Building site machines stand on the construction site of the Grand Ethiopian Renaissance Dam in Guba in the North West of Ethiopia, 24 November 2017. The dam is currently being built on the Blue Nile and is going to be the biggest dam in Africa. However, the construction leads to tensions, especially with Egypt that worries about its share in Nile water. Photo by: Gioia Forster/picture-alliance/dpa/AP Images
Grand Ethiopian Renaissance Dam 24 November 2017/AP

ዋዜማ ራዲዮ- የሕዳሴው ግድብ ዋና መሀንዲስ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ባልታወቀ መልኩ ሞተው ከመገኘታቸውን አስቀድሞ በጣልያኑ ተቋራጭ ሳሊኒ እና በመከላከያ ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ (ሚቴክ) መካከል የከረረ አለመግባባት እንደነበር ይፋ ሆኗል።
ሳሊኒ በሚቴክ ዝርክርክ አሰራር ከፍ ያለ የገንዘብ ኪሳራ ደርሶብኛል ብሏል። ሳሊኒ የደረሰበት የኪሳራ መጠን 350 ሚሊየን ዩሮ ያህል እንደሆነ ይናገራል። ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የተገደሉት የፕሮጀክቱ ባለቤት የኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽን የውል ማስተካከያ አድርጎ ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት እያደረገ በነበረበት ወቅት ነው።

የግድቡን የሲቪል ስራ የጣልያኑ ሳሊኒ ኢምፕሪጂሎ ፣ የሀይድሮ ሜካኒካል ማለትም  የውሀ መተላለፊያ : የግድቡን በሮች የመሳሰሉት የሀገር ውስጡ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) : አምርቶ እንዲገጥም ፤ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ማለትም ግድቡ ሀይል እንዲያመነጭ የሚያስችሉት እንደ ተርባይን ያሉ አካላትን የፈረንሳዩ ፍራንሲስ ተርባይን አምርቶ የጣልያኑ ኤሌክትሮ ኮንሠልት እንዲገጥመው ውሉን ደግሞ ሜቴክ እንዲያስተዳድረው ስምምነት ነበር።

ይሁንና ግድቡ ግንባታው ከተጀመረ ሠባት አመት አልፎት በመጀመርያዎቹ ሁለት ተርባይኖች እንደተባለው ሀይል ሊያመነጭ ቀርቶ ውሀን የመያዝ አቅም ላይ እንኳ መድረስ አልቻለም።ይህ መጠነ ሠፊ መጓተት በሳሊኒ እና ሜቴክ መካከል እርስ በርስ ንትርክን አምጥቷል ብለውናል ጉዳዩን የሚያውቁ ምንጮቻችን።

ግድቡ አስራ ስድስት ተርባይኖች የሚኖሩት ሲሆን ከዚህ ውስጥ ሁለቱ በቅርብ ሀይል እንዲያመነጩ ታስበው በቅድሚያ እንዲገጠሙ ተደርጓል። ተርባይኖቹን የመግጠሙ ስራ የጣልያኑ ኤሌክትሮ ኮንሠልት በኩል የተከናወነ ሲሆን ተርባይኖቹ እንዲሰሩ የሚያደርገውን የኤሌክትሮ መካኒካል ስራ ማከናወን የሚቴክ ድርሻ ነው። አሁን ተገጥመው ሀይል ለማመንጨት ዝግጁ ናቸው የተባሉት ሁለቱ ተርባይኖች የቴክኒክ እክል ገጥሟቸው የተደረገው ሙከራ እንዳልተሳካ ፕሮጀክቱን የሚከታተሉ የመንግስት የሰራ ሀላፊዎች በቁጭት ይናገራሉ።

በመገናኛ ብዙሀን በተደጋጋሚ የሀይል ማመንጨት ከአስራ አንድ ወራት በፊት እንደሚጀመር ሲገለፅ ቆይቷል።
የተፈጠረው የቴክኒክ እክል በቀላሉ መስተካከል የሚችል መሆንና አለመሆኑን መተንበይ እንደሚያስቸግር አሁን ግን ፕሮጀክቱን ከሁለት አመት በፊት ወደ ነበረበት ደረጃ እንደመለሰው እየተነገረ ነው።
በጉዳዩ ላይ ቁጭት ያደረባቸው የውሀ መስኖና ኢነርጂ መስሪያ ቤት ሰራተኞች ጉዳዩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ትኩረት እንዲሰጠው ግፊት እያደረጉ መሆኑን ስምተናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ በርካታ የካቢኔ አባላት በፕሮጀክቱ ላይ በተፈጠረው እክልና የአሰራር ብልሹነት ማዘናቸውንና ጉዳዩ ከዚህ በኋላ በብልሀት መከናወን እንዳለበት ስምምነት መኖሩን ተገንዝበናል።

ሳሊኒ እኔ የሲቪል ስራውን በፍጥነት ብሠራም ሜቴክ በየሲቪል ስራው አምርቶ መግጠም ያለበትን የሀይድሮ መካኒካል አካላትን በጊዜው ማድረስ ባለመቻሉ ስራዬ ተጓቷል ይላል ሜቴክ ደግሞ የሳሊኒን ትችት ያስተባብላል። የጣልያኑ ሳሊኒ ኢምፕሪጂሎ ግድቡ ሲጀመር የሲቪል ስራውን ብቻ ሳይሆን የሀይድሮም ሆነ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎችንም የመውሠድ ጽኑ ፍላጎት ነበረው።አጠቃላይ ኮንትራቱ ለብቻው ስላልተሰጠው ገና ከጅምሩ ደስተኛ አልነበረም።አሠሪው መንግስት ደግሞ ሳሊኒ ቅሬታውን የሚያቀርበው ቀድሞ ሜቴክ የተሰጠውን ውል ይፈልገው ስለነበር የጥቅም ጥያቄ ነው በሚል ጉዳዩን እያጣራ ውሳኔ የሚሠጥ ቡድን በውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር መሪነት እንዲቋቋም አድርጎም ነበር። በሂደት ሲታይ ግን የሳሊኒ አቤቱታ የጥቅም ሳይሆን ሜቴክ ላይ የሚታይ ከፍተኛ የአቅም ክፍተት መሆኑ በግልጽ ታይቷል ።

ለዚህም የሳሊኒንና የሜቴክን የስራ አፈጻጸም በማነጻጸር ማየት ይቻላል። 1 ነብጥ 8 ኪሎ ሜትር የጎን ስፋትና 145 ሜትር ቁመት ያለው ዋናው የግድቡ አካል የሲቪል ስራ በሳሊኒ የሚሠራ ሲሆን ዋናው ግድብ የተጠቀሠውን ስፋትና ቁመት እንዲያገኝ 10.1 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ሮለር ኮምፓክት ኮንክሪት (ጥቅጥቅ ኮንክሪት) መሞላት አለበት።ሳሊኒ ከዚህ ውስጥ ከስምንት ሚሊዮን ሜትር ኪዩቡን ኮንክሪት ከሞላ ሁለት አመት ሊሆነው ነው። ይህ ያለጨረታ ስራውን በማግኘቱ ጥያቄ የሚያነሱበት ቢኖሩም የስራ ፍጥነቱን ማሳየቱ ግን አይካድም። 5.2 ኪሎ ሜትር የጎን ስፋትና 50 ሜትር ቁመት ያለው በግድቡ በስተ በግራ በኩል ያለው አቃፊ ወይንም (ሳድል ዳም) ግንባታም በጥሩ ሁኔታ ተሰርቷል።

በሲቪል ስራው ላይ ይህ ሁሉ ይሠራ እንጂ ግድቡ ሀይል ማመንጨት ብቻ ሳይሆን ውሀ ለመያዝ አልበቃም።ከጥቂት አመት ወዲህ ግድቡን ደጋግሞ ላየ ከአንዱ ጉብኝት ቀጣዩ ጉብኝት ላይ የግንባታ ለውጥ አያይም ። ሳሊኒ ዋናውን ግድብ ከግራና ቀኝ በኩል የሚፈለገው ከፍታ ላይ አድርሶታል።። የዋናው ግድብ መካከለኛ ክፍል ግን ከግራና ቀኞቹ በጣም ዝቅ ብሎ መታየት ከጀመረ አመታት ተቆጠሩ።

እዚህ ክፍት ቦታ ላይ የሲቪል ስራ እንዲቀጥል ውሀን ወደ ሀይል ማመንጫዎች እንዲልክ የሚያስችል (Water Intake) ያሉ የሀይድሮ ሜካኒካል አካላት መተከል አለባቸው። የዚህን አካል ስራ ሜቴክ አጓቶታል።እዚሁ የግድቡ አካል ውስጥ የሚገጠሙ የውሀው ማስተንፈሻ (ከልቨርት እና ቦተም አውትሌት)  አካላት ተጓተው ነበር ።

ሜቴክ ያመረታቸውና ግድቡ ላይ የሚገጠሙ በሮችም አበያየዳቸው ሙሉ ጥንካሬ የላቸውም ብሎ ሳሊኒ ቅሬታውን አቅርቦ ነበር። ከብየዳ አንጻር ፔን ስቶክ ወይንም ውሀ ማስወንጨፊያ አካላት ላይም ሳሊኒ ቅሬታውን በሜቴክ ላይ አቅርቧል። ፔን ስቶክ ላይ የብየዳም ብቻ ሳይሆን የፍጥነት ችግሩም ከፍተኛ ነው። እነዚህ በግድቡ የታችኛው ገጽታ ላይ ውሀው ሀይል እንዲኖረው አድርገው የሚያስወነጭፉት ፔን ስቶኮች በተርባይኖቹ ቁጥር  ልክ አስራ ስድስት ያስፈልጋሉ።ሆኖም ሜቴክ ሁለቱን አምርቶ መጨረስ እንኳ ፈተና ሆኖበታል ። ራዲያል ጌት የሚባሉት ሁለት ግዙፍ በሮች አቃቂ በሚገኘው የሜቴክ ቅርንጫፍ ፋብሪካ ተመርተው ሊወጡ አልቻሉም። አሁን አንዳንድ ስራዎችን ሜቴክ ራሡ ለሶስተኛ አካል ሠጥቻለሁ እያለ ነው።

በሁለቱ የግንባታ ተቋራጮች መካከል ያለው የአቅም ልዩነት ብቻ ሳይሆን ውዝግቡ እየተካረረ ሄዶ ስራውን ማከናወን የሚያስቸግርበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ሚቴክ በተለያዩ ወታደራዊ የስራ ሀላፊዎቹ በኩል ሳሊኒና የኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽንን እስከ አንድ ቢሊየን ብር ክፍያ አልፈፀማችሁልኝም፣ ሳሊኒ ሊያዘኝ አይገባም የሚሉ የቅሬታና ማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎችን ሲፅፍ ስንብቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር በግድቡ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና መዋቅራዊ ማሻሻያ ለማድረግ ሲሞከር ነበር። የኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽንን እና የሚቴክ ሃላፊዎችን በአዲስ በመተካት ለውጥ ለማምጣት ተሞክሯል። በመሀል የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት ሂደቱን አጓቶታል። የአሟሟታቸው ሁኔታ በምርመራ አለመረጋገጡንና ከግድቡ ስራ ጋር ይያያዛል የሚለው ሰፊ ግምትም በግድቡ ቀጣይ ስራ ላይ ጥላውን ማሳረፉ አይቀርም የሚሉ አሉ።