ዋዜማ ራዲዮ- በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አጠቃላይ የማሻሻያ ስራ ላይ እየተከናወኑ ያሉ የጥናት ስራዎችን እያከናወነ የሚገኘው የሰላም ሚኒስቴር ባስጠናው ጥናት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ‘’የፌደራል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መመሪያ’’ የሚል ስያሜ እንዲኖረው ሀሳብ ቀርቧል። ።

በክልል ደረጃ የሚደራጁ የፖሊስ ኮሚሽኖች ደግሞ አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው በየክልሉ ስያሜ በጠቅላይ መመሪያ ደረጃ እንዲደራጁ ታስቧል።

በዚህ መሰረትም የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ወደ አማራ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ስያሜያቸው እንዲቀየር ሌሎችም የክልል ፖሊስ ኮሚሽን አደረጃጀት በዚህ መልኩ እንዲደራጅ የሚያደርግ ጥናት መቅረቡን ነው ዋዜማ የተረዳችው።

አጠቃላይ የፌደራልና የክልል ፖሊስ አደረጃጀትን የሚገልፀውን ዘገባ እዚህ ያንብቡ። የልዩ ፖሊስ ሀይል ጉዳይስ?

በጥናቱ እንደተመላከተው በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና በክልሎች የፖሊስ ኮሚሽኖች መካከል ያለው የተጠሪነት የተዋረድ ስልጣን ሃላፊነት በሀገሪቱ እየተስተዋሉ ላሉ የፀጥታ መደፍረስ እና ህግን የማስከበር እንቅስቃሴ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ በጥናቱ እንደ መሰረታዊ ችግር ቀርቧል።።

በሰላም ሚኒስቴር በኩል ተዘጋጅቶ ለውይይት ሊቀርብ በተሰናዳው የኢትዮጵያ ፖሊስ ዶክትሪን ላይ በግልፅ እንደሰፈረው ‘’ የፖሊስ ተልዕኮ በዋነኛነት ከዜጎች ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጋር እጅግ የተቆራኘ በመሆኑ ከሁሉ በፊት ውስጣዊና ውጫዊ የአደረጃጀት ስርአቱ በግልፅ አሰራርና ፍልስፍና መገንባት አለበት፡” ይላል።

አስከትሎም በገፅ 23 “ የፖሊስ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በግልፅ የአደረጃጀት ስርዓት ካልተደራጁ የስራ ወይም የኃላፊነት ግጭት እና የፍላጎት ወይም የጥቅሞች ግጭት በመፍጠር የተሰጣቸውን ተልዕኮ እና የተቋቋሙበትን አላማ በመሳት ላልተፈለገ ግጭትና መስዋዕትነት ይዳረጋሉ’’ ሲል ደምድሟል።

የፌደራል እና የክልል ፖሊስ ኮሚሽን አደረጃጀት እስከዛሬ በኮሚሽን የአደረጃጀት መጠሪያ በተመሳሳይ ቅርፅ መደራጀታቸው መመሪያዎችን እና ተልእኮዎችን በመቀበል ደረጃ ችግር ሆኖ መቆየቱንም ነው ይህ የውይይት ሰነድ የሚያወሳው።

ለዚህም ይመስላል በአዲሱ አወቃቀር የክልል ፖሊስ ኮሚሽን ወይም በአዲሱ መጠሪያ የክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የስልጣን ወሰንን ሰፍሮ ለመስጠት የታሰበው።

የክልልና የፌደራል ፖሊስ ስልጣን ወሰን

የፖሊስ አደረጃጀት ፍልስፍና የፌዴራል ስርዓቱን ቅርፅ እንደሚከተል ይገልፅና ‘’በፌዴራል ደረጃ የሚኖር የፖሊስ አደረጃጀት የሚኖረው ስልጣን በዋነኛነት ለፌዴራል ፍ/ቤቶች የተሰጡ የስልጣን ወሰኖችን መሰረት የሚደርግ ሲሆን የክልል ፖሊስ ስልጣንም ምንጩ ለክልል ፍ/ቤቶች በተሰጡ ስልጣን ወሰኖች ውስጥ ሆኖ ከየስራ ክፍሎቹ ለየት ያለ ባህርይና ተልዕኮ ጋር የተገናኘ ነው’’ ሲልም ይዘረዝራል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ከአስተዳደር ክልል ወሰን የተሻገረ የጋራ ወንጀልን የመቆጣጠር የተዋረድ የጋራ ስራ ብዙ መሳናክሎች የነበረበት በመሆኑም ይህንን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ግልፅ አሰራር ማስቀመጥ መፍትሄ መሆኑንም ይጠቁማል።

‘’በህገ መንግስቱ ለፌዴራልና ለክልል መስተዳድሮች ተለይተው የተሰጡ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው ፖሊሳዊ ተልዕኮ በባህሪው ድንበር አልባ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የጋራ መግባቢያ ሰነድ በማዘጋጀት እና የህግ ድጋፍ እንዲኖረው በማድረግ በትብብርና በአጋርነት መፈፀም አለበት፡፡’’ ሲልም አፅንኦት ይሰጣል

የዚህ የተጠሪነት ወይም የስልጣን ተዋረድ አስፈላጊነት ክልሎች ባላቸው የፖሊስ ኮሚሽን አደረጃጀት ምክንያት ከማአከል ጋር ያለው አልያም ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንደ ሀገር የጋራ ራእይ ሰንቆ ለጋራ የደህንነት መረጋገጥ ከመንቀሳቀስ ይልቅ በክልሎች የመታጠር ውሱንነት በመስተዋሉ መሆኑን የሚያብራራው ጥናቱ ይህንን ችግር ለመፍታት ያለመ የአደረጃጀት ክለሳ ስለመሆኑም ይጠቁማል።

የፖሊስ የአደረጃጀት መዋቅሩን “ኮሚሽን” ከሚለው ስያሜ ወደ “ጠቅላይ መምሪያ” ስያሜ ለመቀየር አስፈላጊ ከሆኑ መነሻዎች መካከል ለፌደራልና ለክልል በህግ በተሰጡ ህገ መንግስታዊ ተልእኮዎች መነሻነት መሆኑን የሚያብራራው ይህ ሰነድ ሌላው ዓቢይ ምከንያት ደግሞ ‘’የፖሊስ አደረጃጀት አጠቃላይ ዓላማና ግብ ኢትዮጵያዊ የሆነ የፖሊስ ተቋምን በመገንባት ላይ ያተኮረ ሆኖ የአደረጃጀቱ ቅርፅና ይዘቱ የፌዴራል አወቃቀሩን የተከተለ ይሆናል’’ ሲል ተቋሙንም ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዋህዶ ይበልጥ መልክ ማስያዝም እንደሚያስፈልግ ይገልጻል።

ከተቋሙ መጠሪያ ስም ለውጥ ባሻገር ከዚህ ቀደም በፖሊስ አገልግሎት ውስጥ ይሰጡ የነበሩ የማዕረግ መጠሪያዎች ጭምር ሀገራዊ ለማድረግም የሚያስችል ጥናት መቅረቡን ነው ዋዜማ ከምንጮቿ የሰማችው። [ዋዜማ ራዲዮ]