ዋዜማ ራዲዮ- በተለያዩ የልማትና ግንባታ ስራዎች ምክንያት ከእርሻ ቦታቸው ያለበቂ ካሳ አልያም ያለምንም ማካካሻ መሬታቸውን ያጡ አርሶ አደሮችችና ቤተሰቦቻቸው አንዳንዶቹ በቅርቡ የተሰጣቸውን የጋራ መኖሪያ ቤት ከፍ ባለ ዋጋ እየሸጡት መሆኑን ዋዜማ አረጋግጣለች።

በአዲስ አበባ ዳርቻ ለነበሩ አርሶ አደሮች በከተማው ካቢኔ ደረጃ አስወስኖ ለካሳነት ያከፋፈለው የጋራ መኖርያ ኮንደሚኒየም ቤቶችን የወሰዱ የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች አንዳንዶቹ ቤቱን ሳይኖሩበት እየሸጡት መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ ባደረገችው ክትትል ተመልክታለች።

ቤቶቹን ከአምስት አመት በፊት መሸጥ የተከለከለ ቢሆንም አሁን ሽያጩ በስውር ስምምነትና በብድር መያዣነት ሽፋን እየተቸበቸበ ነው።
     
 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ በነበሩበት በ2011 አ.ም ነው 22, 915 የጋራ መኖርያ ኮንደሚኒየም ቤቶች ለልማት ተነሽ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው በካሳነት እንዲሰጥ የተወሰነው።

ሆኖም ለቤቱ ባለቤትነት የተመረጡ አርሶ አደሮች የጋራ መኖርያ ቤቱ ይገባቸው አይገባቸው በአሁኗ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የማጣራት ስራ እንዲከናወን ከተደረገ በሁዋላ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ከተገነቡት የጋራ መኖርያ ቤት ኮንደሚኒየሞች መካከል 22, 915ቱ ለተነሽ አርሶ አደሮች በካሳነት እንዲሰጥ ተደርጓል። የተመረጡት የልማት ተነሽ አርሶ አደሮችም በቅርቡ የቤቶቹን ካርታ ተረክበዋል።

እነዚህ ለካሳነት የተሰጡ ቤቶች ለአርሶ አደሮች እስከ ካርታው ይድረሳቸው እንጂ ቤቱን ከተረከቡ ከአምስት አመት ወዲህ መሸጥ አይችሉም። ነገር ግን የቤቶቹ ሽያጭ እየተከናወነ ያለው በብድር ውል ነው።ቤቱን መግዛት የፈለገው ግለሰብ ቤቱን ለሚሸጥለት የልማት ተነሽ አርሶ አደር የቤቱን ዋጋ የሚያህል ገንዘብ እንዳበደረውና ለብድር ክፍያ ማስያዣም የቤቱ ባለቤት የቤቱን ካርታ ለአበዳሪው እንዲሰጠው ተደርጎ ያንን ገንዘብም በጊዜ ገደብ እንዲከፍለው ውል ይፈራረማሉ። ቀድሞ በሚታወቅ ምክንያትም የልማት ተነሽ የሆነው አርሶ አደር ወይንም የልማት ተነሽ አርሶ አደር ቤተሰብ ገንዘብ ላበደረው ለቤቱ ገዥ ብድሩን ስለማይመልስ የገንዘቡ አበዳሪ ቤቱን ይረከባል። ቤቱን የገዛው ግለሰብም አምስት አመት ሲሞላው ቤቱን በራሱ ስም ያዞራል።

ይህ አይነቱ አሰራር በእጣ የደረሳቸው የቤት እድለኞችም ቤቶችን ለመሸጥ ይጠቀሙበት የነበረ ቢሆንም የልማት ተነሽ አርሶአደሮች ለካሳነት የተሰጠውን የጋራ መኖርያ በብድር ውል መግዛት በጣም ተመራጭ ሆኗል።የዚህም መነሻው ለካሳነት የተሰጡት ቤቶች የባንክ እዳ የሌለባቸው መሆኑ የቤቶቹን ገዥ ካርታውን ቶሎ እንዲያገኝ አድርጎታል። እንዲሁም ቤቶቹ የባንክ እዳ የሌለባቸው መሆኑ በእጣ የጋራ መኖርያ ቤቶቹ ባለ እድል ከሆኑት ግለሰቦች አንጻር ዋጋውን ወረድ ያደርገዋል። በእጣ የጋራ መኖርያ ቤቶች እድለኛ የሆኑ ግለሰቦች ከአምስት አመት በፊት ቤቶቹን ለመሸጥ ሲፈልጉ ለገዥው ከባንክ ጋር የገቡትን የብድር ውል ነው የሚሰጡት። ያለባቸውን እዳ ከግምት ስለሚያስገቡም ከልማት ተነሽ አርሶ አደር የጋራ መኖርያ ቤቶች አንጻር ዋጋውን ወደድ ያደርጉታል።

 የዋዜማ ራዲዮ ዘጋቢ ሽያጩ በዋናነት እየተከናወነበት ባለው የኮዬ ፈጩ የጋራ መኖርያ ቤቶች ተገኝቶ እንዳየውም የጋር መኖርያ ቤት ለካሳነት የተሰጣቸው የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች ባለሶስት መኝታ ቤቱን እንዳለበት የፎቅ ከፍታ በአማካይ ከ700 ሺህ ብር ጀምሮ እንደሚሸጡ ተመልክቷል። ደላሎች ፣ የቤቱ ገዥዎችና ሻጮችም የመረጃችን ምንጮች ናቸው። [ዋዜማ ራዲዮ]