Solome Taddesse
Selome Taddesse

ዋዜማ ራዲዮ- ወይዘሮ ሰሎሜ ቤታቸው ሲገቡ ኢቢሲ ተከፍቶ ከደረሱ ቲቪው እሽሽሽሽ ብሎ ራሱን በራሱ ይዘጋል፤ ለምን ቢባል… ተሸማቆ፡፡ ወይዘሮዋ በዘመነ ሥልጣናቸው እንዲያ የደከሙለት ጣቢያ ዛሬ አድሮ ቃሪያ፣ ከርሞ ጥጃ፣ መሆኑ ለራሱም ሳያሳፍረው አልቀረም፡፡ እርግጥ ነው በዘመን ልዩነት ኢቴቪኢቢሲ ኾኗል፡፡ ይህ ሽግግር መልከጥፉን በሜክ አፕ ብዛት ቆንጆ የማድረግ ሙከራ ይመስላል፡፡ ወይዘሮ ከበቡሽን ኪያ ብሎ እንደመጥራት ያለ፡፡

የዛሬን አያድርገውና በርሳቸው ዘመን ጣቢያው ዉብ ነበር፡፡ ደርዝ ነበረው፡፡ አዝናንቶናል፣ አሳውቆናል፤ እናመሰግናለን፡፡ የምስጋናውን ሲሶ መዝገን ያለባቸው ግን ወይዘሮ ሶሎሜ ናቸው፡፡ ዐይናችን የርሳቸው ሐሳብ ነበር፡፡ አሁን ዐይኑ ጠፍቷል፡፡ ዐውደ-ሰብ ከኢቢሲ አውድ ዉጭ ከኾነ ዘመን የለውም፡፡ አሁን ኢቢሲ አተት ኾኗል፡፡ ወይም አተት አሞታል፡፡ እውነት ለመናገር ያን የጣቢያውን ገናና ዘመን ለመመለስ ዳተኛው ዶክተር ነገሪ ይቅርና ተራማጇ ሶሎሜም አይችሉትም፡፡ በዚህ ዘመን ኢቢሲን ከማቅናት አሊፖን መልሶ መገንባት አይቀልም ብላችሁ ነው?

የቀድሞው ኢቴቪ አለቃ፣ የትርጉም አልባው የድንበር ትንቅንቅ ቃል አቀባይ፣ የሴቶች መብት ተሟጋች፣ የተዋጣላት አግባቢት (Lobbyist) ከሕዝብ ዐይንና ጆሮ ከጠፉ ዘመን አለፈ፡፡ ለመኾኑ ወይዘሮ ሶሎሜ ታደሰ ምህረቱ የት ጠፉ?

ቁጡ፣ብርቱ፣ተናዳፊ፣ተግባቢ፣ ሞጋች፣ ቱባ ሐሳብ አፍላቂ፣ ሸርዳጅ፣ ትጉህ፣ እልኸኛ፣ የነጻነት ጠበቃ፣ ተራማጅ፣ አነቃቂ፣ ተንኳሽ፣ አንኳሳሽ፣ አሸናፊ፣ አጥረግራጊ፣ ተምሳሌት፣ አትንኩኝ ባይ….እነዚህ ሁሉ ቅጽሎች የሚመጥኗት ወይዘሮዋ ከሚያስቆጧቸው ጉዳዮች አንዱ አንቱ መባል ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ያሉ አንቀጾች አንቱታን እንዲገድፉ የኾኑትም በዚኹ ምክንያት ነው፡፡

ሶሎሜ በራስ የመተማመን ኪሊማንጃሮ፣ የልበሙሉነት ራስ ዳሽን፣ የሴትነት ደጀን ናት ይላሉ ወዳጆቿ፡፡ ጾታዊ እኩልነትን በዚች አገር ለማምጣት ከሚፋለሙት የጦር አበጋዞች መካከል የድኅረ ሚሊየንየሞቹን ትወክላለች፡፡

በምትሠራቸው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ቅንጣት ታህል ያለመርካት አባዜ የተጠናወታት ወይዘሮ ሶሎሜ ለሌሎች ሰዎች ነጻነትን እስከ ጥግ መስጠትን ታውቅበታለች፡፡ ማንም እንዲበልጣት አለመፍቀድንም እንዲሁ፡፡ “ድሮ ሁሉን ነገር የመቃወምና የመፈታተን ባህሪ ነበረብኝ” ስትል አምናለች ተምሳሌት ለተሰኘ ቱባ መጽሔት በአንድ ወቅት፣ አሁንም ግን ያ ባሕሪ ብዙም የተለያት አትመስልም፡፡ 

በኢህአዴግ አገር አቀፍ የወግ ምርጫ ፓርላማ ለመግባት ከፍተኛ ጉጉት አድሮባት የነበረችው ወይዘሮ ሶሎሜ የግል ማሊያ ለብሳ በጠባቡ የፖለቲካ ሜዳ ማሟሟቅ ጀምራም ነበር፡፡ እንደ 97ቷ ስንዱ፡፡ ኾኖም የግል እጩዎች በበረከቱ ጊዜ በእጣ ይለዩ የሚለው የምርጫ ሕግ ድንገት ደርሶ ጉድ አረጋት፤ እንጂማ ይሄኔ ፍዙን ፓርላማችንን ታስፈነጥዘው፣ምንኛ ነፍስ ትዘራበት በነበር!

“ብቻ ምናለፋሽ! ሰሎሜ ፓርላማ ገብታ ቢኾን ኖሮ ከቃና ቲቪ ቀጥሎ ተወዳጁ ፕሮግራም ፓርላማ  ሾው ይኾንልሽ ነበር” ብላኛለች ከሶሎሜ ጋር ዊስኪ የምታጋጭ፣ ቄንጠኛ ሮዝማን የምታንቦለቡል ኢትጵያዊት እውቅ የፊልም ዳይሬክተር፣ በአንድ ወቅት፡፡

እርግጥ ነው ይሄ በጠራራ ፀሐይ የሚያሸልበው ፓርላማችን እንደ ሰሎሜ ዐይነት ንቁና ሕይወት ያለው አባልን ይሻል፡፡ ኾኖም ሶሎሜ በየትኛው ትዕግስቷ ነው 15 ገጽ ሙሉ እኝኝኝ የሚል የሚኒስትር ሪፖርት ቁጭ ብላ የምታዳምጥ? ወይ ፓርላማ ረግጣ ትወጣለች፣ ወይ ሚኒስትሩን አጥረግርጋ ታስወጣዋለች፡፡ አላስ!

ሶሎሜ ጋ ቀልድ የለማ፡፡ በተፈጥሮዋ የሚያላዝን ሰው አትወድም፡፡ ነገር የሚደግም ሰው ያንገሸግሻታል፡፡ ትኩስ ሐሳብ የሌለው ሰው ሲያወራ ያቁነጠንጣታል፡፡ ሰው ሁሉ ሐሳቡን በአጭር ከተቻለም በግጥም መልክ ቢገልጥ ምንኛ በወደደች፡፡”አዲስ ሐሳብ ከሌላችሁ፣ እንደዝምታ የሚያምርባችሁ ነገር የለም” ትላቸዋለች የራሷን ሠራተኞች ስብሰባ እንኳ ስትመራ፡፡

እና…ሶሎሚና ፓርላማ ገብታልን ቢኾን ኖሮ ነገሩ ሁሉ ምንኛ መልካም ይኾን ነበር የምንለውም ለዚሁ ነው!!

ለነገሩ ዉጭም ኾና የምታርፍ አይደለችም፣ እሷ፡፡ መብትን በመጠየቅ ረገድ ትንታግ ናት፡፡

ለምሳሌ በቅርቡ እንኳን ፎርቹን ጋዜጣ ላይ ባተመችው አንድ ጽሑፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን ወርፋቸዋለች፡፡ “ቤትህ ዉስጥ በአራት ድንቅ ሴቶች ተከበህ እንዴት ሦስት ሴት ሚኒስትር ብቻ በመሾም ትታበያለህ?” የሚል መንፈስ ያለው ጽሑፍ ጽፋ አስደምማኛለች፡፡ እርግጥ ነው ይህን ተንኳሽ ጽሑፏን ሳነበው የራሱ ሰምና ወርቅ እንዳለው ተሰምቶኝ ነበር፡፡ ሰሙ ምንድነው ካላችሁ ያው 100 ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት፣ 52 ሚሊዮኑ ሴቶች በኾኑበት፣ 30 የካቢኔ አባላት በተሾሙበት አገር፣ ሦስት ሴቶች ብቻ እንዴት ይመረጣሉ? የሚል ሲሆን፣ ወርቁ ግን “የኾነስ ኾነና እኔ እንዴት እዘነጋለኹ?” የሚል ሊኾን ይችላል እላለሁ፣ እንዲሁ ስጠረጥር፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ ለዘብተኛ ተቃዋሚ ኾኖ የመሳተፍ ጽኑ ፍላጎት እያዳበረች መጥታለች የምትባለው ሰሎሜ በዚያ ሰሞኑ የካቢኔ መዋቅር ግብዣ ይቀርብልኛል የሚል ጠጠር ያለ ተስፋን ብታዳብር የሚጠበቅ ነው፡፡ በተለይም በፓርቲው ዉስጥ ከታማኝነት በላይ ለእውቀትና ብቃት ቦታ እሰጣለሁ የሚል ትርክት በፖለቲካው ዐውድ ማንዣበቡ ተስፋዋን አንሮት ሊሆን እንደሚችል እንጠረጥራለን፡፡ ምናለ ግን ሰጥተዋት በነበር? ደግሞም እኮ ይገባታል፡፡

ሶሎሜ የሕጻናትና ሴቶች ሚኒስትርነቱን ቦታ ብታጣ የኮሚኒኬሽን ቢሮ የግሏ እንደሚኾን ተስፋን ሰንቃ ነበር ይላሉ ሐሜተኞች፡፡ የሚገርመው ሴቶች ለምን ከሕጻናት ጋር በአንድ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ተዳበሉ የሚለው ሁሌም የሚያንገበግባት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ መንግሥት ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ የት ድረስ እንደሆነ እንደ አንድ ማሳያ ታነሳዋለች፤ በተደጋጋሚ፣ በየመድረኩ፡፡

ስነግራችሁ አልሰማ አላችሁኝ እንጂ…፣ እነዚህ ሰዎች እኮ እኛ ሴቶችንን እንደሕጻን ነው የሚቆጥሩን፡፡ ካላመናችሁኝ፣ እዩት ይህን መሥሪያ ቤት “ ትላለች በሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር በኩል ያቺን መከረኛ ሲልቨር መርሴዲሷን ይዛ ባለፈች ባገደመች ቁጥር፡፡

BRExit Vs SELOMExit

የሶሎሜ ትልቁ ገቢ ግን ደመወዟ ነው ማለት ይቀላል፡፡ የደመወዟ ምንጭ ደግሞ ደጉ የእንግሊዝ ሕዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ስፓይስ ገርልስ ለመፍጠር የምትሠራው ሶሎሜ የኛ የተባሉ ተወዳጅ የሴት ልጃገረዶች የሙዚቃ ባንድን መስርታለች፡፡ የባንዱ አባላት ለኢትዮጵያዊያን ልጃገዶች ተምሳሌት ኾነው እኛም እንችላለን የሚል መንፈስን፣ በራስ መተማመንን በአገሪቱ ሴቶች ላይ ያሳድራሉ ትላለች፡፡ ለዚህ ተግባሯ ሶሎሜና አምጣ የወለደችው ኢመርጅ  የተባለው አማካሪ ድርጅቷ የትየሌሌ ፖውንድ ይከፈላቸዋል፡፡ ከእንግሊዝ ሕዝብ ግብር የተሰበሰበ 5 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ አገር ቤት ሲላክ አብዛኛው ድርሻ የርሷ ነው ይባላል፡፡  የእንግሊዝ ሕዝብ ምን ደልቶት ነው ይህን ሁሉ ፓውንድ ለአንድ የልጃገረድ ባንድ የሚከሰክሰው የሚል ስሞታ መሰማት ከጀመረ ታዲያ ቆየ፡፡ እነ ዴይሊ ሜይል፣ እነ ዘቴሌግራፍ፣ እነ ዘሰን እንባቸው ጠብ እስኪል በጉዳዩ ዙርያ አልቅሰዋል፣ ቀለማቸው እስኪዶሎዱም ጽፈዋል፡፡

ይህ ተደጋጋሚ ለቅሷቸው ታዲያ ከሰሞኑ ፍሬ ያፈራ ይመስላል፡፡ ባሳለፈነው ሳምንት የእንግሊዝ ፓርላማ የዉጭ እርዳታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የእርዳታና ትብብር ሚኒስትሯን ወይዘሮ ፕሪቲ ፓቴልን ጠርቶ ጉዳዩን በአስቸኳይ እንድታጤነው አስጠንቅቋታል፡፡ ይህን ተከትሎ የእንግሊዝ ሕዝብ BRExitን እንደመረጠው አሁን ደግሞ SOLOMExit ብሏል፡፡ ይህ ግን ለሶሎሜ አስደንጋጭ ዜና አይደለም፡፡ ምናለ በሉኝ አሁን አጋር አታጣም፡፡ የባንዱ አባላት ቢኾን ለጊዜው እያነቡም ቢኾን እስክስ ይሏታል እንጂ አይበተኗትም፡፡ ሴቲቴ ሶሎሜ ናታ!

የወይዘሮ ሶሎሜ ሕይወትና እርምጃ

ወይዘሮ ሶሎሜ የመምህር ልጅ ናት፡፡ እናቷ መምህርት፣ አባቷ መምህር፡፡ በታኅሳስ ግርግር ጊዜ አክሱም ተወለደች፤ ድክድክ ማለት ስትጀምር አዲስ አበባ መጣች፡፡ የሰሜን ማዘጋጃ ያውም የታክሲ ማዞርያ ሰፈር ልጅ ናት፡፡ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ሴንትሜሪ የካቶሊክ ትምህርት ቤት ነው የተማረችው፡፡ አራት ወንድምና ቁርጥ እርሷን የምትመስል ቆንጅዬ የደስደስ ያላት እህት አለቻት፡፡

የሴቶች ጠበቃ ወይዘሮ ሶሎሜ በዓለም ላይ እንደ አባቷ አቶ ታደሰ ምህረቱ የምትወደው ሰው አለ? የለም፡፡ ቀጥሎ ነው እናቷን ወይዘሮ አሰፋሽ ካሳሁንን የምትወዳቸው፡፡ እንዲህ ተንሰፍስፋ የምትወዳቸው አባቷ ታዲያ በ42 ዓመታቸው በመኪና አደጋ ተለይዋት፡፡ የፈጠሩባት በራስ መተማመን ግን ዘላለማዊ ይመስላል፡፡ አባቷ ያኔ በጥቁርና ነጭ ቲቪ አምባሳደር ዮዲት እምሩን ሲያዩ ወይ ደግሞ ወይዘሮ ስንዱ ገብሩን ሲመለከቱ…የኔ ሰሎሜ ስታድግ እንዲህ ዲፕሎማት ነው የምትኾን ይሉ ነበር ይባላል፡፡ ሴት ጋዜጠኛ ሲያዩም…የኔ ሸኮሪና ሶሎሚና ወደፊት ጋዜጠኛ ነው የምትኾን… ይሉ ነበር፡፡ ትንቢታቸው ዘመን ቆጥሮም ቢኾን በከፊል ሠራ፡፡

ሰሎሜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተረጋግታ መማር ስላልቻለች ዉጤቷ አልሰመረም፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ ብትባረርም ያኔዉኑ ወደተባበሩት ሶቭየት ኅብረት መብረር ግን አላቃታትም፡፡ ሩሲያ- ሚኒስክ ቢሉሩሲያ በተባለ የሌኒን መታሰቢያ ኮሌጅ ጋዜጠኝነትን ለአራት ዓመት ያህል ተማረች፡፡ በነ አንቶን ቺኮቭ ጥበብ ደነሰች፣ በነቶልስቶይ ምስጢር ተምነሸነሸች፤ በነዶስቶቪስኪ ሥነ ጽሑፍ ሰከረች፣ በአሌክሳንደር ፑሽኪን ግጥም እስክስታ ወረደች፡፡ ሕይወት ጣፈጠቻት፡፡ ሳይቤሪያ ሞቀቻት፡፡ ይበልጥ ልታጣጥማት ስትል ግን እክል ገጠማት፡፡ እዚያ በነበረ አንድ የኢትዮጵያ ማኅበር ፀረ አብዮተኛ የሚል ታርጋ ተለጠፈባት፡፡ ወደ አገር ቤት ልትጠረዝ ኾነ፡፡ ሳትውል ሳታድር በፖላንድ በኩል ሾልካ ጀርመን ገባች፡፡ ጀርመን በስደተኛ ጣቢያ ዉስጥ ዛሬ ጥቁሮች ከሚያዩት መከራ ያልተናነሰ ጊዜን አሳፈች፡፡

በስንት ጣጣ ከጀርመን አሜሪካ ተሻገረች፡፡ ማውንት ሆልዮክ ኮሌጅ ገብታ ዲግሪ ያዘች፡፡ ደርግ ወደቀ፡፡ ብሶት -የወለደው ጀግናው የኢህአዴግ ሠራዊት አዲስ አበባን ያዘ፡፡ ይህን ተከትሎ ለስንት ዘመን ተከርችሞ የነበረውን በር አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ፈንቅሎት አሜሪካን ኤምባሲ ገባ፡፡ ሶሎሜ የርሱ ቀኝ እጅ ኾነች፤ ኢህአዴግ ሁለት መልከኛ አባሎች አሉት፡፡ አንዱ አርከበ ነው፤ አንዱ ብርሃነ ገብረክርስቶስ፡፡ ሶሎሜ ታዲያ የብርሃነ የፕሬስ አማካሪው ኾነች፤ ቆንጅዩዋ ሶሎሜ የመልከኛው አምባሳደር ተወዳጇና ተመራጯ ሠራተኛ እንደነበረች ይታማል፡፡

ሶሎሜ ወደ አገር ቤት ገብታ የኢቴቪ አለቃ ከኾነች በኋላ የመንግሥት አንደበት ኾና ቃል እያቀበለች በዝና መሰላል ሰማይ ወጣች፡፡ አንዳንዴ እንዲህ አስባለሁ፡፡ ያን ወቅት ግን ሶሎሜ ባትኖር ኢህአዴግ ምን ይውጠው ነበር? ከጉድ እኮ ነው ያወጣችው፡፡ ከመለስ ሌላ ዱዳ የነበረው ህወሃት/ኢህአዴግ እንደ አደይ አበባ የሚፍነከነክ እንግሊዝኛና ማን ይናገርለት ነበር? ኢህአደግ ዱዳ እኮ ነው፡፡ የተጻፈ እንኳ አጥርቶ የሚያነብ የሌለበት የጨበራ ማኅበር፡፡ እናስ ራሱን አፍታቶ መግለጽ የጀመረው በሶሎሜ አንደበት አይደለምን?

ሶሎሜ እኮ የቢቢሲውን ዘጋቢ አሌክስ ላስትን ባድመ ምሽግ ገብቶ ሲፎልል ሰንብቶ አፉን ያዘጋች ጀግና ናት፡፡  ጋዜጠኝነቱን ዳግም እንዲፈትሽ፣ አንገቱን እንዲደፋ ያደረገች የከባድ ሚዛን ቃል አቀባይ ናት፡፡ ሶሎሜ ታዲያ ያኔ ከራሷ ጋር ተቀራራቢ ሥራ ከነበራትና የአሌክስ ላስት ወዳጅ ከነበረችው ከኤርትራዊቷ ሩት ስምዖን ጋር እልህ ሳትጋባ አልቀረችም፡፡ በመጨረሻ ግን ዘረረቻት፡፡

ብቻ ምን አለፋችሁ….ሶሎሜ በኢህአዴግ ውስጥ በድንገት በርታ ድንገት ድርግም ብላ የጠፋች አብሪ ኮከብ ነች፡፡ በመጨረሻ እንዲህ ኾነ፡፡ ባድመም ሄደች እንደቀልድ፣ ሶሌሜም ሄደች፣ እየሳቀች፡፡ አፋኙ የኢህኤደግ የፖለቲካ ድባብ ግን ዛሬም ድረስ ቀጥሏል፡፡

ቃል አቀባይነትም ቢኾን በሶሎሜ ዘመን ተወለደ፡፡ ሶሎሜ ሥራ ስትለቅ ሞተ፡፡

ድኅረ ኤቲቪ

ሶሎሜ አፈና አይመቻትም፡፡ የምትወደው ሥራዋ የምትወደውን ነጻነቷን ሊቀማት ሲሞክር ያን የሚሞቅ የኢቴቪ ወንበር ጥላ በረረች፡፡ “ወዴት እንደምሄድ እንኳ አላውቀውም ነበር” ትላለች፡፡ ከዚያ በኋላ ከሌላኛዋ የሴቶች ተምሳሌት ከመዓዛ አሸናፊ ጋር አብራ የኢትዮጵያ ሴቶች ቅንጅትን መሠረተች፡፡

የ94ቱ ረሀብ በገባ ጊዜ ሰሎሜ ቆንጆ ምሳ ከፕሮፌሰር አንድሪያስ ጋር እየተመገበች ነበር፡፡ ያስተረፉትን ምግብ ስታይ አዘነች፡፡ ሐሳብ ማፍለቅ ማቆም የማይችለው የሰሎሜ ጭንቅላት አዲስ ነገር አሰበ፡፡ የተራቡ ወገኖችን መርዳት፡፡ “አንድ ብር ለአንድ ወገን” የተባለውን ስኬታማ ዘመቻ አስጀምራ አስጨረሰች፡፡ በአንድ ቆንጆ ምሳ የጠነሰሰችው ሐሳብ 14 ሚሊዮን ብር ወለደ፡፡ እንዲህ ናት ሰሎሜ፡፡ በሐሳብ ጎርፍ የምትዋልል ጅረት፡፡

ሰሎሜ አሁን የምትኖረው 22 ማዞርያ በሚገኝ፣ አረንጓዴ በበዛበት የቀበሌ ቤት ዉስጥ ነው፡፡ ከረፈደ በትዳር ገብታ ብዙም ሳታረፍድ ወጥታለች፡፡ ሁለት ዉብ መንትያ ልጆችን እንደ እናት ታሳድጋለች፡፡ ሊሴ ገብረማርያም ታመላልሳቸዋለች፡፡ ሶሎሜ በሁሉም ጉዳዮች ላይ መቀለድ ትችላለች፡፡ በመንታ ልጆቿ ግን ቀልድ አታውቅም፡፡ እነርሱ ከደወሉላት ነፍሷን አታውቅም፡፡ እንኳን ሥራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አያቆማትም፡፡ መብረር ነው፡፡ ብዙ ፍቅርን ትመግባቸዋለች፡፡

የሶሎሜ የረዥምና የአጭር ጊዜ እቅዶች ሁለት ናቸው፡፡

የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን ሀውልት በፊንፊኔ አንድ አደባባይ ላይ ማቆም፡፡ ሶሎሜ-ቲቪ የሚባል ግሩም ድንቅ የቴሌዥዥን ጣቢያን መክፈት፡፡ በቃ!

ኣ…አ….ሰሞኑን ለካ አንድ ሌላም ሕልም ጨምራለች፡፡ እንደ ኦፕራይ ዊንፍሬይ አንድ የሴቶች ብቻ የኾነ ዩኒቨርስቲን በኢትዮጵያ መክፈት፡፡ ዉብና አጫጭር ቀሚሶችን መልበስ ለምታዘወትረው ሰሎሜ ይህ ረዥም የሚባል ሕልም አይደለም፡፡