Credit-Melody Sundberg
Temesgen Desalegn, Credit-Melody Sundberg

በዝዋይ እስር ቤት የታጎረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዛሬ 37ኛ ዓመቱን ደፍኗል፡፡ ልደቱን አስመልክተው ወዳጆቹ፣ ቤተሰቦቹና አድናቂዎቹ የልደት ቀኑን በማስመልከት መለስተኛ ዝግጅት ለማሰናዳት ላይ ታች ሲሉ ቢከርሙም አልተሳካላቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎቹ ሆቴሎቹ አዳራሻቸውን ከፈቀዱ በኋላ የተመስገን ዳሳለኝ ልደት መሆኑን ሲረዱ ‹‹እባካችሁ ችግር ዉስጥ ትጥሉናላችሁ›› በሚል ፍቃደኝነታቸውን መሰረዛቸው ነው የተነገረው፡፡

በስተመጨረሻ አንድ ጣይቱ ሆቴል አካባቢ በሚገኝ መለስተኛ ሬስቶራንት ጓሮ የጋዜጠኛው ልደት ተከብሮለታል፡፡
ከምሽቱ 12›00 ሰዓት ላይ የጀመረው አጭር ዝግጅት እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ዘልቆ የቆየ ሲሆን ወዳጆቹ፣ የሥራ ባልደረቦቹና ወላጅ እናቱ አጭር የማስታወሻ ንግግር አድርገዉለታል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ተመስገን ደሳለኝ በበጎ ፍቃደኝነት ያሳደጋቸው ሁለት ሕጻናት በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን ዝግጅቱን እንደሚታደሙ ተገልጾ የነበረው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ግን ባልታወቀ ምክንያት ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡

የልደት ኬኩን የቆረሱት ወላጅ እናቱና የጋዜጠኛ ርዕዮት አባት አቶ አለሙ በጋራ በመሆን ሲሆን ሁለቱም ባሰሙት አጭር ንግግር ጋዜጠኛ ተመስገንን ‹‹ላመነበት ሀሳብ እስከመጨረሻው የቆመ ወጣት›› ሲሉ አወድሰዉታል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የጋዜጠኛ ተመስገን ሁለት ወንድሞቹን ጨምሮ ከ20 የማይበልጡ ግለሰቦች ብቻ ታድመውታል፡፡ ይህንኑ አስመልክተው ጓደኛውና የሥራ ባልደረባው የነበሩት ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ባሰሙት ንግግር ‹‹አንድ ማኅበረሰብ ዉስጥ ራሳቸውን ትተው ለብዙኃኑ የሚቆሙ ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ ተመስገን አንዱ ነው፡፡ እነዚህን የሚዘክሩም በቁጥር ብዙ አይደሉም…ተመስገንን የመሰሉ ዜጎች ሲበዙ ለውጥ አይቀሬ ነው፡፡ በዘመኑ እንደ ተመስገን ያሉ ሰዎችን የሚኖሩት በጥቂቱ ነው፡፡ ልንዘክረው ይገባል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሌላው በዝጅግቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የቀድሞው የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ ባሰሙት አጭር ንግግር ‹‹ተመስገን አንድ ራሱን የቻለ ፓርቲ ነው ማለት ይቻላል›› ሲሉ ያወደሱት ሲሆን እንግሊዝ ለፓርቲ ሥራ ሄደው በአንድ አዳራሽ ዉስጥ ያጋጠማቸውን የአንድ ሰው አስተያየት ለታዳሚው አጋርተዋል፡፡ ይህ ግለሰብ ኢትዮጵያ መጥቶ ያየነው በአዳራሹ ሲያጋራ ‹‹እናንተ ፓርቲ ፓርቲ ትላላችሁ፣ እኔ አገር ቤት ሄጄ ያየሁትና ሕዝቡም የሚያውቀው አንድ ተመስገንን ነው›› ሲል መናገሩን አስታውሰው ተመስገን የፈጠረውን አልሸነፍ ባይነት ከአንድ ፓርቲ በላይ እንደነበር አውስተዋል፡፡

የግል ጓደኛውና ፀሐፊ ተውኔት አቶ መስፍን ጌታቸው በበኩላቸው ‹‹ የልጁን ልድት ጓሮ ዉስጥ እንዲህ ተወሽቀን ማክበራችን ያስቆጨኛል፡፡ ባለኝ መረጃ ትልልቅ ሆቴሎች የተመስገን ልደት በአዳራሻቸው እንዲከበር አለመፍቀዳቸው የሚነግረኝ ሁለት ነገር ነው፤ አንድም ፍርሃታችን ተለጥጦ የት እንደደረሰ፣ ሁለትም በጠላትነት መታየየታችን ከዕለት ዕለት እየበረታ አንደሄደ ነው፡፡ ሁላችንም የተመስገንን አርአያ ተከትለን ለምናምንበት ነገር ብንቆም እንዴት ጥሩ ነበር፡፡ ለማንኛውም መልካም የእስር ጊዜ እንዲሆንለት እመኛለሁ፡፡›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ ከእስር የተፈቱት አቶ ሀብታሙ አያሌው በበኩላቸው ‹‹እኔ ለረዥም ጊዜ ከአሳሪዎች ወገን ስለነበርኩ ስለ እስር ብዙ ግንዛቤ አልነበረኝም፡፡ እስር ካልተራዘመ መማሪያ ይሆናል፡፡ እኔም ሂሳቤን ያወራረድኩ ይመስለኛል›› ካሉ በኋላ ‹‹መታሰሩን የሰማሁት ማዕከላዊ በድብደባ ላይ ሳለሁ ነበር፡፡ እውነቱን ለመናገር የሱን መታሰር ስሰማ ደብዳቤዎቼ ካደረሱብኝ ህመም በላይ ነበር የተሰማኝ፣ የሱን መታሰር ስሰማ ከፍተኛ ድብታና ተስፋ መቁረጥ ዉስጥ ገብቼ እንደነበር አልሸሽጋችሁም፡፡ ፍርድ ቤት ሲፈረድበትና ፖሊሶች ፍርግርግ ብረት ዉስጥ አስገብተው ሲቆልፉበት እኔ አዚያው ነበርኩ፡፡ አልቅሻለሁ፡፡ ብዙ ጊዜዬን ከአሳሪዎች ወገን ስለነበርኩ የመታሰርን ሕመም ያን ያህል አልተረዳሁም ነበር፡፡ አሁን ግን ልምድ አግኝቻለሁ›› ሲሉ ለታዳሚው ተናግረዋል፡፡

ፍትህ፣ አዲስ ታይምስ፣ ልዕልና፣ በመጨረሻም ፋክት በተሰኙ መጽሔትና ጋዜጦች ለአመታት ሕትመት ሚዲያው ላይ የቆየው ተመስገን ደሳለኝ በጻፋቸው ጽሑፎች ምክንያት  እስር የተፈረደበት ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከአዲስ አበባ 165 ኪሎ ሜትር ላይ ርቃ በምትገኘው በዝዋይ እስር ቤት ታስሮ ይገኛል፡፡ በእስር ላይ በደረሰበት ድብደባና እንግልት ጤናው ከእለት እለት እያሽቆለቆለ ሲሆን የግራ ጆሮው መግል እያዠ የመስማት አቅሙም እየተዳከመ መሄዱን ቤተሰቦቹ ይናገራሉ፡፡ አሳሪዎቹ ሐኪም እንዲያየው ባለመፍቀዳቸው ችግሩ እየተባባሰ ሄዶ በአሁነ ሰዓት የሰው ድምጽ ለመስማት አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ከመሆኑም በላይ በወገብ ህመም እየተሰቃየ እንደሆነ ወንድሞቹ ለዋዜማ ምንጮች አስረድተዋል፡፡