Vaccinationምንም እንኳን አፍሪካ በማጅራት ገትር እና ፖሊዮ ክትባት ረገድ ፈጣን እመርታ ብታስመዘግብም አሁንም ከአምስት ህፃናት ውስጥ አንዱ ወይም 20 በመቶ ህፃናት የተላላፊ በሽታዎች መሰረታዊ ክትባት ተደራሽ እንዳልሆኑ ሰሞኑን የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ገልጧል፡፡

በቀሪው ዓለም ገዳይነታቸው በእጅጉ የተመናመነው ኩፍኝ፣ ቅድመ-ወሊድ መንጋጋ ቆልፍ እና ሳንባ ምች በአህጉሪቱ አሁንም በስፋት እንደሚታዩ ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡ በአፍሪካ ሁለቱ ዋና የህፃናት ገዳይ በሽታዎች ሳንባ ምች እና ተቅማጥ እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በአፍሪካ ባለፉት 25 ዓመታት ብቻ የህፃናት ሞት በ54 በመቶ ለመቀነሱ ዓይነተኛውን ሚና የተጫወተው የበሽታዎች መከላከያ ክትባት ነው፡፡ ክትባት በሽታን በመከላከል ወይም ጭራሹን በማጥፋት የህፃናትን ሞት በከፍተኛ ደረጃ ከመቀነስ አንፃር በወጭ ቆጣቢነቱ ተወዳዳሪ የለውም፡፡

[ቻላቸው ታደስ ያዘጋጀው ዘገባ ዝርዝር አለው አድምጡት]

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ለክትባት የሚወጣ ወጪ ብዙ ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ ከሚጠይቀው ህክምና ጋር ሲነፃፀር ወጪው በ16 እጥፍ ይቀንሳል፡፡ በበሽታዎች ሳቢያ በኢኮኖሚው ዘርፍ አምራች የሆነው የሰው ኃይል ከስራ ውጭ ከሆነ ምርታማነትን ስለሚጎዳ በሽታዎችን ቀድሞ በክትባት መከላከል አመርቂ ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት ማስገኘቱ የሚያከራክር አይደለም፡፡ የእያንዳንዱ ሀገር መፃዒ እጣ ፋንታ በህፃናት ጤናማ ዕድገት የሚወሰን መሆኑ ደግሞ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በአፍሪካ ለክትባት ሽፋን ትልቅ ፈተና ከሆኑት ምክንያቶች መካከል የበጀት ውስንነት፣ በአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚታዩ ችግሮች፣ ደካማ የጤና አገልግሎት፣ የወረርሽኝ ክትትልና ቁጥጥር አቅም ውስንነት፣ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ ተፍጥሯዊ አደጋዎች፣ በክትባት መድሃኒቶች ላይ የሚያዙ የተዛቡ አመለካከቶች፣ ለተዳራሽነት የማይመቹ ገጠራማ ቦታዎችና እንደ ኢቦላና ዚካ ቫይረስ ያሉ አዳዲስ ቀሳፊ ወረርሽኞች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተለይ ክትባት ከፍተኛ በጀት ስለሚፈልግ የመንግስታትን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ ሆኖም የኣለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከሃምሳ በመቶ በላይ ያለውን የክትባት ወጭ በራሳቸው ካዝና የሚሸፍኑ አፍሪካዊያን ሀገሮች ሃያ እንኳን አይሞሉም፡፡

በኢትዮጵያ ሀገር ዓቀፍ የክትባት ፕሮግም ስራ ላይ የዋለው ከ36 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1980 ለስድስት በሽታዎች መከላከያ የተጀመረው ፀረ-ስድስት ክትባት ባሁኑ ጊዜ አስራ አንድ የክትባት ዓይነቶች ላይ ደርሷል፡፡ ያም ሆኖ በሀገሪቱ አሁን ላይ ያለው የሁሉም ዓይነት ክትባቶች አማካይ ሽፋን 77 በመቶ ብቻ ነው፡፡

ባሁኑ ጊዜ ክትባት የሚሰጠው በየወረዳው በተመደቡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የቤት ለቤት አሰሳ እና በዘመቻም ጭምር በመሆኑ ተደራሽነቱን እንዳሰፋው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ኢትዮጵያ በምዕተ ዓመቱ ልማት ግቦች እኤአ በ2015 የህፃናት ሞትን በ2/3ኛ ለመቀነስ ተቀምጦ የነበረውን ግብ ከሦስት ዓመታት ቀደም ብላ እንዳሳካች የተመሰከረላት ሲሆን ለስኬቷም ዓይነተኛውን ሚና የተጫወተው የክትባት ሽፋን መጨመር ነው፡፡

ሩዋንዳ በቅርቡ መቶ በመቶ ሁሉን ዓቀፍ የክትባት ሽፋን ማዳረስ የቻለች ሲሆን ታንዛኒያ ደግሞ 98 በመቶ ሽፋን አስመዝግባለች፡፡

ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በአፍሪካ በኩፍኝ ወረርሽኝ ለህልፈት የሚዳረጉ ህመምተኞችን ቁጥር በ86 በመቶ መቀነስ ተችሏል፡፡ ምንም እንኳ ሁኔታው ከሀገር ሀገር ቢለያይም አዳዲስ ክትባቶችን በአህጉሪቱ ማስተዋወቅ መቻሉም እንደ ትልቅ እምርታ ተወስዷል፡፡

በያዝነው ዓመት የልጅነት ልምሻ ወይም ፖሊዮ ቫይረስ በየትኛውም አፍሪካዊ ሀገር አለመታየቱም የፀረ-ፖሊዮ ክትባት ተደራሽነት መስፋት ያስገኘው ስኬት እንደሆነ ይታመናል፡፡ የፖሊዮ ቫይረስ በኢትዮጵያም ባለፉት ሁለት ዓመታት ያልተከሰተ ሲሆን አሁንም የድንበር-ተሻጋሪ ፖሊዮ ቫይረስ ስጋት ስላለ ሀገሪቱ ከቫይረሱ ነፃ መሆኗ ገና በይፋ አልታወጀም፡፡ በያዝነው ዓመትም በመርፌ የሚሰጠውን በዋጋው ውድ የሆነውን አዲሱን ፀረ-ፖሊዮ ክትባት ስራ ላይ ማዋል ጀምራለች፡፡

ከዕርዳታ ለጋሾች በሚገኘው ድጋፍም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ህፃናትን በአጣዳፊ ተቅማጥ ለህልፈት የሚዳርገውን ሮታ ቫይረስ ለመከላከል የሚያስችለው ክትባት በመደበኛነት ስራ ላይ መዋል ጀምሯል፡፡ ሮታ ቫይረስ በየዓመቱ በኢትዮጵያ በአማካይ 28 ሺህ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህፃናትን እንደሚገድል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ መንግስት ማጅራት ገትርን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎችንም አማጭ ለሆነው ባክቴሪያ (Pnuemococcal) አዲስ የክትባት መድሃኒት በማስገባት ስራ ላይ አውሏል፡፡

በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነው የማጅራት ገትር ክትባትም ከአንድ አመት እስከ 29 ዕድሜ ክልል ላሉ ሁሉ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ በመጭዎቹ አምስት ዓመታትም አዳዲስ የክትባት መድሃኒቶችን በመደበኛው የአንድ ዓመት በታች ክትባት መርሃ ግብር ለማካተት እንደታሰበ ከጤና ጥበቃ ሚንስቴር የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ አዳዲስ የክትባት መድሃኒቶችን ስራ ላይ ማዋል በመግዛት አቅም፣ በበሽታው ስርጭት መጠንና በክትባቱ ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት ላይ ይወሰናል፡፡

በወባ ትንኝ ተሸካሚነት የሚተላለፈው አዲሱ የዚካ ቫይረስ ወረርሽኝ እስካሁን በአፍሪካ ሀገሮች ባይታይም የወረርሽኙ የመከሰት ዕድል ግን ከፍተኛ እንደሆነ ዓለም ዓቀፍ የጤና ተቋማት ከማስጠንቀቅ አልተቆጠቡም፡፡ የአሜሪካው በሽታ መቆጣጠሪያ ድርጅት (ሲዲሲ) በበኩሉ ነፍሰጡር እናቶችንና አራስ ልጆቻቸውን ለህልፈት በመዳረግ ለሚታወቀው ዚካ ቫይረስ ክትባት ለማግኘት እስከ ሁለት ዓመት ሊፈጅ እንደሚችል መግለፁ ለአህጉሪቷ ታዳጊ ሀገሮች መልካም ዜና አይደለም፡፡

በአወዛጋቢው የዓለም ንግድ ድርጅት ህግ መሰረት ሁሉም ሀገሮች የክትባት መድሃኒትም ሆነ የሌሎች መድሃኒቶች አምራች ኩባንያዎቻቸው ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የመድሃኒቱን የመጀመርያ አምራች ፋብሪካዎችን የባለቤትነት መብት እንዲያከብሩ የማስገደድ ሃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህም መድሃኒቶች ለታዳጊ ሀገሮች በርካሽ ዋጋ እንዳይቀርቡ እንቅፋት ፈጥሯል፡፡

በኋላ ላይ ግን አቅማቸው የክትባት መድሃኒት ለማምረት የማይፈቅድላቸው ድሃ ሀገሮች በሌላ ሀገር እንዲያስመርቱ ፍቃድ አግኝተዋል፡፡ ያም ሆኖ የድርጅቱ የባለቤትነት መብትና ተዛማጅ የንግድ ህጎች አሁንም ግልፅነት እንደሚጎላቸውና ለተለያየ ትርጉምም የተጋለጡ እንደሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በበለፀጉት ሀገሮች መድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ግዙፍ የስራ ዕድል ፈጣሪዎች በመሆናቸው ከስረው እንዲዘጉ አይፈለግም፡፡ ያ ደግሞ የበለፀጉት ሀገሮች ለብዙ በሽታዎች ክትባት ለማግኘት ተነሳሽነት እንዳይኖራቸው እንዳደረጋቸው ይታመናል፡፡

በአዳዲስ ክትባቶች ላይ የሚደረጉትን ሳይንሳዊ ምርምሮችም መንግስታቱ በገንዘብ የመደጎም ፍላጎት ስለሌላቸው ምርምሮቹ በበጎ ፍቃደኞችና መንግስታዊ ያልሆኑድርጅቶች ላይ ጥገኛ ሆነዋል፡፡ ይህም የክትባት መድሃኒቶችን ለመፈብረክ የሚጠይቀውን ጊዜና ወጪ ከፍተኛ ከማድረጉም በላይ ቢፈበረኩም እንኳ ለትርፍ ብቻ የቆሙ ፋብሪካዎች የሚያመርቷቸውን መድሃኒቶች ዋጋ የማይቀመስ አድርጎታል፡፡