img_1764

ባሕርዳርና ጎንደር እስከ 650 ብር ይሸጣል

ዋዜማ ራዲዮ- የአቶ ኤርሚያስ ለገሠ ሁለተኛ ሥራ የኾነው የመለስ ልቃቂት የተሰኘው መጽሐፍ በአገር ቤት ገበያው ደርቶለታል፡፡ ለአንድ ቅጂ ከ450 እስከ 580 ብር ይጠየቅበታል፡፡ ይህ ታዲያ በአዲስ አበባና አካባቢዋ ብቻ የሚሸጥበት ዋጋ ነው ተብሏል፡፡ ወደ ባሕርዳር፣ ጎንደርና ሌሎች ከተሞች ሲሻገር ዋጋው ከዚህም በላይ ይንራል፡፡ በባህርዳር እንዲሁም ጎንደር ከተሞች ከቀናት በፊት በ650 ብር ሲሸጥ ነበር ተብሏል፡፡ ኾኖም በርካታ አንባቢዎች መጽሐፉን በቅብብሎሽ መልክ ከወዳጅ እንዳገኙት ነው የሚናገሩት፡፡

መጽሐፉ በአገር ቤት በሚገኝ አንድ ማተሚያ ቤት እንደታተመና ጊዮርጊስ አካባቢ በሚገኝ አንድ “አርከበ ሱቅ” እንደሚከፋፈል በወሬ ደረጃ በስፋት ከመሰማቱ ዉጭ ትክክለኛ አሳታሚው፣ የአታሚው ማንነትም ኾነ ዋና አከፋፋዩ በውል አይታወቁም፡፡

ከቀናት በፊት ስቴዲየም ዙርያ ምሳ ሰዓት ላይ መጽሐፉን እንዲያመጣልኝ የጠየቅኩት አዝዋሪ ዋጋው ከ550 ብር ምንም እንደማይቀንስና ከተስማማሁ ብቻ ከሰዎች ዘንድ በፍጥነት እንደሚያመጣልኝ ገልጾልኛል፡፡ የት እንደሚከፋፈል ለጠየቁት ጥያቄ እሱን እንደማያውቅ ገልጾልኛል፡፡ መጽሐፉን ሲሸጡ የተያዙ ወይም የታሰሩ ሰዎች ካሉ ያውቅ እንደሆነ ጠይቄውም ‹‹አላውቅም›› የሚል አጭር ምላሽ ሰጥቶኛል፡፡

ካዛንቺስ “ኮፊዴይስ” አካባቢ የሚገኝ አዝዋሪ በበኩሉ “እኔ ደንበኛዬ ላልሆነ ሰው አልሸጥም”፡፡ መጽሐፍ የሚገዙኝ የራሴ ደንበኞች አሉኝ፡፡ እነሱ ከጠየቁኝ አመጣላቸዋለሁ፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት ለምሳሌ አራት አራት መቶ ብር ሽጨላቸዋለሁ›› ይላል፡፡

መጽሐፉ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተጠቅልሎ እንደሚያዝም አጫውቶኛል፡፡

አራት ኪሎና አምስት ኪሎ የፓትሪያርኩ ጽሕፈት ቤትና መኖርያ ደጅ ላይ መጻሕፍትን ዘርግተው ከሚሸጡ በርካታ አዝዋሪዎች ሁለቱ መጽሐፉ እንደሌላቸው ሲናገሩ ማለዳ ካፌ መግቢያ ላይ የሚገኝ ሌላ አዝዋሪ በዋጋ ከተስማማሁ ብቻ ለነገ ጠዋት ሊያገኝልኝ እንደሚችል ነግሮኛል፡፡ ቁርጥ ዋጋው 580 ብር እንደሆነም ነግሮኛል፡፡

ጊዮርጊስ አካባቢ ሳይሆን እንዳልቀረ የሚገመተው ዋናው አከፋፋይ መጽሐፉን በ180 ብር ለሚያውቃቸውና ለሚያምናቸው አዝዋሪዎች ብቻ ባለፉት ሳምንታት ሲያከፋፍል እንደነበር የተነገረ ሲሆን አሁን ግን መጽሐፉን ከምንጩ ማግኘት አዳጋች ነው ተብሏል፡፡ ምናልባት በድጋሚ ከታተመ ዋጋው እስከ 3 መቶ ብር ሊሆን ይችላል ብለው ይገምታሉ፣ አንዳንድ አዝዋሪዎች፡፡ መጀመርያ የወጣ ሰሞን እስከ 250 ብርም ሸጠነዋል ብለውኛል አንዳንዶች፡፡ አሁን ግን አልቋል፡፡ ወይም እጥረት ተፈጥሯል፡፡

መጽሐፉ ምን ያህል ቅጂ ታትሞ እንደተሸጠ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

አሁን ገበያ ላይ የሚገኘው መጽሐፍ የስካን ቅጂ አለመሆኑ ሲታይና ኦሪጅናል ሕትመት መምሰሉ ምናልባትም ብዙዎች እንደሚገምቱት በሕገወጥ መንገድ የተባዛ ላይሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬን አሳድሯል፡፡ ይልቁንም ዋናው የጽሑፍ ቅጂ (ሶፍት ኮፒ) ደራሲው ሙሉ ፍቃዱን ሰጥቶ በወኪሉ አማካኝነት በአገር ቤት ማተሚያ ቤት በመደበኛ ሁኔታ በወረቀት እንደተባዛ የሚያስጠረጥርሩ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የሕትመት ቅጂው በግለሰቦች በድፍረት እንደገና በትየባ ተለቅሞ በድጋሚ እንዲጻፍ ከተደረገ በኋላ በድብቅ ወደ ማተሚያ ቤት ተልኮ ሊሆን ይችላል፡፡

ይህን ሁሉ ጥርጣሬ የሚያጭረው አሁን በስርጭት ላይ የሚገኙ ቅጂዎች የጥራት ደረጃ ከፍ ማለቱ ነው፡፡

መጽሐፉ ዉጭ ከታተመው ዋናው ቅጂ ጋር መጠነኛ የይዘት ለውጦች ተደርገውለታል መባሉም መላምቱን ለእውነት የቀረበ ያደርገዋል፡፡ በዋናው ቅጂ የነበሩ ሁለት ገጾች ሆን ተብለው እንዲቀነሱ ሆነዋል ይላሉ ሁለቱንም ቅጂዎች አስተያይተናቸዋል የሚሉ ሰዎች፡፡ የትኞቹ ገጾች እንደተቀነሱና ለምን እንደተቀነሱ ሲጠየቁ ግን ምላሽ አይሰጡም፡፡

568 ገጾች እንዳሉት የተነገረው የአቶ ኤርሚያስ መጽሐፍ በይበልጥ ስለ ማኅበረ ረድኤት ትግራይ (ማረት)፣  ስለ ትግራይ መልሶ ማቋቋሚ ድርጅት (ኤፈርት) ያልተሰሙ ሚስጢሮችን ይዟል መባሉ ከወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት ጋር ተዳምሮ ነው ከፍ ያለ የገበያ ፍላጎት መፍጠር የቻለው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ ከመሆኑ ጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎ የፖለቲካ ይዘት ያላቸው መጻሕፍትን ሲያዘዋውሩ የነበሩ በርካታ መጻሕፍት አዝዋሪዎች መታሰራቸውና በፖሊሶች እንግልትና ወከባ እንደደረሰባቸው መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ (በዋዜማ ሪፖርተር)