VISUALIZE
VISUALIZE -CLICK!

ዋዜማ ራዲዮ- በየአስር ዐመቱ የሚካሄደው ሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በውስብስብ ጥያቄዎችና ችግሮች ታጥሮ ከተፍ ብሏል፡፡በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አማካኝነት የሚካሄደው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለታል፡፡ በኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ሕዝብና ቤቶች ቆጠራ የተጀመረው ከ1976 ዓ.ም ነበር፡፡ ዐለም ዐቀፍ ድርጅቶች ባሁኑ ጊዜ ጠቅላላ ሕዝብ ብዛት 100 ሚሊዮን እንደደረሰ ሲገምቱ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ትንበያ ግን 90 ሚሊዮን ገደማ መሆኑን ይገልጻል፡፡

አሁን ኢሕአዴግ የሚመራው መንግስትና በጠቅላላው ሀገሪቱ ከገቡበት ፖለቲካዊ አጣብቂኝ አንጻር ሲታይ የዘንድሮው ሕዝብና ቤት ቆጠራ ከድሮው በተለየ ልዩ ትኩረት እንደሚስብና ተግዳሮቶችም እንደሚበዙበት ከወዲሁ መናገር አይከብድም፡፡ በርግጥ ዕቅዱ በሚጠበቀው ደረጃ የመገናኛ ብዙሃንን እና ፖለቲከኞችን ትኩረት በበቂ ሁኔታ አልሳበም ማለት ይቻላል፡፡ የሀገሪቱ አጠቃላይ ድባብ መጠነ-ሰፊውን ዕቅድ ተራ የመንግሥት ሥራ ነው ያስመሰለው፡፡ ይሄ ማለት ግን በቆጠራው ሂደትም ሆነ በውጤት አገላለጹ ከድሮው በተለየ ሁኔታ አወዛጋቢ ጉዳዮች ላለመነሳታቸው ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡ ብሄርን መሰረት ባደረገ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ የህዝብ ቆጠራ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ትርጉም አለው። [የድምፅ ዘገባ ከታች ያገኛሉ]

የሚቆጠረው ብሄራችን (ማንነታችን) ነው?

ሀገር ዐቀፍ ሕዝብና ቤት ቆጠራ ለሀገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ፋይዳ ጉልህ ነው፡፡ በተለይ በፌደራላዊ ስርዓት ሕዝብና ቤት ቆጠራ ለአንገብጋቢ ፖለቲካዊና የልማት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጠውን ያህል ሌሎች ፖለቲካዊ ጥያቄዎችንም ሊወልድ ይችላል፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ፣ የሰው ሃይል፣ ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ መጠነ-ሰፊ ሥራ እንደሆነም ግልጽ ነው፡፡

የመጨዎቹ አሥር ዐመታት የተለያዩ የልማት ፖሊሲዎች የሚቀረጹት የዘንድሮውን ህዝብ ቆጠራ መረጃና ወደፊት በየጊዜው የሚሰጡትን ትንበያዎች መሰረት አድርገው እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤትም ፌደራል መንግስቱ በየዐመቱ ለክልሎች የሚሰጠውን የድጉማ ቀመር የሚሰራው በከፊል በክልሎች ሕዝብ ብዛት ላይ ተመርኩዞ ነው፡፡ በቅርቡ ደሞ የሕዝብ ቁጥር ዋነኛው የባጀት ቀመር መደልደያ መስፈርት ሆኗል፡፡ በልማት ኋላ ቀር የሆኑት አናሳ ክልሎች ይቅሩና አራቱ ትላልቅ ክልሎችም ትላልቅ የልማት ሥራዎቻቸው በፌደራሉ መንግሥት ድጎማ ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡

ሕዝባዊ ተቃውሞውን ለቀሰቀሰው የወጣቶች ግዙፍ ስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ቃል ቢገባም እዚህም እዚያም ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከመገንባት የዘለለ ዘላቂ የተባለው መፍትሄ የውሃ ሽታ ሆኖ ነው የቀረው፡፡ ይሄ ችግር ሳይፈታ የዘንድሮው ሕዝብ ቆጠራ የሀገሪቱ ወጣቶች ብዛት በብዙ እጅ እንዳደገ የሚያሳይ መረጃ ይዞ ብቅ ሊል ከወዲሁ መናገር ይቻላል፡፡

መቼም ኢሕአዴግ-መራሹ መንግሥት አሁንም “ሕዝብ ቆጠራ” (population census) የሚለውን ስያሜ ቢጠቀምም ቆጠራው ግን በመሠረቱ “የብሄረሰብ ወይም ማንነት ቆጠራ” (ethnic census) ስለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም፡፡ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ከሕገ መንግስቱ መሰረት የተቋቋመ በመሆኑ የብሄረሰብ መመዝገቢያ ቅጹ ራሳቸውን በብሄር ማንነት ለማይመድቡ ዜጎች ቦታ ሊኖረው አይችልም፡፡ እናም ከሁለት እና ከዚያ በላይ ብሄረሰብ የሚወለድ ዜጋ ሁሉ እንደተለመደው “አንዱን ምረጥ” የሚል ምንም ሞራላዊ እና ሕጋዊ መሰረት የሌለው ምርጫ ነው የሚቀርብለት፡፡

ቆጠራውና የተባባሰው የፖለቲካ ቀውስ

መንግስት የዘንድሮውን ሕዝብና ቤት ቆጠራ ለማካሄድ ምን ፖለቲካዊ፣ ሞራላዊ እና ነባራዊ መሠረቶች አሉት? የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ቆጠራውን ለማካሄድ ዝግጅቱ እየጧጧፈ ያለው መላ ሀገሪቱ በተማከለ ወታደራዊ ዕዝ በሚመራ ጸጥታ አጠባበቅ ስር በመሆኗ ያለችበት ሁኔታ በከፊል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊባል የሚችል ነው፡፡ አሁንም የሀገሪቱ ሰላም እየተጠበቀ ያለው በመደበኛ ጸጥታ ሃይሎች ሳይሆን በሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ነው፡፡ እዚህም እዚያም ብሄርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በርክተዋል፡፡

ጸጥታ ሃይሎች በሰላማዊ ተቃዋሚ ሕዝብ ላይ በሚወስዱት የሃይል ርምጃ በርካቶች ተገድለዋል፡፡ አሁንም እየተገደሉ ነው፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው ከቀያቸው ይፈናቀላሉ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በያዝነው ወር ይቅርና በቀጣዮቹ በርካታ ወራትም መሻሻል ስለማሳየታቸው ምንም ዋስትና የለም፡፡

በ1999ኙ ሀገር ዐቀፍ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ማግስት የአማራ ክልል ህዝብ ለምን ከተገመተው በታች እንደቀነሰ የስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሃላፊዋ ወይዘሮ ሳሚያ ዘካሪያ በፓርላማው ሲጠየቁ የክልሉ ሕዝብ ቁጥር ከተገመተው በታች ለምን እንደቀነሰ ሲጠየቁ ያለሙያቸው ገብተው “ብዙ ሕዝብ በኤድስ በሽታ ሳቢያ በመሞቱ ነው” የሚል ዘረኛ ምላሽ በመስጠታቸው ክፍተኛ ውግዘት ደርሶባቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የሆነው ሆኖ ሃላፊዋ ለዘረኛ አባባላቸው ይቅርታ ሳይጠይቁ ኖረው አራተኛው ህዝብ ቆጠራ በሚካሄድበት ዋዜማ ላይ ከጥቂት ቀናት በፊት ለአወዛጋቢው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሃላፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡

የክልል መንግስታት የፌደራሉ ሕገ መንግስት ካስቀመጠው መርሆ በተቃራኒ በየክልላቸው ላሉ አናሳ ብሄረሰቦች በቂ ሕጋዊ፣ አስታደራዊና ፖለቲካዊ መብት አልሰጡም፡፡ ከአማራ ክልል በስተቀር ሌሎች ክልሎች የተራ ዘጎችን ይቅርና የአናሳ ብሄረሰቦችን በራሳቸው ቋንቋ የመማር፣ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ለመሳሰሉ መብቶች ተግባራዊ ምላሽ አልሰጡም፡፡

ለተወሰኑ ክልሎች ቆጠራው ወሳኝ የፖለቲካ ግብ ነው

በተለይ በአዲሳባ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል፣ ድሬዳዋ እና ሐረሬ ክልሎች የሚካሄደው ቆጠራ ልዩ ትኩረት መሳቡ አይቀርም፡፡ በተለይ አዲሳባ ከምንጌዜውም በላይ የትኩረት ማዕከል እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡

ባለፉት ሁለት ዐመታት ለከተማዋ የተሰራው መሪ ዐቅድ (ማስተር ፕላን) ከባድ ውዝግብ እና ደም አፋሳሽ ግጭት አስነስቶ በእንጥልጥል እንደቀረ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ብሄርተኞች በከተማዋ ላይ የባለቤትነት ጥያቄ ሲያነሱ ሲያነሱ ከታሪክ እና ከከተማዋ የግዛት አቀማመጥ ሌላ ጥያቄውን ወደፊት ለመግፋት የሚጠቅማቸው አንዱ መከራከሪያ የኦሮሞ ተወላጆች በከተማዋ ያላቸው ብዛት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ችግሩ ግን አብዛኛው የከተማዋ ሕዝብ በመንግሥት ቅጾች አስገዳጅነት አንዱን የብሄር ማንነት እንዲይዝ ካልተደረገ በስተቀር ራሱን ከአንድ ወይም ከሌላ ብሄረሰብ የሚመድብ እንዳልሆነ ነው በስፋት የሚታመነው፡፡

በያዝነው ወር እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በገዥው ፓርቲና መንግስት ከፍተኛ መዋቅሮች አንገብገቢ ፖለቲካዊ ጉዳይ ሆኖ የመውጣት እድል እንዳለው መገመት አያስቸግርም፡፡ ምክንያቱም ቆጠራውን ከድሮው የተለየ የሚያደርጉት ብዙ ፖለቲካዊ ምክንያቶች አሉ፡፡

በርግጥም ለሕዝብና ቤት ቆጠራ ሲባል የበታች አስተዳደሮችን እና ክልሎችን ድንበር በጊዜያዊነት መከለል፣ የዜጎችን ሙሉ መረጃ መሰብሰብ፣ ማጠናቀር እና የመጨረሻውን ውጤት በብሄረሰብ፣ በክልል እና ሀገር ደረጃ ለይቶ ይፋ ማድረግ ዴሞክራሲና ተቋማዊነት እጦት እና ብዝሃነት ባለባቸው ሀገሮች ተራ ሳይንሳዊ ክንውን ሳይሆን ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ የብሄር ማንነትን መሠረት ያደረገ ፌደራላዊ አወቃቀር በምትከተል ሀገር ሲሆን ደሞ በሂደቱና ውጤቱ ላይ የሚያጠላው ጥላ ይገዝፋል፡፡

በርግጥ ሀገሪቱ ባንድ ገናና ገዥ ግንባር ተጠርንፋ የተያዘች በመሆኗ ሕዝብ ቆጠራ ካሁን ቀደም ውዝግብ ፈጥሮ አያውቅም፡፡ በጉዳዩ ላይ የተደረጉ ጥናቶችም የሉም፡፡

ባለፉት ሦስት ዐመታት በተለይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልና የፍትሃዊ ልማት ተጠቃሚነት ጥያቄ ከታች እስከላይ ገፍቶ የመጣ ጥያቄ መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ደሞ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ የኦሮሞ ህዝብ ከፍትሃዊ ሃብት ክፍፍል ተጠቃሚ እንዲሆን እንደሚታገል አጽንዖት ሰጥቷል፡፡ ፍትሃዊ እና ትክክለኛ የሆነ የህዝብ ቆጠራ መረጃ ደሞ ይህንኑ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ነው የሚጫወተው፡፡ ከብሄሩ መብት ተሟጋቾች በተጨማሪ ኦሕዴድም ካለፈው ዐመት ወዲህ ኦሮምኛ ቋንቋን የፌደራል ቋንቋ ለማድረግ እንደሚታገል በቅርቡ ባወጣው መግለጫው ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል የኦሮሞ ብሄር መብት ተሟጋቾች በአዲሳባ ከተማ ላይ በርካታ ጥያቄዎችን ባነሱበት ማግስት የሚካሄድ ህዝብ ቆጠራ መሆኑ በተለይ አዲሳባ ላይ ለሚረገው ህዝብ ቆጠራ ልዩ ፖለቲካዊ ገጽታ ይሰጠዋል፡፡ የአዲሳባ ከተማ ባለቤትነት ጉዳይ ፌደራል መንግስቱን፣ ኦሮሚያ ክልልን፣ ተቃዋሚ ድርጅቶችን፣ የመብት ተሟጋቾችንና በተለምዶ ቁቤ እየተባ የሚጠሩትን የኦሮሞ ወጣቶች ሲያላትም የከረመ ነው፡፡ ከሀገር ውጭ ያሉ አክራሪ የብሄሩ መብት ተሟጋቾችና ፖለቲከኞች ለመጀመሪያ ጊዜ ሊባል በሚችል ሁኔታ ከኦሕዴድ ጋር ባንድ ግንባር እንዲሰለፉ ማድረግ ችሏል፡፡

ኦሮምኛ ቋንቋን በአደሳባ ከተማ የአስተዳደራዊ እና መማሪያ ቋንቋ እንዲሆን ግፊቱ ጠንክሯል፡፡ የኦሮሚያ ክልል በከተማዋ ላይ ስላለው ልዩ አስተዳደራዊ ጥቅም በሕገ መንግስቱ የተደነገገ በመሆኑ ይህንኑ ወደ ተግባር ለመለወጥ ኦሕዴድ ከወራት በፊት መነሻ ረቂቅ ሕግ አዘጋጅቷል፡፡ መነሻ ሃሳቡ ደሞ ኦሮምኛን የሥራ ቋንቋ ማድረግን፣ በአስተዳደር አካላት ውክልና የማግኘትን እና የቦታ ስያሜዎችን መለወጥን የመሳሰሉ አንቀጾችን አካቶ የያዘ ነው፡፡ ይሄ ማለት ደሞ ሕገ መንግስታዊው መብት በተሟላ ሁኔታ እንዲፈጸም ደሞ ኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ በከተማዋ ያለውን ብዛት በትክክል ማወቅ ዋነኛው ግብዓት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ቆጠራው የሚካሄደው ደሞ ይሄንኑ ልዩ ጥቅም የሚመለከተው ረቂቅ አዋጅ ገና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሳይጸድቅ ነው፡፡

እናም ኦሕዴድ ምናልባት ከአዲሳባው ሕዝብ ቆጠራ ውጤት ጠቃሚ ግብዓት ካገኘበት ረቂቅ ሃሳቡን ለማጎልበት ወይንም ወደፊት የሚወጣውን አዋጅ ተገቢነት ለማሳመን ጥሩ እድል ይፈጥርለታል፡፡

ከሰባት ዐመት በፊት በደቡብ ክልል፣ በጉራ ፈርዳ ወረዳ ነዋሪ በነበሩ የአማራ ብሄር ተወላጆች ላይ የማፈናቀል ወንጀል የፈጸሙ የወረዳው የበታች አስተዳደር እና ጸጥታ ሃላፊዎች ላይ ምንም ርምጃ ሳይወስድ የኖረው የክልሉ ፍርድ ቤት ከሳምንት በፊት ጥቂት ወንጀለኞችን በእስር መቅጣቱ በገዥው ግንባር ኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረው የሃይል ሚዛን መነቃነቅ እና ሕዝባዊ ተቃውሞው መበርታቱ ባንድ ላይ ተዳምረው ያመጡት ውጤት ይመስላል፡፡

በብሄር ተኮሩ ፌደራላዊ አወቃቀር ሳቢያ በተለይ በስድስቱ ክልሎች- ማለትም በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ሱማሌ እና አፋር- ያሉ ክልል መንገስታት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መዋቅር በገናናው ብሄረሰብ የበላይነት የተያዘ በመሆኑ ላለፉት ሃያ ዐመታት የክልል ድንበር ተሻጋሪ ፍልሰት ውስን ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ይልቁንስ አልፎ አልፎ በደቡብ እና ቤንሻንጉል ክልል ይታይ የነበረው ማንነትን መሠረት ያደረገ ውስን የህዝቦች መፈናቀል በያዝነው ዐመት በመጠን ሰፍቶ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ኦሮምኛ ተናጋሪ ዜጎች ከሱማሌ ክልል ተፈናቅለዋል፡፡ በርግጥ ከአዲሳባ ሌላ በአዳማ፣ አዲሳባ፣ ሀዋሳ እና ድሬዳዋ የሕዝብ ስብጥር ያለማቋረጥ ሲቀየር እንደኖረ ለእውነታ የቀረበ ግምት መያዝ ይቻል ይሆናል፡፡

የድንበርና የማንነት ጥያቄዎች ቆጠራውን የበለጠ ፖለቲካዊ ያደርጉታል

እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀሉም ነገር በብሄር ማንነትና በብሄረሰቦች ብዛት ላይ በቆመበት ሀገር ሳይንሳዊ ህዝብ ቆጠራ ይፋ ማድረግ አስቸጋሪ በመሆኑ የብሄረሰቦችን፣ ክልሎችን እና አጠቃላይ የመላ ሀገሪቱን ትክክለኛ ሕዝብ ብዛት ይፋ ማድረግ ቀላል አይሆንም፡፡ እናም ከጸጥታ ችግሮች ባሻገር የፓርቲ እና መንግሥት ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት በኤጀንሲው ሥራ ላይ እክል ሊፈጥር ይችላል፡፡

በተለይ የኤጀንሲው ተቋማዊ ጥንካሬ እና ነጻነት ውስን መሆን እንዲሁም የሕግ አውጭ አካላት እና መገናኛ ብዙሃን ያላቸው የቁጥጥር እና ክትትል አቅም ውስን መሆኑ ለፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነቱ ዕድል እንደሚፈጥር ካሁን በፊትም በተለያዩ ሀገራዊ ክንውኖች የታየ ክፍተት ስለመሆኑ ዓሊ የሚባል አይደለም፡፡ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች መጠነ-ሰፊ ሕዝባዊ አመጽ የተነሳበት ኢሕአዴግና በተለይም አስኳል ድርጅቱ ሕወሃት የህዝብ ቆጠራ ሂደቱን እና ውጤቱን እንዴት ይቀበሉት ይሆን? የሚለው ጥያቄ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡

በትግራይ ክልል ስር ያሉ ወልቃይቶች ብሄረሰብ ማንነት ጥያቄ ሁነኛ ሕገ መንግስታዊ ምላሽ ሳያገኝ በእንጥልጥል ባለበት ሁኔታ ነው ሀገር ዐቀፉ ሕዝብ ቆጠራ የሚካሄደው፡፡ በአማራ ክልልም በቅማንት ማንነት ላይ በጥቂት ቀበሌዎች ወደፊት የተገፉት ሕዝበ ውሳኔዎች ገና አልተካሄዱም፡፡ በአማራ እና ትግራይ እንዲሁም በኦሮሚያ እና ሱማሌ ክልሎች መካከል ሲንከባለሉ የኖሩ የወሰን ይገባኛል ውዝግቦች ገና መፍትሄ አላገኙም፡፡ በደቡብ ክልልም ተመሳሳይ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ኤጀንሲው እነዚህ ውዝግቦች እልባት ያገኙ መሆናቸውን ጠቅሶ ቆጠራውን ለማካሄድ አስተማማኝ ሁኔታ እንዳለ ሰሞኑን ቢገልጽም ካሁን በፊት ያሉ ልምዶች የሚያሳዩት ግን ውዝግቦቹ ተፈቱ ከተባለ በኋላ ተመልሰው እንደ አዲስ እንደሚያገረሹ ነው፡፡ ምናልባት ካልተሳካለት ግን በሌላ ጊዜ ልዩ ቆጠራ ለማካሄድ ነው እቅድ የያዘው፡፡ ውጤቱንም ለየትኛውም ይገባኛል ባይ ክልል ላለመደመር ወስኗል፡፡

ከወራት በፊት የሀገሪቱን ዐለም ዐቀፍ የውስጥ አከላለል የሚያሳዩ ሐሰተኛና አደገኛ ካርታዎች በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ቀርበው ይቅርታ የተጠየቀባቸው መሆኑ ወደፊት ምን ያህል አወዛጋቢ ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ የጠቆመ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ካርታዎች ሥራ ድርጅት በበኩሉ ለመላ ሀገሪቱ ያወጣው የመጨረሻ ኦፊሴላዊ ካርታ እንደሌለ መግለጹ ደሞ በራሱ ግርምት ፈጥሮ ነበር፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ሳይስተካከሉ ነው እንግዲህ አራተኛው ሀገር ዐቀፍ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ሊካሄድ የታቀደው፡፡

ቀደም ሲል በጸጥታ ሌሎች ምክንያቶች ወደ ኋላ የሚቀረው ሱማሌ ክልል ብቻ ሲሆን አሁን ከሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በዘንድሮው ቆጠራ በተለይ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎች እክል ሊያጋጥም እንደሚችል መገመት አይከበድም፡፡ በደንቡ መሰረት በሀገሪቱ ቆጠራውን ለማካሄድ የሚስችል አስተማማኝ ጸጥታ ከሌለ ፓርላማው ቀኑን እንዲያራዝምለት መጠየቅ የሚችለው ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ኮማንድ ፖስት እየተባለ የሚጠራው ማዕከላዊ ወታደራዊ ዕዝ ወይም በምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን የሚመራው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ኮሚሽን እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በርግጥ በመላ ሀገሪቱ ወይንም በአንዳንድ ከፊል ቦታዎች ብቻ የሚራዘም ከሆነ በኤጀንሲው ጥያቄ እንደተራዘመ ተደርጎ ሊገለጽ ይችል ይሆናል፡፡ [የድምፅ ዘገባ ከታች ያገኛሉ]

https://youtu.be/ULnKIRpzpBc