ዋዜማ ራዲዮ- የሕወሓት ስራ አስፈፃሚና የቀድሞው የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በሌሎች የሕወሓት መሪዎች ላይ ምስክር ለመሆን “ተስማምተው” ከተከሳሽነት ቢሰናበቱም አሁን በድጋሚ ሃሳባቸውን ቀይረው ምስክር እንደማይሆኑ ተናግረዋል። ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በስምምነት ትቶት የነበረውን ክስ በወ/ሮ ኬሪያ ላይ በድጋሚ ሊያቀርብ እየተዘጋጀ መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

የመቀሌ ከተማን በፌደራል መንግሥቱ ሃይሎች መያዝ ተከትሎ በሕዳር ወር ለመንግስት እጃቸውን የሰጡት ወ/ሮ ኬሪያ የሕወሓትን የጦርነት ዕቅድ እንዲሁም ድርጅቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲፈፅማቸው ነበሩ ለተባሉ የተደራጁ ጥቃቶች ብሎም ከጦርነቱ ሽንፈት በኋላ ወደ በረሃ የተደረገውን ሽሽት የተመለከቱ “ቁልፍ መረጃዎችን” ለመንግስት “በፈቃደኝነት ሰጥተዋል” ይላል ዋዜማ ያገኘችው መረጃ። መንግስት ወ/ሮ ኬሪያ ሰጡኝ ያለው መረጃ እጅግ ጠቃሚና ዋና ዋና የሕወሓት አመራሮችን ለመያዝና ሌሎቹንም ለመግደል እንዳስቻለው ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ይገልፃሉ።

ወ/ሮ ኬሪያ ለመንግስት በሰጡት “ጠቃሚ መረጃ” ና አሳዩት በተባለ ከፍተኛ የትብብር መንፈስ የሕወሓት መሪ በመሆናቸው ቀርቦባቸው የነበረውን ክስ በማንሳት የኢትዮጵያ መንግስት ሕግ በሚፈቅደው መሰረት በሕወሓት መሪዎች ላይ ምስክር ለመሆን “ስምምነት” ላይ ደርሰው እንደነበር ተሰምቷል። ወ/ሮ ኬሪያም መንግስት ጥበቃ ሊያደርግላቸውና የተወሰኑ ጥቅማ ጥቅሞችን ሊሰጣቸው፣ እሳቸው ደግሞ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው ለመቅረብ ተስማምተው እንደነበር የመንግሥት የመንግሥት ምንጮች ይናገራሉ። ወ/ሮ ኬሪያ ከእስር የተለቀቁት በዚህ ስምምነት መሰረት ነበር።

መንግስት ወ/ሮ ኬሪያ ሰጡኝ ያለው መረጃ እጅግ ጠቃሚና ዋና ዋና የሕወሓት አመራሮችን ለመያዝና ሌሎቹንም ለመግደል እንዳስቻለው ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ይገልፃሉ።

በእስካሁኑ ሂደት በቪዲዮ በተቀረፀ የምርመራ ቃላቸው ሕወሓት በተለያየ ጊዜ በምስጢር ያደረጋቸውን ውይይቶች፣ የተደረሰባቸውን ስምምነቶች እንዲሁም የጦር መሳሪያ ክምችትን፣ የገንዘብ ዝውውርን፣ ስውር የንግድ እንቅስቃሴዎችን የሚመለከቱ መረጃዎችን ለፌደራል ፖሊስ መርማሪዎች በዝርዝር መናገራቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የሕወሓት ስራ አስፈፃሚ እና ማእከላዊ ኮሚቴ መቀሌ ከተማን ለቆ ወደ በረሃ ለመሸሽ በወሰነበት ጊዜ አመራሮቹ የት መደበቅ እንዳለባቸዉ የተወሰነውን ዉሳኔ በዝርዝር የገለፁበት መረጃና ምስክርነት ከሌሎች መረጃዎች ጋር ተጣምረው መንግስት ሲወስዳቸው ለነበሩ ወታደራዊ እርምጃዎች “እጅግ ጠቃሚ” እንደነበሩና ይህ ትብብር መንግስት ከወ/ሮ ኬሪያ ጋር “ስምምነት” እንዲደርስ መተማመኛ ሆኖት እንደነበረ ሰምተናል።

ይህ አይነቱ ከተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ ጋር የሚደረግ ስምምነት በተለያዩ ሀገሮች የሚሰራበት ሲሆን በኢትዮጵያም ይህን አስራር የሚደግፍ የህግ አግባብ መኖሩን ባለሞያዎች ይናገራሉ። የጠቋሚዎች እና ምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንድ ምስክር ጥቆማ በሰጠበት ጉዳይ እንዳይከሰስ ጥበቃ እንዲደረግለት ጠይቆ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጥበቃዉን ለመወሰን እንደሚችል ደንግጓል። ከወ/ሮ ኬሪያ ጋራ የተደረገው ስምምነት በዚህ ሕጋዊ መነሻ ላይ የተመሠረተ እንደነበር አቃቤ ሕግ ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል።

ይሁንና ወ/ሮ ኬሪያ ትናንት ግንቦት 17 ቀን ዓ.ም የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የምስክርነት ቃል ለመስጠት ቀርበዉ እያለ ምስክር ለመሆን ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ለፍርድ ቤት ገልፀዋል፡፡

አቃቤ ሕግ የወ/ሮ ኬሪያ እምቢታ የስምምነት መፍረስን ያቋቁማል ከሚል ድምዳሜ መድረሱን ሰምተናል። ስለዚህም ሕጋዊ መሰረት ያለው ስምምነት በወ/ሮ ኬሪያ በመፍረሱ ሲያደርግላቸው የነበረውን የምስክር ልዩ ጥበቃ በማንሳት ቀድሞ እንዲቋረጥ ተደርጎ የነበረው ክስ እንዲቀጥል ከውሳኔ መድረሱን ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ሰምታለች። [ዋዜማ ራዲዮ]


ማስታወሻ፣ ለመረጃ ግልጽነት ሲባል በዚህ ዜና ላይ አነስተኛ የሰዋስው ማስተካከያ ተደርጎበታል።