port djibouti

በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የፖለቲካ ኪሳራውን በመፍራት ይመስላል ሀገሪቱ ወደብ አልባ በመሆኗ በአጠቃላይ እየደረሰ ስላለው ብርቱ ኢኮኖሚያዊይና ማህበራዊ ቀውስ ይፋ ማድረግ የማይደፍረው። አሁን አሁን ግን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ባለስልጣናት፣ የልማት አጋሮችና አለም ዓቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ በተለይ ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል መራር ዋጋ እንዲከፍል እንዳደረገው መናገር ጀምረዋል። ከታች ያድምጡ

የመጀመሪያው ክፍል ሪፖርትን ደግሞ እዚህ ያድምጡ ፡ ጠቅ

ኤርትራ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ፩፱፱፩ ዓመተ ምህረት ከኢትዮጵያ ከተገነጠለች ጀምሮ ኢትዮጵያ በአለም ትልቋ ወደብ አልባ ሀገር ለመሆን ተገዳለች፡፡ በመሆኑም ለስምንት ዓመታት ያህል የኤርትራዋን አሰብ ወደብ ለውጪ እና ገቢ ንግዷ ትጠቀምባት ነበር፡፡ ሆኖም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ፩፱፺ ዓመተ ምህረት በሁለቱ ሀገሮች መካከል የድንበር ግጭት ሲቀሰቀስ ኢትዮጵያ አሰብ ወደብን መጠቀም አቁማ ፊቷን ሙሉ በሙሉ ወደ ጅቡቲ ወደብ ለማዞር ተገደደች፡፡

በጅቡቲ ውደብ መጠቀም በወቅቱ የሞትና ሽረት ተደርጎ ሊውሰድ ቢችልም ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በኤርትራ ጉዳይ ላይ በያዘው የተሽመደመደ አቋም ሀገሪቱን ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ሸክም፣ ገዥውን ፓርቲም ለክፍፍልና አተካሮ እንደዳረገውም ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባችበት ጊዜ ፩፱፺ ጀምሮ ፺ በመቶ ያህሉን ገቢ እና ወጪ ንግዷን የምታካሂደው በጂቡቲ ወደብ በኩል ነው፡፡ ነዳጅ ዘይት፣ ካርጎ፣ ኮቲኔር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት እንዲሁም ቡናና እንስሳትን ጨምሮ ሌሎች ምርቶች ለውጭ ገበያ የሚቀርቡት በጅቡቲ ወደብ በኩል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአሁን ጊዜ ጅቡቲ የሚራገፈው የኢትዮጵያ ካርጎ በወር ኣስር ሺህ ኮንቴነር ያህል እንደሆን ይገመታል፡፡ ከጅቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያም በየቀኑ ከአምስት መቶ በላይ ከባድ ካሚዎኖች እቃ ጭነው እንደሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ጂቡቲም በበኩሏ ሶስት መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ጫት በየአመቱ ከኢትዮጵያ ታስገባለች፡፡ የምተገዛበት ዋጋ ተመን በይፋ ባይታወቅም ዋነኛ የሃይል አቅርቦቷንም የምታገኘው ከኢትዮጵያ ነው።

ኢትዮጵያ በአለም ላይ ካሉት ፬፭ ወደብ አልባ ሀገሮች አንዷ ስትሆን ከ፫፪ቱ ወደብ አልባ ታዳጊ ሀገሮች ውስጥ ትመደባለች፡፡ ከነዚህ ውስጥ ፩፮ቱ የአፍሪካ ሀገሮች ናቸው፡፡ ወደብ የሌላቸው ሀገሮች የንግድ ወጪ ወደብ ካላቸው በሁለት እጥፍ እንደሚጨምር ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ እድገታቸውም ወደብ ካላቸው ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር በስድስት በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ይታመናል፡፡

ለወደብ አገልግሎት የሚወጣ ወጪ ለገቢ ንግድ የሚወጣው ወጪ እንዲጨምር ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም ለሀገራችን ወጪ እና ገቢ ንግድ መዛባትም የራሱን ሚና እንደሚጫወት ይታወቃል።፡፡ የተጋነነ የወደብ ወጭ በዓለም ዓቀፍ ንግድ ተወዳዳሪነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስላለው ሀገራችንም በዚህ ረገድ እየተጎዳች እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።

በሀጋራችን በተደጋጋሚ የሚከሰተውም ከፍተኛ የዋጋ ንረትም ከወደብ ወጭ ከፍተኛነት ጋር ተያያዥነት እንዳለው ከሁለት ዓመት በፊት የገንዝብ ሚንስትር ደኤታው አህመድ ሽዴ በአንድ አህጉራዊ ስብሰባ ላይ መናገራቸው ይታወሳል።

ለወደብ አገልግሎት የወጣው ከፍተኛ ወጭ የሀገሪቱን የሚለኒዬም ልማት ግቦችን ለማሳካት በርካታ የትምህርትና ጤና ተቋማትን መገንባት ያስችል እንደነበርም ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ ሁለት ሺህ ስምንት ዓመተ ምህረት ድረስ ለወደብ አገልግሎት በአመት ስምንት መቶ ሃምሳ ሚሊዮን ዶላር ትከፍል እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ የተደረገው አስደንጋጭ ጭማሪ ግን በዓመት ሁለት መቶ አስር ሚሊዮን ተጨማሪ ወጭ ጠይቋል። ጭማሪውም የሀገሪቱ ወጭ በዓመት ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲሆን አድርጎታል። ባሁኑ ጊዜም ሀገራችን ለወጪ እና ለገቢ ንግዷ በየቀኑ ከሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምትከፍል መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ይሄም ወጭ የሀገራችን ጠቅላላ የውጪ ንግድ የገንዘብ መጠን አስራ ስድስት መቶኛ ያህል እንደሆነ የፋይናንስ ሚንስትር ደኤታው አህመድ ሽዴ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

በጂቡቲ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ፪፻፫ በወደብ አጠቃቀም ላይ ስምምነት ተደርሶ ነበር ፡፡ ስምምነቱ የሚከለሰውም በሁለቱ ሀገሮች ሙሉ ስምምነት እንደሚሆን መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሆኖም ጅቡቲ ከኢትዮጵያ መንግስት እውቅና ውጪ ብቻ ሳይሆን ያለ ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ የክፍያ መጠኑን እና ሌሎች አሰራሮችን ስትቀይር ተስተውሏል፡፡

ለአብነት ያህልም በሁለቱ ሀገሮች መካከል መጀመሪያ የተደረሰበት ስምምነት የአገልግሎት ክፍያ የሚፈፀመው እቃዎች ከተነሱ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይሆናል የሚል ቢሆንም ጅቡቲ በ፳፩፫ ገቢ እቃዎችን ለመረከብ የቅድሚያ ክፍያ የባንክ ዋስትና እንዲቀርብላት መጠየቋም ይታወሳል። በሁለቱ መንግስታት ድርድር ውሳኔው እንዲዘገይ ቢደረግም ለውጡ ግን የውጭ ምንዛሬ በቀላሉ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለማግኘት ለሚቸገሩት ኢትዮጵያውያን አስመጪዎች ከባድ ፈተና ከመሆኑም በላይ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ላይ እጅግ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ጅቡቲ ቀደም ሲል ለገቢ ካርጎ ነፃ ማስቀመጫ የፈቀደችውን ፩፭ ቀን ወደ ፰ ቀን ማሳጠሯ ይታወሳል፡፡ ለወጭ ካርጎ ደግሞ ፲ ቀን የነበረውን ወደ ፫ ቀን አሳጥራዋለች፡፡ አሁን በተግባር ላይ ያለው አሰራርም ይኸው ነው፡፡ ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ መንግስትን ብቻ ሳይሆን የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚም ዋንኛ ራስ ምታት ነው። እነዚህ ለውጦች በገንዘብ ወጭና በጠቅላላው በሀገሪቱ እድገት ላይ የሚያስከትሉት ወጭ ቢሰላ የትየለሌ እንደሚሆን ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

የሀገራችንን የወደብ ወጪ ያባባሱትና በአለም አቀፍ ኢኮኖሚ ያላትን ተወዳዳሪነት ከቀነሱት በርካታ ምክንያቶች ውስጥ የወደብ ክፍያ ወጪ መናር፣ ጅቡቲ ለገቢ እቃዎች በነፃ ማስቀመጪያ የፈቀደችውን ጊዜ ማሳጠሯ፣ የባዶ ኮንቴነሮች በብዛት አለመገኘት፣ የእቃዎች ማከማቻ ቦታ እጥረት እና እቃዎችን ከወደቡ ወደ መሀል ሀገር ለማመላለስ የሚወስደው ጊዜ ረዥም መሆናቸውን የገንዝብ ሚንስቴር ባለስልጣናት ሲናግሩ ይሰማሉ። ሀገሪቱም ወጭዋን ለመቀነስ በትራንዚት ቴክኖሎጂ ዓለም ዓቀፍ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ሲናገሩ መደመጣቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚያመላክት ነው። ኢትዮጵያ ንግዷ በማደጉ ባለፈው ኣመት ዘጠኝ የንግድ መርከቦችን መግዛቷ ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይም የእቃዎች በወደቡ ላይ ለብዙ ጊዜ መጠራቀም ሀገሪቱን በዓመት ከ፪፻ ሚሊዮን ዶላር በላይ እያስወጣት እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን መንግስት እቃወቻቸውን በቀን ገደቡ የማያነሱ አስመጭዎችን መቅጣት መጀመሩን መዘገቡ ይታወሳል። ይህንን ችግር ለመቅረፍም ሀገሪቱ የመልታይ ሞዳል ትራንስፖርት አሰራር ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች።

ሁለቱ ሀገሮች በእጅጉ የሚፈላለጉ ሀግሮች ቢሆኑም ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚዋ ግዙፍነት፣ ህዝብ ብዛቷ፣ ወታደራዊ ሀይሏ፣ ክፍለ አሕጉራዊ ዲፕሎማሲያዊ ጡንቻዋ እና ለጅቡቲ ከምትሰጠው ዓይነተኛ ጥቅም አንፃር የጅቡቲን እጅ መቆልመም አልተቻላትም። ባንፃሩ ጅቡቲ ሉዐላዊነቷንና ክብሯን አስጠብቃ ከመሄዷም በላይ የኢትዮጵያን እጅ በተደጋጋሚ ስትቆለምም ተስተውሏል፡፡

በእርግጥ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ‹‹ፖለቲካዊ ውህደት››ን ለመፈፀም እየተሰራ ስለመሆኑ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ሲነገር ይሰማል። የጂቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኡመር ጌሌህም ባለፈው አመት ‹‹ኢትዮጰያ ማለት ጂቡቲ ነች፣ ጂቡቲ ማለት ኢትዮጵያ፣ ምንም ልዩነት የለም›› ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ሆኖም ግን እስካሁን ከሚታዩት ተጨባጭ ሁኔታዎች አንፃር የፖለቲካዊ ውህደት ትርክቱን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠራጠሩ ታዛቢዎች በርካታ ናቸው። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ እስካሁንም ድረስ በወደቡ ከመገልገል ውጪ ምንም የኣክሲዮን ድርሻም ሆነ ሌላ ኢንቨስትመንት እንደሌላት የሚታወቅ ነው።

ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ ላይ ያላት ጥገኝነት እንዲቀጥል የሚያደርጉት ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ይኖራሉ። የመጀመሪያው በኢትዮጵያ ኤርትራ ድንበር ውዝግብ ላይ ዓለም ዓቀፉ ፍርድ ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ተግባራዊ ሳይሆን ተንጠልጥሎ በመቅረቱ ሁለቱ ሀገሮች በቅርቡ ሰላማዊ ግንኙነት እንደማይጀምሩ ስለሚታምን ነው። ሆኖም ኢትዮጵያ ትክክለኛ አማራጭ ወደብ ከፈለገች ከአሰብ ወደብ የተሻለ አማራጭ ያላት አይመስልም።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያ የወደብ ፍላጎት በማደጉ ሳቢያ ይህንኑ ፍላጎት ለማሟላት ሲባል የጅቡቲ ወደብ የማስተናገድ አቅምና የአግልግሎት አሰጣጥ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉ ይታውቃል። የጅቡቲ ወደብ ከፍተኛ ስራ ሃላፊ ባለፈው ግንቦት ወር ለኬንያው ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ “እንደ ዱባይ እና ሲንጋፖር ለመሆን መንገዱን ተያይዘነዋል” ብለው ነበር። በርግጥም የጅቡቲ አካሄድ የምስራቅ አፍሪካ ወጭና ገቢ ንግድ እና ዋና የሎጅስቲክ ማዕከል መሆን እንደሆን የሚያጠራጥር አይደለም።

ስለሆነም ሀገራችን ባህር በር አልባ ሆና እሰከቀጠለች ድርስ ወደፊትም የጅቡቲ ወደብ የኢትዮጵያ ዋነኛ የወጭና ገቢ ንግድ መተላለፊያ ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ነው። እስካሁን ከታየው የጅቡቲ ባህሪና ከተያያዘችው መሰረት ልማት ማስፋፊያ አንፃርም የወደብ አገልግሎት ክፍያው እየጨመረ እንደሚሄድ መገመት አይከብድም። የኢትዮጵያ የወደብ ወጭ በዓለም ዓቀፍ ንግዷም ሆነ በሁለንተናዊ ዓልማቀፍ ንግድና እድገቷ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖም በዚያው ልክ እየጨመረ ይሄዳል። ሁነኛ መፍትሄ ጠፍቶ እንጅ ወደብ አልባነት ከዋንኛዎቹ የሃገሪቱ እድገት ማነቆዎች አንዱ እንደሆነ በመንግስት ከታመነበት ቆይቷል።