስተዳደር ሀላፊዎች ሰፊ ጥያቄ አንስተውላቸው ምላሽ እንደተሰጠባቸም ስምተናል።


 ዋናው ጥያቄ የነበረውም የከተማ አስተዳደሩ ሚያዝያ ወር ላይ ቃል እንደገባው የመስቀል አደባባዩ መስከረም 16 ቀን 2013 አ.ም የመስቀል ዳመራን ለማክበር ዝግጁ ነው ? ። የቤተ ክርስቲያኑን ልኡክ መርተው ከአስተዳደሩ ጋር የተወያዩት መጋቤ ካህናት ሀይለስላሴ ለዚህ ጥያቄያችን ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘነው ምላሽ ; የመስቀል ዳመራ መትከያ ቦታው መስከረም 1 2013 አ.ም ድረስ ዝግጁ ይሆናል የሚል ነው ብለውናል። ከታጠረው አጥር ውስጥ የሚገኘው የደመራ መትከያው ቦታም አጥሩ ተነስቶ ለበአሉ ጥቅም ላይ ይውላል እንደተባሉም ነግረውናል።


የመስቀል ዳመራ በፊት የሚተከልበት ቦታ ላይ አሁንም እንደሚተከል የገለጹት መጋቤ ካህናት ሀይለስላሴ የቤተ ክርስቲያኗ ተወካዮች በስፍራው ባደረግነው ጉብኝትም የደመራ መትከያ ቦታው ዝግጁ ሊሆን እንደሚችል እምነት ይዘናል ብለውናል። ሆኖም የመስቀል ደመራ በአል አከባበርን እጅግ ድምቀት የሚሰጠውና የእምነቱ ተከታዮች ጧፍ አብርተው በአሉን የሚከታተሉበት በኤግዝቢሽን ማእከል በኩል ያለው ስፍራ እንደማይደርስ የተረጋገጠ መሆኑን ; ይህም ብቻ ሳይሆን በአደባባዩ ግራና ቀኝ ያሉት ቦታዎችም ለበአሉ ዝግጁ አይደሉም ብለውናል።


የከተማ አስተዳደሩ እንዳለው ሳይሆን አደባባዩ በቀደመ አቋሙ ለበአሉ ዝግጁ እንደማይሆን በአሉ ሲከበር የበአሉ ታዳሚያን የሚቆሙበት ስፍራ ሌላ መልክ እንዲኖረው እንደታሰበ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሀላፊው ለዋዜማ ራዲዮ አስረድተዋል። የመስቀል ዳመራ በአል አከባበር መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ለከተማ አስተዳደሩ ተሰጥቶታል ።


እንደ መጋቤ ከህናት ሀይለስላሴ ዘማርያም ከሆነም አሁን አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት አንጻር በአሉ እንዴት ተጣጥሞ ይከበር የሚለው ነው።ለዚህም በበአሉ ላይ የሚያገለግሉ የካህናት : የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች : ታዳሚዎችና እንግዶች ቁጥር ከዚህ ቀደም ከነበረው እንዲቀንስ የማድረግ ሀሳብ ያለ ሲሆን ይህንንም ቤተ ክርስቲያኗ ትወስንበታለች።


በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በኢትዮጵያ መኖሩ መታወቁን ተከትሎ የቫረይሱን ስርጭት ለመቀነስ ይረዳል በሚል ፒያሳ የሚገኘውን የአትክልት ተራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለጥምቀት ማክበሪያ ወደ ምትጠቀምበት ጃን ሜዳ መውሰዱ አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ ስንብቶ ነበር። ይህን የከተማ አስተዳደሩን እርምጃም በወቅቱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ከእውቅናዬ ውጭ የተደረገ ነው ብላ ተቃውማው እንደነበርም የሚታወስ ነው።


የጃን ሜዳስ ጉዳይ ከምን ደረሰ?  ያልናቸው የካህናት አስተዳደር መምሪያ ሀላፊ መጋቤ ካህናት ሀይለስላሴ ዘማርያም : የከተማ አስተዳደሩ ጃን ሜዳን ለአትክልት ተራ ጥቅም ላይ የሚውለው ለአምስት ወራት ነው ብሎ የገለጸልን ቢሆንም አምስት ወራት አልፈውም የተለወጠ ነገር የለም ። በዚህና በጥምቀት በአል አከባበር ዙርያም ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር ውይይት እንደሚደረግ ነው የነገሩን።


በዘላቂነት ግን ጃን ሜዳን ለማልማትና በራሷ ጥቅም ላይ ለማዋል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በራሷ መሀንዲሶች ዲዛይን እያሰራች እንደሆነ ተገልጾልናል። [ዋዜማ ራዲዮ]