• የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ  ከብሄራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ጋር መግባባት አቅቷቸው የቴክኒክ ቡድኑ አባላት ላይ ዘለፋ በመሰንዘራቸው ስብሰባው ረግጠው የወጡ ሙያተኞች መኖራቸው ተሰምቷል።
  •      ዛሬም በሱዳን ካርቱም የሶስትዮሹ ስብሰባ ይቀጥላል ። ዝርዝሩን ያንብቡት
Water Irrigation and Energy minister Sileshi Bekele- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሀ አሞላልና አስተዳደር ላይ የኢትዮጵያ : ግብጽና ሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ; ከኢትዮጵያ ደግሞ የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ተጨምረው በኢትዮጵያ አቆጣጠር በጥቅምት ወር መጨረሻ በዋሽንግተን ዲሲ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚያም ከአሜሪካው የግምጃ ቤት ሀላፊ ስቴፈን ሙኒሽን እና ከአለም ባንክ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል። ይህም ችግር ገጥሞት የነበረውን የህዳሴውን ግድብ ውሀ አሞላልና አስተዳደር ውይይት ለማስቀጠል እንደረዳ ተነግሯል።

ከዋሽንግተኑ የመጀመርያ ስብሰባ በሁዋላም የሶስቱ ሀገራት የውሀ ሚኒስተሮችና የቴክኒክ ሙያተኞች አንዴ በአዲስ አበባ ሌላ ጊዜ ደግሞ በግብጽ ካይሮ በዚሁ የግድቡ ውሀ አሞላልና አስተዳደር ላይ ተወያይተዋል።በሁለቱም ስብሰባዎች ላይ አሜሪካና አለም ባንክ ተገኝተዋል። አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ስብሰባ ላይ ግብጾች ከዚህ ቀደም ያሳዩት የነበረውን ግትርነት ቀንሰው የታዩ ሲሆን ቀጥሎ በካይሮ በተደረገው ስብሰባ ግን የቀድሞ አቋማቸውን በመድገም የኢትዮጵያ ተወካዮችን የቅኝ ግዛት ስምምነትን እንዲቀበሉ ጭምር ለማግባባት ሲቃጣቸው ታይቷል።


ከካይሮው ስብሰባ በሁዋላ የሶስቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሮችና ሙያተኞች እንደገና በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የዛሬ አስራ አምስት ቀን አካባቢ ለድጋሜ ውይይት በሄዱበት ወቅት የግድቡን ውሃ አሞላልና አስተዳደር የሚያካሄድበትን ህግ ስለማውጣት ተስማምተዋል።

ሀገራቱ በስብሰባቸው ማጠናቀቂያ ላይ ባወጡት መግለጫ ጭምር የዓባይ ውሀ ተፈጥሯዊ ፍሰቱ በድርቅ ወይም በሌላ ምክን ያት ቢዛባ ግብፅ ማግኘት ይገባኛል የምትለውን የውሀ መጠን እንዳይነካ ሽፋን የሚሰጥ መመሪያ ይዘጋጃል የሚል ያስገቡት ነጥብ አሁን የኢትዮጵያን ተደራዳሪዎችና ባለሙያዎች እያወዛገበ ነው።

የኢትዮጵያ ወኪሎች በዚህ ላይ ተስማምተው መምጣታቸው እጅግ ስህተት መሆኑን ባለሙያዎች ለዋዜማ አስረድተዋል። ኢትዮጵያ በአባይ ውሀ ላይ ከታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ጋር ስትወያይ ተፈጥሯዊ ፍሰት የሚባል ነገር ለውይይት እንኳ መቀበል እንደሌለባት ነው አቋም ተይዞ የነበረው። ምክንያቱም ተፈጥሯዊ ፍሰት ሲባል አንድ ወንዝ ላይ ምንም አይነት ሌላ መሰረተ ልማት የለም ማለት ሲሆን ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በአባይ ተፋሰስ ላይ ከህዳሴ ግድብ በፊት ጣና በለስ ፣ ፍንጭ ፣ ጨርጨርና ቆጋ አይነት ግድቦችን ስለሰራች በተፋሰሱ ላይ ለሚደረጉ ስምምነቶች ተፈጥሯዊ ፍሰት የሚባል ነገር ሊመጣ አይችልም።

ተፈጥሯዊ ፍሰትን ወደፊት ለሚመጣ ድርቅ ማካካሻ መመሪያ ለማውጣት ይረዳል ማለት እስካሁን በተፋሰሱ ላይ ኢትዮጵያ ለሰራቻቸው መሰረተ ልማቶች እውቅናን ከመንፈግ ባለፈ ከዚህ በሁዋላ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ሌላ መሰረተ ልማትን እንዳታስብ የማድረግ አላማም ያለው ነው ይላሉ ድርድሩን በቅርቡ የሚከታተሉ ሙያተኞች።

ይህም ብቻ ሳይሆን የግብጹ የውሀ ሚኒስትር መሀመድ አብደል አቲ ባለፈው አመት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ተቋርጦ የነበረውን ውይይት ካይሮ እንዲቀጥል ትፈልጋለች ብለው ባመጡት ሰነድ ላይ ፣ ኢትዮጵያ የአባይ ውሀ ተፈጥሯዊ ፍሰቱን ሳይለቅ በየአመቱ 40 ቢሊየን ሜትር ኩዩብ ወሀ ትልቀቅልን የሚል ነበረበት። በዚህ ጊዜ ታድያ “መጠኑንም አንስማማም” ፣ “ተፈጥሯዊ ፍሰት የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም” በሚል ምላሽ ለግብጽ ተሰጥቷት ነበር።

በኢትዮጵያ በኩል ተፈጥሯዊ ፍሰት የሚባል ነገር የሶስትዮሽ የስምምነት መግለጫ ላይ እንዴት እንዲገባ ተፈቀደ የሚለው ግልጽ አይደለም። የኢትዮጵያና የግብጽ የድርቅ ትርጉም የተለያየ በሆነበት መልኩ ይህ የጋራ መግለጫ መውጣቱ ተገቢ አለመሆኑንም የዋዜማ ምንጮች ተናግረዋል። ግብጾች የአባይ ውሀ ከዓመታዊ አማካይ ፍሰቱ በታች ከሆነ ድርቅ ስለሆነ ኢትዮጵያ የወንዙን ተፈጥሯዊ ፍሰት ሳትነካ ውሀ ትልቀቅ ነው የሚሉት። ይህ ማለት የአባይ ወንዝ አማካይ አመታዊ ፍሰቱ 49 ቢሊየን ሜትር ኩብ ሲሆን ፣ ከዚህ ዝቅ ካለ ኢትዮጵያ በግድቧ ውሀ ሳትይዝ ውሀውን ወደ ግብፅ እንድትለቅ ይጠበቅባታል።

እነዚህ ነገሮች የኢትዮጵያን ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዱ እና ውሀውን የመጠቀም መብቷንም የሚጋፋ ነው።ስለዚህ ስምምነት ከተደረገ እንኳ መደረግ ያለበት ግድብ ውስጥ በገባ ውሀ ብቻ ነው መሆን የሚገባው ይላሉ ምንጮቻችን።

ከዋሽንግተኑ ስብሰባ በሁዋላ የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩን ዶር ስለሺ በቀለን ጨምሮ ኢትዮጵያን የወከሉ የውሀ ሙያተኞች አንዴ ሱዳን ስለፈለገች ተስማምተናል ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተፈጥሯዊ ፍሰት ለይ አልተነጋገርንም ነበር ግብጾች ናቸው መግለጫ ላይ ያስገቡት ብለው ሊያስተባብሉ ሞክረው ነበር።

ሆኖም የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ የሶስትዮሹ ስምምነት በዚህ መልኩ ሊቀጥል እንደማይገባ በኢትዮጵያ የቴክኒክ ሰዎች ተደጋጋሚ ጉትጎታ የቀረበላቸው ሲሆን ድርድሩም እንዲቆም ተመክረዋል። ነገር ግን ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ሰምታለች። እንደውም እሮብ በውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስቴር በዚሁ ጉዳይ ባተኮረ ስብሰባ ላይ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ ወይይቱ እየተመራበት ያለው መንገድ ለኢትዮጵያ አዋጭ አይደለም ይቁም በሚል ምክር የሰጧቸው የቴክኒክ ሰዎችን እንደዘለፏቸው ሰምተናል። ስብሰባውንም አቋርጠው የወጡ ነበሩ።

ሶስተኛ ወገን

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮች ውይይት ሌላ አካል በታዛቢነትም ሆነ በአደራዳሪነት እንደማይገባ ሲናገሩ ነበር። ይህን ለግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በሩስያ ሶቺ ሲገናኙም ነግረዋቸው እንደተስማሙ ገልጸው ነበር። የግድቡ ጉዳይ ለቴክኒክ ሰዎች ብቻ እንዲተውም ስምምነት ነበር። የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለም ኢትዮጵያ ታዛቢም ሆነ አደራዳሪ እንደማትቀበል በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ መንግስት ለሶስቱም ሀገራት ጥሪን አቅርቦ የኢትዮጵያ ልኡክ ከመሄዱ ሁለት ቀን አስቀድሞ በተደረገ ምክክር በሶስትዮሽ የህዳሴ ግድብ ውይይት ላይ ምንም አይነት የሌላ አካል ጣልቃ ገብነት ቢጠየቅ ላለመቀበልም ስምምነት ነበር። ታዲያ በመሪ የተወሰነ ውሳኔ እያለ ፣ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ኢትዮጵያን ወክለው የሄዱ አካላት የአለም ባንክና የአሜሪካን ታዛቢነት መቀበላቸው እስካሁን ግልጽ አይደለም።

አንድ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ የዋዜማ ምንጭ እንዳሉት ፣ ብዙዎች አሜሪካና አለም ባንክ አደራዳሪ ሳይሆኑ ታዛቢ በመሆናቸው ችግር የለውም ብለው ያስባሉ፤ ነገር ግን ታዛቢ በውይይቱ መጨረሻ ለተወከለበት አካል ሪፖርት ማቅረቡ ስለማይቀር አለም ባንክና አሜሪካ ኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ውስጥ የማይጨምር ስራ ላለመስራታየው መተማመኛ የለም ብለውናል።

አለም ባንክ ደግሞ በየጊዜው የቀጠራቸው ግብጻውያን ምክትል ፕሬዝዳንቶች ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ልማት እንዳትሰራ ገንዘብ እንድትከለከል ፖሊሲ ያወጡ ናቸው። የአባይ ተፋሰስ የላይኛው ሀገራት ከታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ፍቃድ ውጭ ወንዙ ላይ ልማት እንስራ ቢሉ አለም ባንክ ገንዘብ እንዳይሰጥ የሚከለክል ህግ የወጣው ግብጻዊው እስማኤል ሳራጊልተን የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ መሆኑ ይታወሳል።

አሁንም ጊዜው አልረፈደም የሚሉት የዋዜማ ራዲዮ ምንጭ ዛሬ በሱዳን ካርቱም የሶስትዮሹ ስብሰባ የሚቀጥል በመሆኑ ውይይቱን የኢትዮጵያንም ጥቅም በሚጠብቅ መልኩ ማስቀጠል ከተቻለ መልካም : ካልሆነ ግን የሶስትዮሽ ውይይቱን ኢትዮጵያ ያለምንም ተጨማሪ እርምጃ ማቆም አለባት ነው ያሉት። [ዋዜማ ራዲዮ]