Ethiopia Parliament
Ethiopia Parliament

ዋዜማ ራዲዮ- መቶ በመቶ በገዢው ፓርቲ እና በአጋሮቹ የተሞላው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዛሬ ከቀረቦለት አጀንዳዎች ውስጥ በአንድ ተቃውሞ እና በአንድ ድምፀ ተአቅቦ አስተናግዷል። አጀንዳው በሀገሪቱ በየ10 ዓመት ልዩነት የሚካሄደውን የህዝብ እና የቤቶች ቆጠራ በበላይነት ለሚመራው ኮሚሽን አባላትን መሾም ነበር።

በዚህም መሰረት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሰብሳቢነት የሚመራ 23 አባላት ያሉበት ኮሚሽን ተሰይሟል። ከአባላቱ መካከል ስድስቱ ሚኒስትሮች ናቸው። ሚኒስትሮቹ ከገንዝብ እና ኢኮኖሚ ፣ ትምህርት፣ ጤና ጥበቃ፣ ትራንስፖርት፣ ፌደራል እና አርብቶ አደሮች እንደዚሁም ከእርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የተውጣጡ ናቸው።

የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ይናገር ደሴ እና የመንግስት ኮሚኔኬሽን ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ የኮሚሽኑ አባል እንዲሆኑ ተሰይመዋል። ከፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ሌላ እያንዳንዱ ክልል ከሀረሪ በስተቀር በምክትል መስተዳድር ደረጃ በኮሚሽኑ ተወክለዋል። የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድሩን አቶ ሙራድ አብዱላሂን ለኮሚሽኑ ያዋጣ ሲሆን ድሬዳዋ እና አዲስ አበባ በምክትል ከንቲባዎቻቸው ቦታ አግኝተዋል።

ከኮሚሽኑ አባላት መካከል የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት ወይዘሮ ሱአድ አህመድ ብቸኛዋ ሴት መሆናቸው በፓርላማ አባላቱ ጥያቄ አስነስቷል። የባለፈው የህዝብ እና ቤት ቆጠራ ችግር እንደነበረበት ያነሱት የፓርላማ አባላት ዳግም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይፈጠርም አሳስበዋል።

ያለፈው የህዝብ እና ቤት ቆጠራ ውጤት በፓርላማ አባላት ፊት ይፋ ሲደረግ በገዢው ፓርቲ አባላት ዘንድ ሳይቀር ከፍተኛ ተቃውሞ መቀስቀሱ አይዘነጋም። ከውዝግቦቹ ሁሉ ከፍተኛ ትኩረትን ስቦ የነበረው የአማራ ብሔር ተወላጆች ቁጥር ቀንሶ መታየቱ እና የአዲስ አበባ ህዝብ ቁጥር ከሚገመተው በታች አነስተኛ ሆኖ በውጤቱ ላይ መቅረቡ ነበር።

በዛሬው የፓርላማ ውሎ በአዲሱ ኮሚሽን አወቃቀር ያልረኩ የሚመስሉት የፓርላማ አባላት አንድ ተቃውሞ እና ዘጠኝ ድምፀ ተአቅቦ በማስመዝገብ በሹመቱ አለመስማማታቸውን አሳይተዋል።

የህዝብ እና ቤቶች ቆጠራ በሚቀጥለው ዓመት ህዳር ውስጥ እንደሚካሄድ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር ወደ 100 ሚሊዮን መጠጋቱን የተባበሩት መንግስታት ዓመታዊ የህዝብ ብዛት ሪፖርት እና የሲ.አይ.ኤ ዓለም አቀፍ የእውነታ መጽሐፍ ያመለክታሉ። እስከ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት በድረ-ገጹ የሚያስነብበው የማዕከላዊ ስታትስቲክ ኤጀንሲ ግን ትንበያዊ ቁጥሩ 90 ሚሊዮን መሆኑን ያሳያል።