Hacking teamበቅርቡ ለኮምፒውተር ስለላ የሚውል ቴክኖሎጂ ሲያቀርብ የነበረው ሀኪንግ ቲም የራሱና የደንበኞቹ ሚስጥር ከተጋለጠ በኋላ የተማርናቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። መዝገቡ ሀይሉ ቢታሰብባቸው ያላቸውን የሀኪንግ ቲምን መረጃ ተንተርሶ ይነግራችኋል። አድምጡት

 

ብዙ የዓለማችን መንግስታት ዓለም አቀፍ ሽብርንና በኢንተርኔት መረብ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን መከላከል ዋነኛ የደኅንነታቸው ማረጋገጫ መንገድ እያደረጉት መጥተዋል። ለዚህም ተገባር እነዲረዳቸው ለኢንተርኔት ቁጥጥር ወይም ሰርቪላንስ የሚያገለግሉ ቴክኖሎጂዎችን የሚያመርቱ ኩባንያዎችን አገልግሎት ይጠቀማሉ። ይህም አገልግሎት በቢሊዮን የሚቆጠር የገቢ ምንጭ የሚያመጣ ኢንደስትሪ ወደመኾንም አድጓል።

ችግሩ ይህ ቴክኖሎጂ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት ካለባቸው አገሮች ውጪ ሲሰራበት የሚያስከትለውን አስከፊ ውጤት ለመገደብ አለመቻሉ ነው። እንደኢትዮጵያ ላሉ ሰብአዊ መብት ረጋጭ መንግስታት ይህን ቴክኖሎጂ አሳልፎ መስጠት አምባገነኑ መንግስታት በህዝባቸው ላይ ለሚያደርጉት ቁጥጥር አሉታዊ ውጤት የሚያስከትል ኃይል ይሰጣቸዋል።
ሰሞኑን በዓለም መገናኛ ብዙኃን ሳይቀር የመነጋገርያ ርእስ የነበረው የኢትዮጵያን የኢንተርኔት ስለላ ይደግፍ የነበረው የሃኪንግ ቲም መጋለጥ ጉዳይ ነበር። በተደረገበት የጠለፋ ወይም የ ሃኪንግ ጥቃት ምክንያት ከአገልግሎት ውጭ የኾነው ሃኪንግ ቲም ይደግፋቸው የነበሩት የልዩ ልዩ አገራት መንግስታዊ የስለላ ቡድኖች ትልቅ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በቆጵሮስ የኾነውን እንደምሳሌ ብንወስድ፤ ሰሞኑን በተጋለጠው መረጃ መሰረት ቆጵሮስ ለሃኪንግ ቲም በከፈለችው ፶ ሺህ ዩሮ ክፍያ የገዛችው የሃኪንግ ቲም ቴክኖሎጂ ከአገሪቱ ሕግ ጋር የሚጻረር ኾኖ መገኘቱ ባሰከተለው መዘዝ የቆጵሮስ የስለላ አገልግሎት ባለስልጣን ከስራቸው እንዲባረሩ ምክንያት ኾኑዋል። ለባለስልጣኑ መባረር ምክንያት የኾነውም እንዲህ ያለው በዜጎች ላይ የሚደረግ ስለላ የግለሰብን መብት የሚጋፋ ድርጊት ተደርጎ ስለሚቆጠርና የቆጵሮስም ሕግ ይህን መሰሉን በዜጎች ላይ የሚደረግ ስለላ መከልከሉ ነው።
በኢትዮጵያ የወቅቱ የፖለቲካ ኹኔታ እንዲህ ያለው ሕግም ኾነ ተጠያቂነት መኖሩ የሚታሰብ ጉዳይ እንኳን አይደለም። ለኢትዮጵያ መንግስትም ይህ መጋለጥ ሊያስከትለው የሚችለው ጉዳት ይተማመንበት የነበረውንና በሚሊዮኖች የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ ያፈሰሰበትን የመረጃ ምንጭ መነጠቁ ብቻ ይመስላል።
ይኹንና እንደ ኢትዮጵያው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ፤ በእንግሊዘኛው ምህጻረ ቃል ኢንሳ ጉዳቱ ያየለበት ያለ አይመስልም። ምክንያቱም ኢንሳ ከውጭ አገር በመንግስት ላይ የሰነዘራል ብሎ ለሚፈራው ጥቃት መፍትሄ ለማግኘት ይህንኑ ተቋም የሙጥኝ ያለበት መንገድ ከሌሎች አገሮች የስለላ ተቋማት ጋር ሲነጻጸር ጎልቶ መታየቱ ነው።
እስካሁን እየወጣ ባለው መረጃ መሰረት የ ኢንሳን ያህል ለጠላፊው ቡድን ገንዘብ የከፈለም ኾነ ተጻራሪዎቹን ለመያዝ ጥረት ያደረገ የስለላ ድርጅት አይታይም። በተለይም የኢትዮጵያ መንግስት ዋነኛ ስጋቱ አድርጎ የሚቆጥረው ግንቦት ሰባት የመሳርያ ጥቃት መፈጸም በጀመረበት በዚህ ወቅት ይህን አይነት የመረጃ ክፍተት ሲያጋጥመው ተልቅ ጉዳት ሊኾንበት እነደሚችል መገመት የሚያዳግት አይደለም። አሁን ከተጠለፉት የኢንሳና የሃኪንግ ቲም የኢሜይል ልውውጦች ላይ እንደሚታየው መንግስት ዋነኛ የጥቃቱ ዒላማ ያደረገው ይህንኑ ግንቦት ሰባትን እንደነበረ ግልጽ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ከተጋለጡበት ምስጢሮቹ የተነሳ ከዚህ በሁዋላ ድምበር ዘለል የኢንተርኔት ስለላ ለማኪያሄድ የሚያደርገው ሙከራ ቀላል ባይኾንለትም፤ መዘንጋት የሌለብን በሰብአዊ መብት ተምዋጋቾች ዘንድ የኢንተረኔት ነጻነት ጠላቶች ተብለው የሚታወቁ ለሎች ሃኪንግ ቲምን የመሰሉ የኢንተረኔት ስለላ ደጋፍ የሚያደርጉ ቅጥር ድርጅቶች መኖራቸውንም ነው። የኢትዮጵያ መነግስት የሚያደርገው የኢንተርኔት ስለላ ሲጋለጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከዚህ በፊትም ጋማ ግሩፕ ተብሎ በሚታወቅ የእንግሊዝ ኩባንያ የተሰራ ፊን ፊሸር የተባለ የስለላ ሶፍት ዌር መጠቀሙ ተደርሶበት ነበር። እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን የመሰሉ ለሎችን ድርጅቶችንም አለመጠቀሙን ርግጠኛ ለመኾን አይቻልም። ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ መነግስት የዓለም አቀፉ ጸረሽብር ውጊያ አጋር ተደርጎ መቆጠሩ የሚያስገኝለት መንግስታዊ ድጋፍ መኖሩን ማስታወስም ይበጃል።
አሁን ይፋ በኾነው መረጃ ላይ እንደሚታየው አንድ እስራኤላዊ ኩባንያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተመሳሳይ ግንኙነት ነበረው። ይህ በስም ያልተገለጸ የእራኤል ኩባንያ ለኢትዮጵያ መንግስት ያደርገው የነበረው ድጋፍ ግልጽ ባይኾንም ሃኪንግ ቲም ለኢትዮጵያ መንግስት ይሸጠው ከነበረው አገልግሎት ጋር በብዛትም ኾነ በጥራት ተመሳሳይነት ያለው አይመስልም።
ሃኪንግ ቲም በመጀመሪያ ከኢንሳ ጋር እንዲገናኝ የማቀራረቡን ሚና የተጫወተው ናይስ በሚል ምሕጻረ ቃል የሚጠራ ሌላ የእስራኤል ኩባንያ ነው። ናይስ ራሱን የቻለ የኢንተርኔት ወንጀሎችን የመከላከል አማካሪ ድርጅት አድርጎ ቢያስተዋውቅም አሁን በወጣው መረጃ መሰረት የሃኪንግ ቲምን ቴክኖሎጂ ኢንሳን ለመሰሉ የተለያዩ አገራት የስለላ ድርጅቶች የማሻሻጥ ስራንም ደርቦ ይሰራል።
እስካሁን ከወጡት መርጃዎች መካከል በጣም አስፈላጊ የኾኑ ብዙ ዶክመንቶች ይገኙባቸዋል። ከነዚህም መካከል ኢንሳ እስካሁን ሲጠቀምባቸው የነበሩትን የጠለፋ ስልቶች የሚጠቁሙት የስልጠና ሪፖርቶች ተጠቃሽ ናቸው። የኢንሳ ስለላ ብዙ እውቀት የጎደለው ቢኾንም በገንዘብ ብዛት በተገዙ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የታጠቀውን ቴክኖሎጂ ምን ሲያደርግበት እንደቆየ መረዳት ይቻላል። ይህም መታወቁ ከዚህ ሁዋላ ይህን የመሰለ ጥቃት ለመሰንዘር ቢሞክር እንዴት መከላከል እንደሚቻል ፍንጭ ከመስጠቱም በላይ አሁን ባለው መረጃ ላይ ተመስርቶ በራሱ በኢንሳ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችል ሙከራ ቢደረግም ኢንሳን ከአጥቂነት ወደ ተጠቂነት የሚለውጥ የመልስ ምት ሊያመጣበት ይችላል።
የኢንሳ ሰራተኞች አንድ ጊዜ በአዲስ አበባ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሚላን ስልጠና መውሰዳቸውም መረጃዎቹ ይጠቁማሉ። ሪፖርቱ ከተገኘው ሃኪንግ ቲም ለኢንሳ የሰጠው ስልጠና ይዘት ለመረዳት እንደሚቻለው ኢንሳ ጠለፋውን ያኪያሂድበት የነበረው መንገድ በመገለጹ ጥንቃቄ የሚያሻው መረጃ ያላቸው ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተምዋጋቾች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ብሁዋላ ከኢንሳ ጥቃት እንዳይሰነዘርባቸው የኢንተርኔት እና የስልክ ግንኙነቶቻቸውን እንዴት ባለ ጥንቃቄ መጠበቅ እንደሚችሉም ፍንጭ ይሰጣል።
በሃኪንግ ቲም ከተሰጣቸው አንዱ ስልጠና ለመረዳት እንደሚቻለው የኢንሳ ጠላፊዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩት ቴክኖሎጂዎች ተዘርዝረው ቀርበዋል። በካይ የኢሜይል መልእክቶቻቸውን ለማሰራጨት ታንደር በርድ እና ጃንጎ ኤስ ፒ ቲ ኤም ሶፍት ዌሮችን እንዲጠቀሙ ከመመከራቸውም በላይ የኢሜይል መልእክት ርእሶቻቸውን ተቀባይነት ያላቸው ለማድረግ ኤም ኤክስ ቱል ቦክስ የተሰኘውንም ሶፍትዌር መጠቀም የሚያስችል ስልጠና ተሰጥቱዋቸዋል።
ባብዛኛው የስልጠና ይዘቶቹ የተዘጋጁትም የኢንተርኔት እውቀት ላልዘለቃቸው ተጠቃሚዎች የእጅ መፍቻ እንዲኾኑ ታስበው ነው። ይጠቀሙባቸው ከነበሩት ሶፍትዌሮች መካከልም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ርስበርሳቸው ያላቸውን ግንኙነት ለመተንተን ያሚያስችለው ማልቴጎ የሚባለው የስለላ ሶፍትዌርም ቢኾን ጥቂት ጊዜውን በሰጠ ማንኛውም ሰው ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል መገልገያ ነው።
እነኚህ ምስጢሮች ይፋ መውጣታቸውና የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጉ የነበሩትም ድርጅቶች እጃቸውን መሰብሰባቸው ለኢትዮጵያ መንግስት ድምበር ዘለል የስለላ ስራ ትልቅ ጉዳት ቢኾንበትም አሁንም ቢኾን እነኚህን ማንም ሰው በቀላሉ ሊጠቀምባቸው የሚያስችሉ ሶፍትዌሮች በመጠቀም በተለይ በአገር ውስጥ ባሉ ዒላማዎች ላይ ስለላውን ከመቀጠል የሚያግደው ነገር ቢኖር ምናልባት የእውቀት ማነስ ብቻ ሊኾን ይችላል።
በመኾኑም በቀላሉ ይታዩ የነበሩ የኢንተርኔት ደኅንነት ስልጠናዎች ከምንጊዜውም ይልቅ አሁን በትኩረት ሊጤኑ የሚገባበት ጊዜ ኾኑዋል። ጥንቃቄ የሚያሻው መረጃ ያላቸው ግለሰቦች ና ድርጅቶች አጥራቸውን ማጠባበቃቸው ከዚህ አጋጣሚ በሁዋላ የሚጠበቅ ውጤት ይኾናል።