Meles bio bookዋዜማ ራዲዮ-ቼምበር ማተሚያ ቤት የታተመና የጊዮርጊስ ቢራ ስፖንሰር ያደረገው የመለስ ግለታሪክን የሚያወሳ መጽሐፍ ዛሬ ረፋዱ ላይ ለአንባቢ ቀርቧል፡፡ የመጽሐፉ ዋጋ አንድ መቶ ብር ሲሆን የገጹ ብዛት ግን 189 ብቻ ነው፡፡ ደራሲው ደግሞ መምህር መኮንን አብረሃ ይባላሉ፡፡

‹‹መለስ ዜናዊ እና የ3ሺ ዓመት የቁጭት ዘመን›› የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ መጽሐፍ ለመለስ 4ኛ ሙት ዓመት እንዲደርስ ታስቦ የተዘጋጀ ይሁን እንዲሁ የቀን መገጣጠም የታወቀ ነገር የለም፡፡ መጽሐፉ ከአድልዎ የፀዳና ገለልተኛ ሥራ ስለመሆኑ ደራሲው አበክረው የገለጹ ሲሆን ታሪክ ሲጻፍ ከማንኛውም ዉሸትና ስሜት የጸዳ መሆን እንዳለበትም ደጋግመው መክረዋል፡፡ ኾኖም ደራሲው ‹‹ትእምት››ን የመሰሉ የትግራይ ድርጅቶች ሕትመቱን ስፖንሰር ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ክፉኛ ማዘናቸውን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

‹‹መጀመርያ መጽሐፉን ለመጻፍ እቅድ ሳወጣ መለስን ሕዝብ ስለሚወደው መጽሐፉን ጽፌ ከጨረስኩ በኋላ ለማሳተም ብዙ ድርጅቶች በተለይም ትእምዕት ይተባበሩኛል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡›› የሚሉት ደራሲው ይህ ሳይሆን መቅረቱ እንዳሳዘናቸው ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹የትእምዕት ዋነኛ አላማ ሲቋቋም መተዳደሪያ ደንቡ የትግራይ ሕዝብ ፀጋዎች የሆኑትን…በቀጣይነት እንዲዳብሩ ማድረግ ቢሆንም ወደ ሜጋ እግሬ እስኪነቃ ተመላልሻለሁ፣ ሁሉም ጨካኞች ናቸው›› ሲሉ ጽፈዋል፡፡ ‹‹ለመለስ እንኳንስ መጽሐፍ ሐውልት የሚሰራለት ሰው ነው፣ (የነዚህ) ተቋማት መልስ ግን ሁሌም አልተፈቀደም የሚል ነው፡፡›› ካሉ በኋላ የትእምዕት ድርጅቶች አቶ ገብሩ አስራት በመጽሐፋቸው እንደገለፁት ‹‹ሙያዊ ብቃት ያለውና በሥነምግባር የታነፀ አመራር ያላገኙ›› ኾነው አግኝቻቸዋለሁ ብለዋል፡፡ ደራሲው አያይዘው እንደገለፁት ‹‹በ17 የጦርነት ዓመታት የማቀቀው የትግራይ ወጣት፣ ወላጆቹ ሲሞቱ ጉድጓድ ቆፋሪ የሬሳ ሳጥን ተሸካሚ አጥቶ የቆየው የትግራይ ሕዝብ (ነጻ ያወጣ)፣ አሁን (ደግሞ) 17 አመት ታግሎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሕይወቱን ለሰዋው መለስ ‹‹ትእምት›› (የርሱን ታሪክ የያዘች) አንዲት መጽሐፍ ስፖንሰር ለማድረግ ባለመቻሉ በጣም የሚያሳዝን ክስተት ነው፡፡›› ሲሉም ኢንዶውመንቱን ክፉኛ ወርፈውታል፡፡

መጽሐፉ 16 ምዕራፎች ያሉት ሲሆን 40 የተለያዩ ንዑሰ ጉዳዮችን አካቶ ይዟል፡፡ በመጽሐፉ ከተካተቱት ሰነዶች መሐል አቶ መለስ ለኢሳያስ አፈወርቂ በቀጥታ የጻፏቸው ደብዳቤዎች ይገኙበታል፡፡  በምዕራፍ ስድስት ደግሞ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ምን ያህል ንግግር አዋቂና አንደበተ ርቱዕ እንደነበሩ ለማሳየት የሚረዱ ዘገባዎችና ከቢቢሲ ሃርድ ቶክ ወደ አማርኛ የተመለሱ  ቃለመጠይቆች ተካተውበታል፡፡

ደራሲው በመጽሐፋቸው የተለያዩ ምዕራፎች መለስ ላይ በተለያየ ጊዜ ነቀፌታ የሰነዘሩ ግለሰቦችን እያነሱ ያብጠለጠሉ ሲሆን ትችት ከሰነዘሩባቸው ሰዎች መካከልም ፕሮፌሰር መስፍን ይገኙበታል፡፡ እሱ ‹‹ግንቦታ 29፣ 1997- የትግራይ ሕዝብ ሲመርጥ እንዲሁ ከፋብሪካ መደዳውን ተፈብርኮ እንደሚወጣ ሳሙና ነው‹‹ ሲል የትግራይን ሕዝብ አንቋሸዋል፡፡ ሲሉም ፕሮፌሰሩን ይከሷቸዋል፡፡

የታሪክ ፀሐፊው የመምህር መኮንን አብረሃ መጽሐፉ የመለስ ዜና መዋዕልና ግለ ታሪክ መሆኑን ቢጠቀስም ከተለመደው የግለታሪክ አጻጻፍ ወጣ ባለ መልኩ በብዙ ዉዳሴዎችና እንጉርጉሮዎች የታጀበና ስሜታዊነት የሚታይበት ነው፡፡ በመጽሐፉ መለስን የሚያወሱ በርከት ያሉ ግጥሞች በመጨረሻዎቹ ገጾች ተካተውበታል፡፡ ከዚህም ባሻገር የመለስን ሞት ተከትሎ የሐዘን መግለጫ የላኩ የዓለም መሪዎች ስም  በተራ ቁጥር ተዘርዝሯል፡፡ መጽሐፉ የመለስን ሞት ተከትሎ አርቲስቶችና ታዋቂ ሰዎች ሐዘናቸውን እንዴት ገልጸው እንደነበረ የሚያብራራ ሲሆን የአንዳንዶቹ ንግግር በተለይም በመስቀል አደባባይ የቀረቡ የስንብት ንግግሮች ታትመዉበታል፡፡

ደራሲው በመጽሐፉ መግቢያ ላይ መጽሐፉን ለመጻፍ የተነሱበትን ዓላማ እንዲህ በማለትም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹የ3ሺ ዓመት የቁጭት ዘመን›› የሚለው መጽሐፌን የጀመርኩት መጻፍ ከሚገባኝ ጊዜ በላይ እጅግ ዘግይቼ ነው፡፡ (እንዲያውም) መጀመርያ ይህን መጽሐፍ ለመጻፍ ሐሳቡ አልነበረኝም፤ ምክንያቱም 1ኛ የመለስን የምጡቅ ስብእና ያለው መሪ ለመግለጽ አቅሙ ይኖረኛል ወይ ብዬ አልተማመንኩም ነበር›› ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ‹‹የአክለሊ ሀብተወልድን ባዮግራፊ ጽፈሃል፣ የመለስን ታዲያ ለምን አትጽፍም እያሉ ሲጠይቁኝ…የመለስን ስብዕና በሚገልጽ መልኩ ለመጻፍ ታጥቄ ተነሳሁ፡፡›› ብለዋል፡፡

ይህ የመለስን ታሪክ የሚያወሳው መጽሐፍ ጠጠር ያሉና በመረጃ ያልተደገፉ ድምዳሜዎቸም አላጡትም፡፡ ለምሳሌ በገጽ 72 ላይ የቀረበ አንድ የመለስ ዜናዊ ምስል ሥር የሚከተለው ዐረፍተ ነገር ተጽፎበታል፡፡

‹‹መለስ ሦስቴ መብላት በአጭር ጊዜ ያሳካ መሪ››፡፡

ፀሐፊው ይህ ጽሑፍ ከሰፈረበት ገጽ ላይ ጨምረው እንዳስቀመጡት.. ‹‹ሙሉ በሙሉ ድህነት ጠፋ ባይባልም መለስ…የኢትዮጵያን ሕዝብ ከስንዴ ልመና አውጥቷል›› ሲሉ ይሟገታሉ፡፡

የመለስን ሞት ተከትሎ የተፈጠረውን ስሜት ባወሱበት ክፍል ደግሞ አዲስ ጉዳይ መጽሔትን ዋቢ አድርገው ደራሲው የሚከተለውን ጽፈዋል፡፡

‹‹የመለስ ሞት በተሰማበት ጊዜ በብዙ አካባቢዎች ደረትን መድቃትን ዘልሎ በመፈጥፈጥ ራስን እየጎዱ ማዘን በመለስ ሞት ምክንያት አገርሽቷል››

ይህ የመለስ ዜና መዋዕል ለማዘጋጀት ደራሲው ለአንድ አመት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጥናትና ምርምር ተቋምና የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብት ኤጅንሲ እንደተመላለሱና አያሌ ሰነዶችን እንዳገላበጡም ተናግረዋል፡፡

‹‹የአክሊሉ ሃብተወልድ መጽሐፍ ስጽፍ የዉጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰራተኞች በምሰራው ስራ ስለተደሰቱ የግል ማኅደራቸውን ሳይቀር በማቅረብ በሄድኩ ቁጥር በግቢያቸው ባሉት ክበቦች ዉስጥ ብዙ ጊዜ ምሳ ይጋብዙኝ ነበር፤ ስለዚህ ተልእኮዮን በደስታ ተወጣሁ፡፡ …የመለስን ባዮርግራፊ ስጽፍ ግን እንደ አክሊሉ ሃብተወልድ ሳይሆን ማተሪያል በማግኘት በኩል ችገሮች ነበሩብኝ›› ብለዋል፡፡

‹‹ሚያዚያ 22፣1983 የአዲስ አበባ ሕዝብ መለስን በቴሌቪዥን ሲመለከት እሰይ ተመስገን ፈጣሪ፣ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይድረሰው የደህና ሰው ፊት አየን›› ብሎ ነበር የሚሉት ደራሲው በ97 ግን የዶክተር ነገደ ጎበዜን መጽሐፍ እንደመመሪያ በመጠቀም ሥልጣን ከገዢው ፓርቲ ለመንጠቅ ተነሳ ይላሉ፡፡ ያኔ ‹‹መለስ ሕዝብ ኢህአዴግን ይደግፋል የሚል ሐሳብ ስለነበረው ደስ የሚል ነግግር አድርጎ ነበር፤ በሒደት ግን ቅንጅት የሸረበው ብዙ ጉድ ነበር፤ ሰልፉም የጋጠወጦች ነበር›› ሲሉም 10 ዓመታት መለስ ብለው የአዲስ አበባ ሕዝብን ወቅሰዋል፡፡ ‹‹አጋጣሚ ሆኖ ነውጡ በመለስ ብርታት ተረጋጋ እንጂ በኃይል ቤተመንግሥት ለመያዝ አስበው ነበር፣ ነገር ግን በዕለቱ ዝናብ ስለዘነበ ቅንጅት ያሰበውን ለውጥ ሳይሳካለት ቀረ›› ሲሉም አውስተዋል፡፡

ስለ መጽሐፉ አስተያየት ከሰጡ ግለሰቦች መካከል አቶ ይትባረክ ግደይ ደራሲውን መምህር መኮንን አብረሃን ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ ሆነው ወገንተኝነት ሳያጠቃቸው ይህን የመለስን ታሪክ መጻፋቸው ካደነቁ በኋላ በግላቸው መለስ ወደዚች ምድር የመጡትና የተፈጠሩትም ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮችን እንዲፈጽሙ ከፈጣሪ የተላኩ መስለው ይታዩኛል ሲሉ የራሳቸውን ሐሳብ በመጽሐፉ አስፍረዋል፡፡ አንደኛው ታሪክ የራሳቸው ንዑሳን ጎሳዎችን ከያሉበት ለማንሳት፣ 2ኛ አባይን ለመገደብ፣ 3ኛ አዲስ አበባ ከተማን መሐል ለመሐል ሰንጥቆ የሚያልፍ ባቡር ለማስገንባት…ሲሉ ይዘረዝሩና መለስ ዜናዊ ከላይ የተላኩ ‹‹ታላቅ ሐዋሪያ›› ብለው ሐሳባቸውን ይቋጫሉ፡፡

የመለስ ዜናዊ የልጅነት ጊዜ በተዳሰሰበት የመጽሐፉ ክፍል ገጽ 4 ላይ ደግሞ የሚከተለው ሰፍሮ ይገኛል፡፡

‹‹መለስ ገና በልጅነቱ የ4ኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ጊዜ የእንግሊዝኛ አስተማሪው Sneeze በሚለው ቃል አረፍተ ነገር እንዲሰሩ ክፍሉን ሲጠይቅ መለስ እጁን በማውጣት When Queen Elizabeth Sneeses, the whole of Europe weeps ብሎ መልሷል፡፡ የ4ኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ የዚህ አይነት አረፍተ ነገር መስራት ማለት ምን ያህል ጎበዝ ተማሪ እንደነበር ያመለክታል፡፡ሲሉ ደራሲው ለመለስ እድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹መለስ ዜናዊ እና የሦስት ሺህ ዓመት የቁጭት ዘመን›› ደራሲ መምህር መኮንን ትውልድ አገራቸው አድዋ ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት መምሪያ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቅጥርና ድልደላ ዋና ክፍል ኃላፊ ከዚያም በመቀጠል የዩኒቨርስቲው የሰዉ ኃይልና ጠቅላላ አገልግሎት መምሪያ ሥራ አስኪያጅ በመሆን ያገለገሉ ሰው ናቸው፡፡