ዋዜማ ራዲዮ- በስነምግባር ጉድለትና ብሄርን መሰረት ባደረገ ወገንተኝነት ከስራ ውጪ የተደረገውን የሐረሪ ክልል ፖሊስ ከውድቀት ለመታደግ የፖሊስ አባላቱ የተሀድሶ ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ነው። የክልሉ ፖሊስ አገልግሎት በመከላከያ ሰራዊትና በፌደራል ፖሊስ እጅ መወደቁን ተከትሎ የክልሉ ፖሊስ አባላት ሰንዳፋ ፖሊስ ማስልጠኛ ኮሌጅ ለአንድ ወር የሚቆይ ስልጠና በተለያየ ዙር እየወሰዱ ነው።


በሐረሪ ክልል በነዋሪዎች ላይ አጋጥሞ የነበረው የጸጥታ ችግር በሌሎች አካባቢዎች ሲያጋጥም ከቆየው በእጅጉ የተለየ እንደሆነ ነው ምንጮቻችን የሚናገሩት፡፡የዚህ መነሻው ለአካባቢው ነዋሪ ስጋት የሆነው ችግር የሚፈጸመው ነዋሪው ደህንነቴን ያረጋግጡልኛል የሚል ተስፋ በሚጥልባቸው የጸጥታ አካላት መሆኑ ነው፡፡ በተለይ በኦሮሞ ተወላጅ ፖሊሶችና በሐረሪ ተወላጅ ፖሊሶች መካከል ያለው ውጥረትና እና አልፎ አልፎም እስከ መጋጨት የደረሰ ችግር መከሰቱ የፖሊስ አገልግሎቱ የመፍረስ ደረጃ አድርሶት ቆይቷል፡፡

ከዚህ በኋላ ነው የክልሉ መንግስት የክልሉን የጸጥታ መዋቅር የፌደራሉ መንግስት እንዲረከበው ጥያቄ ያቀረበው፡፡ ፌደራሉ መንግስትም ጥያቄውን በመቀበል በቀጥታ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጠ ትእዛዝ መሰረት የፌደራል እና መከላከያ ሃይሉ የክልሉን የጸጥታ አገልግሎት እንዲረከብ ተደርጓል፡፡

የመከላከያ ሃይሉ በክልሉ የሚገኙ ዋና ዋና የፌደራል ተቋማትንም እንዲጠብቅ ሲደረግ፤ የፌደራል ፖሊስ ደግሞ የእለት ተእለት የከተማዋን የጸጥታ ጥበቃ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ በኋላም ከክልሉ አጠቃላይ የፖሊስ ሃይል 50 ከመቶ የሚሆነው ለተሃድሶ ስልጠና በሚል ወደ ማሰልጠኛ ተቋም እንዲገባ መደረጉ ይታወሳል፡፡

የክልሉን የፖሊስ ሃይልም በሁለት ዙር በማደራጀት ሰንዳፋ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ተከታታይ ስልጠና እና ተሃድሶ እንዲወስድ እየተደረገ ነው፡፡ ዋዜማ ሬዲዮ እንዳረጋገጠችው የፖሊስ ሃይሉን ለተሃድሶ ስልጠና ለማስገባት በተደረገው ግምገማ እጅግ አስደንጋጭ የሆኑ የወንጀል እንቅስቃሴዎች በክልሉ ፖሊስ ይፈጸም እንደነበር ተደርሶበታል፡፡

ከፍተኛ ከሚባለው በአካባቢው ከሚስተዋለው የህገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የክልሉ ፖሊሥ አባላት ቀጥተኛ ተሳታፊ ከመሆን ጀምሮ በማን አለብኝነት የሚፈጸሙ በሆቴሎችና በተለያዩ አገልግሎት መሥጫዎች ከተጠቀሙ በሃላ ሂሳብ አልከፍልም የማለት ተግባራት ድረስ በስፋት ሲፈጸሙ እንደነበር በግምገማ መለየቱን ምንጮቻችን ይናገራሉ፡፡

በርካታ የፖሊስ አባላት ከራሳቸው የብሄር ተወላጅ ውጪ በሆኑ የፖሊስ አዛዦቻቸው የሚሰጣቸውን መመሪያና ትእዛዝ እስካለመቀበል የደረሰ መመሰቃቀል ፈጥሮ ቆይታል [ዋዜማ ራዲዮ]