Sileshi Bekele (PhD) Chief Negotiator of GERD- Photo AP/File
  • ድርድሩ ሳይጠናቀቅ የውሀ ሙሌቱ እንዳይጀመር አሜሪካ በድጋሚ አሳስባለች
  • ግብፅና ሱዳን በኢትዮጵያ የቀረበውን የድርድር ምክረ ሀሳብ አልተቀበሉም
  • “ወደ ድርድሩ መመለስ የለብንም” የድርድሩ ቡድን አባላት

ዋዜማ ራዲዮ- በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ረገብ ብሎ የሰነበተው የሕዳሴው ግድብ የውሀ ሙሌትና አለቃቀቅ ድርድር የበለጠ ወደ ተወሳሰበ የዲፕሎማሲ ጥልፍልፍ ውስጥ እየገባ ነው።

ግብፅና ሱዳን በኢትዮጵያ በኩል የቀረበውን የመደራደሪያ ምክር ሀሳብ አንቀበልም በማለት ውድቅ አድርገውታል። ።

ግብፅ የዲፕሎማሲ ጥረቷን የበለጠ በማጠናከር ጉዳዩ ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የወሰደች ሲሆን አሜሪካ ድርድሩን በአስቸኳይ አስቀጥላ ኢትዮጵያ በአሜሪካ የቀረበውን ስነድ እንድታስፈርም ጠይቃለች።

ግብፅ አንደምትለው ኢትዮጵያ ስምምነቱ ሳይፈረም የግድቡን ውሀ መሙላት ብትጀመር በቀጠናው የከፋ አለመረጋጋት ይከሰታል።

ይህ ጉዳይ ያሳሰባቸው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ስልክ ደውለው የመንግስታቱ ድርጅት ለጉዳዩ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግለት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ስምምነት ሳይፈረም የግድቡ የውሀ ሙሌት እንዳይጀመርና ባለድርሻዎቹ ሀገራት በቶሎ ወደ ድርድር እንዲመለሱ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ በኩል የተዘጋጀው የድርድር ምክረ ሀሳብ

ሰነዱ 9 ገጾች ያሉት ሰሆን በመጀመርያው ላይ ጠቅላላ ጉዳዮችን አንስቶ ቀጥሎ ኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብን እንዴት እንደምትሞላ ያብራራል። የመጀመርያው ደረጃ ሙሌት በሁለት አመት የሚከናወን ሲሆን በመጀመርያው አመት 4.9 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ይይዛል ይላል።በቀጣይ አመት ደግሞ 13.5 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ በጥቅሉ 18.4 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀን ግድቡ ይይዛል ይላል። ይህም የውሀውን ደረጃ ከግድቡ 595 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ያደርሰዋልም ሲል ሰነዱ ይገልጻል።

ይህም ግድቡ በመጀመርያ ደረጃ ሙሌቱ የመጀመርያው አመት ላይ 4.9 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ከያዘ በሁዋላ በሁለተኛው አመት ወደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚደርሰው ውሀ በዝናብ እጥረት ወይንም በድርቅ ምክንያት ከ31 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ በታች ከሆነ ሙሌቱ አይከናወንም የሚል ነው። ድርቅን ሲገልጽ በኢትዮጵያ የሚከሰተውን ድርቅ ብሎ መጥቀሱ ከዚህ ቀደም ከነበሩ አቋሞች መሻሻልን አሳይቷል ።

የሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሀ ሙሌት ግድቡ የሚይዘውን ውሀ 49.3 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ እንደሚያደርሰው የውሀ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ በተደጋጋሚ ሲያብራሩ ነበር። የተያዘው ውሀ 49.3 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ እንዲደርስ ወይንም የግድብን ከባህር ጠለል በላይ 625 ሜትር ላይ እንዲደርስ በመጀመርያ ሙሌት ላይ ከወሰደው ሁለት አመት በተጨማሪ ከሁለት እስከ አምስት አመት ይወስዳልም ይላል።

በሰነዱ መሰረት ሁለተኛ ደረጃ ሙሌት ላይ ግድቡ የሚይዘው ውሀ 49.3 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ እንዲደርስ ተጨማሪ 30.9 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ መያዝ ነው የሚጠበቅበት። ለ30.9 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ተጨማሪ ከሁለት እስከ አምስት አመት ካስፈለገ ግድቡ በሁለተኛው የሙሌት ደረጃ በአማካይ በየአመቱ 6 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ነው የሚይዘው ማለት ነው። ይሄ ሰነድ የህዳሴው ግድብ በጥቅሉ በሰባት አመት 49.3 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ እንጂ ከዚህ ቀደም እንደተገለፀው በሙሉ አቅሙ ይይዛል የተባለውን 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ እንደማይዝ በተዘዋዋሪ መልኩ ነግሮናል።

ከዚህ በፊት የህዳሴው ግድብ መያዝ የሚችለውን 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ለመሙላት ከአራት እስከ ሰባት አመት ይወስዳል ሲባል ቢቆይም በተዘጋጀው ሰነድ መሰረት ግድቡ ሙሉ ለሙሉ 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ለመያዝ (ቀሪውን 25 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ለመያዝ ተመሳሳይ አመታዊ አማካይ ስሌት ጥቅም ላይ ከዋለ) የሚያስፈልገው ጊዜ ሲሰላ ከ10 አመት በላይ ሊወስድ ይችላል።

ይህ ሰነድ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ፍላጎት ለመመለስ ያለመና የተለሳለስ ቢሆንም ግብፅና ሱዳን ግን እቅዱን ሳይቀበሉት ቀርተዋል። ሱዳን ከአሜሪካ በኩል የሚደርስባት ጫናን በመፍራት በዋሽንግተን የቀረበው ሰነድ ላይ ተስማምተን እንፈርም የሚል አቋም አላት።

ግብፅ ከውሀ አለቃቀቅና አሞላል ጋር በተያያዘ በቁጥር የተደገፈ ማረጋገጫ እንዲሰጣትና ይህንንም ለመከታተል በግድቡ አስተዳደር ውስጥ ተሳትፎ እንዲኖራት ትፈልጋለች።

ወደ ዋሽንግተኑ ድርድር እንመለሳለን?

በኢትዮጵያ በኩል በድጋሚ ወደ ዋሽንግተኑ ድርድር መሄድ የለብንም፣ ላልተፈለገ ጫናና ውዝግብ ይዳርገናል የሚሉ የድርድር ቡድኑ አባላት መኖራቸውን ስምተናል።

“ድርድሩን አንዴ ጀምረነዋል ሙሉ በሙሉ ጥለን መውጣት ጥሩ ውሳኔ አይደለም ባይሆን የመደራደሪያ ነጥቦቻችን ጥቅማችንን ባስከበረ መልኩ አሸናፊ ሆነው እንዲወጡ እንረባረብ” የሚል አቋም አመዝኖ ታይቷል።

የሕዳሴው ግድብን በተመለከተ ሁለቱ ተደራዳሪ ተቋማት ማለትም የውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲሆኑ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀድሞ የነበረው የመሪነት ሚና ዝቅ ብሎ ድርድሩ በውሀ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ መሪነት እንዲካሄድ መደረጉ ሊታስብበት የሚገባ መሆኑን የነገሩን የውጪ ጉዳይ ባለስልጣናት አሉ።

ጉዳዩ ብዙ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ስለያዘ በውሀ ሚኒስትሩ መመራቱ ተገቢ መሆኑን የሚያምኑ የድርድሩ አባላት ባይሆን ለድርድሩ አሁን እየተሳተፉ ካሉት በተጨማሪ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎች ቢጨመሩ አስፈላጊ ነው።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ገዱ አንዳርጋቸው በዋሽንግተን በተደረገው ድርድር ላይ ተሳትፈው የነበረ ሲሆን አንድም በድርድሩ ከጅምሩ ስላልነበሩ አንዲሁም በዲፕሎማሲ ዘርፍ ካላቸው ውስን ልምድ የተነሳ የመሪነት ሚና ከመጫወት ይልቅ የሀገር ጥቅም የሚጎዳ ስምምነት አካል ላለመሆን ሲጠነቀቁ እንደነበር የቅርብ ምንጮቻችን ነግረውናል። ድርድሩ እንዲቋረጥ የተደረገውም በአቶ ገዱ “ይህን ጉዳይ እናዘግየው” የሚል ውሳኔ መሆኑ ይታወሳል።

የተደራዳሪዎች ቅሬታ

በድርድሩ አመራርና ይዘት ላይ ስጋት አለን ያሉ ሶስት የቡድኑ አባላት ስጋታቸውንና ቅሬታቸውን ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በደብዳቤ ያሳወቁና በቀጣይ ድርድር ላይሳተፉ እንደሚችሉ አሳውቀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ቅሬታውን ተከትሎ በሙያ የውሀ መሀንዲስ የሆኑትን የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ይፋዊ ባልሆነ መልኩ በጉዳዩ ላይ ሚና እንዲጫወቱ እያደረጉ መሆኑን ተገንዝበናል። እንዲሁም የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የደህንነት አማካሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ በሕዳሴው ግድብ ድርድር ላይ እንዲሳተፉ መመደባቸውን ዋዜማ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። አቶ ሞቱማ መቃሳ ከዚህ ቀደም የመከላከያ ሚንስትር እንዲሁም የውሀ ሀብት ሚንስትር ሆነው ሰርተዋል።

ግብፅና አሜሪካ ድርድሩ ሳይቋጭ ኢትዮጵያ የግድቡን የውሀ ሙሌት እንዳትጀምር በብርቱ እያስጠነቀቁ ባለበት በዚህ ስዓት የውሀ ሀብት ሚንስትሩ ስለሺ በቀለ የውሀ ሙሌቱ በተያዘለት ዕቅድ መሰረት በሐምሌ ወር ይጀመራል ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል።

የኮሮና ወረርሽኝ የደቀነው ዘርፈ ብዙ አደጋ ተጨምሮበት የገባንበት የዲፕሎማሲ አጣብቂኝ በመጪው ሐምሌ የውሀ ሙሌት ለመጀመር አዳጋች ሊሆን ይችላል፣ በመሬት ላይ ያለው እውነታም ያንን አያመለክትም። [ዋዜማ ራዲዮ]

To contact Wazema Editors, you can write wazemaradio@gmail.com