mimi sibhatu
Mimi Sibhatu-FILE

ዋዜማ ራዲዮ-በመንግሥት የስለላ መዋቅር በሕቡዕ ይደገፋሉ የሚባሉት የዛሚ ሬዲዮና ኢኤንኤን ቴሌቭዥን ትናንት ከኦሮሚያ አመጽ ጋር በተያያዘ ያስተሏለፏቸው ስርጭቶችን ተከትሎ ከአድማጭ ተመልካች ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ነው ተባለ፡፡ ‹‹ከጠዋት ጀምሮ የስልክ ዛቻው ከሚገመተው በላይ ስለሆነ ከለላ እንዲሰጥ ተጠይቋል›› ትላለች አምባሳደር አካባቢ በሚገኘው ዛሚ ሬዲዮ ጣቢያ የምትሠራ ነባር ጋዜጠኛ፡፡ ‹‹ስልኩ ለደቂቃ አላረፈም፤ በጣም ብዙ ሰው ነበር እየደወለ የነበረው፤ በጣም ብዙ…›› ብላለች የጣቢያው ባልደረባ፡፡ የስልክ ጥሪዎቹ በአመዛኙ ጣቢያዉን በዘር ፍጅት ቅስቀሳ የሚወነጅሉ ናቸው፡፡
ዋዜማ አዲስ አበባ የሚገኙ የሁለቱን ጣቢያ ኃላፊዎች በስልክ ጠይቃ ስለጉዳዩ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ተረድታለች፡፡ ኾኖም ከጣቢያው ሠራተኞችና ሌሎች ታማኝ ምንጮች ባገኘችው መረጃ መሠረት ዛሬ ከረፋድ ጀምሮ ከቅጥር ጊቤያቸው ዙርያ ጥበቃ የሚያደርጉ ፖሊሶች መመደባቸውን አረጋግጣለች፡፡
ትናንት ማምሻውን የዛሚ ሬዲዮ ‹‹የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ›› በቀድሞው አጠራር ኢሊባቡር አካባቢ (ቡኖ በደሌ ዞን ዴጋ፣ መኮና ጮራ ወረዳዎች) በትግራይና አማራ ተወላጆች ዘንድ ደርሷል በተባለ ብሄርን ያማከለ ጥቃት ዙርያ ሁለቱ ጣቢያዎች የሠሯቸውን ዘገባዎች ተከትሎ የኦሮሚያ መንግሥት ቅሬታውን ማሰማቱ ይታወሳል፡፡
ወይዘሮ ሚሚ ስብሐቱ ከአቶ ፍጹም ብርሃኔ ጋር ባደረጉት የትናንቱ ‹‹የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ›› ውይይት የሥራ መልቀቂያ ያስገቡትን አቶ አባዱላ ገመዳን ባልተለመደ ሁኔታ ለግጭቶች መባባስ አንድ ምክንያት ናቸው ሲሉ የሰላ ትችት ሰንዝረውባቸዋል፡፡
‹‹የአቶ አባዱላ ንግግር ለአመጽና ሁከት ግብአት ነው፣ …አመጽና ሁከት ለማስቀጠል ለሚፈልጉ ወገኖች መልዕክት የማስተላለፍ ያህል ነው፡፡ …ሕዝብን ክብሬ ተነካ ማለት ተነስ ማለት ነው…ሌላ ምንም ማለት አይደለም፡፡››ሲሉ አፈጉባኤውን የተቹት ወይዘሮ ሚሚ ስብሐቱ ምናልባት በአቶ አባዱላ ላይ በዚህ ደረጃ የሰላ ትችት መሰንዘራቸው ሰውየው ላይ በቀጣይ የሚወሰዱ ፖለቲካዊ እርምጃዎች ይኖሩ ይሆን የሚሉ መላምቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነዋል፡፡
ወይዘሮ ሚሚ አክለው በአቶ አባዱላ ላይ በሰነዘሩት አስተያየት ‹‹…26 አመት ውስጥ በዚህ ድርጅት የኖሩ ናቸው፤ በተለይም ኦፒዲኦ የሚባለው ድርጅት የመሠረቱ ናቸው፡፡ ለረዥም ጊዜ ከጠባቦች ጋር የታገሉ ናቸው…፡፡››ሲሉ አፈጉባኤውን ካሞገሷቸው በኋላ ስማቸውን ከሙስና ጋር ለማስተሳሰር ሞክረዋል፡፡ ‹‹…እንደዚያ ቢሆንም ደግሞ በከፍተኛ ደረጃም ደግሞ የምናውቀው ነው፣ ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው ብዬ ነበር ባለፈው ጊዜም…በከፍተኛ ደረጃ ደግሞ ስማቸው በጥሩ የማይነሳባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ…፡፡ ሲሉ አቶ አባዱላን በሾርኔ ለመንካት ሞክረዋል፡፡
‹‹…ይሄ ኃላፊነት የጎደለው ንግግር ነው፡፡ የሕዝብ ክብር እንዴት ነው የተነካው? በምንድነው የተነካው? የሳቸው ክብር ነው የተነካው? ምንድነው እሳቸው ራሳቸውን እንደ ሕዝብ ነው እንዴ የሚመለከቱት?›› ሲሉም ወይዘሮዋ በአቶ አባዱላ ላይ ለማፌዝ ሲሞክሩ ነበር፣ በትናንቱ የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ ኢኤንኤን ቴሌቭዥን የኢትዮጵያ ቡናና የቅዱስ ጊዮርጊስን ጨዋታ በቀጥታ ሥርጭት አቋርጦ በሰበር ዜና ያቀረበው ዘገባ ‹‹በተዛባና ሐሰት በሆነ ሁኔታ ነው›› ሲሉ ያጣጣሉት የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በተመሳሳይ የዛሚ ጣቢያንም ወቅሰዋል፡፡ ጣቢያዎቹ ‹‹ግጭቱን ሊያባብሱ የሚችሉ ዘገባዎችን ከመስራት እንዲቆጠቡ›› ካሳሰቡ በኋላ ‹‹ካልሆነም ወደፊት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እናደርጋለን›› ሲሉ ለኢቢሲ የምሽት ዜና ክፍለ ጊዜ ተናግረዋል፡፡
በመንግሥትና ክልል የፖለቲካ መዋቅር በዚህ ደረጃ እርስበርስ መወነዳጀል የተለመደ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የኢህአዴግ ማእከላዊ አስተዳደር እየላላ ስለመሆኑ የሚናገሩ አልጠፉም፡፡
በቡኖ በደሌ ዞን ዴጋ፣ መኮና ጮራ ወረዳዎች በተፈጠረው ግጭት ከፍተኛ ውድመት ከደረሰ በኋላ ማምሻውን ከአካባቢው ሽማግሌዎች ጋር በተደረገ ጥረት መርገቡ እየተነገረ ነው፡፡