Meaza Ashenafi

ዋዜማ ራዲዮበሙስና፣ በመልካም አስተዳድርና አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም በአጠቃላይ የፍርደ ቤት ሂደት ውስጥ ክስ የቀረበባቸው ከ 300 በላይ የፌደራል ዳኞች ጉዳያቸው በፌደራል ዳኞች አስተዳድር ጉባዔ መታየት የነበረበት ቢሆንም ክሳቸው ዕልባት ሳያገኝ በስራ ላይ መቀጠላቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 

በፌደራል ዳኞች ላይ ክስ ሲቀርብ መልስ መስጠት የሚጠበቅበት የዳኞች  አስተዳድር ጉባዔ  እነዚህ ክስ የቀረባባቸው ዳኞች በተከሰሱበት ጉዳይ ህግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ የነበረበት ቢሆንም እሰካሁን በተከሰሱበት ሳይጠየቁ ስራቸውን እያከናወኑ መሆኑን የፍትህና ህግ ኢንስቲዩት ያደረገው የዳሰሳ ጥናት አጋልጧል፡፡

የፌደራል  የፍትህና ህግ ኢንስቲትዩት የፌደራል የፍትህ ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ፣ የመልካም አስተዳድርና የተገልጋዩ ህዝብ እርካታን በተመለከተ ጥናት እንዲያካሂድ ከህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በቀረበለት ጥያቄ መሰረት ላለፉት አምስት ወራት ያካሄደውን የጥናት ውጤት ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ይፋ አድርጓል፡፡

የፍርድ ቤቶችን አጠቃላይ ጥናት በተመለከተ ጥናቱን ያቀረቡትና የኢንስቲትዩቱ የሀግ ባለሙያ  አቶ ሙሉዓለም አበራ፣ ክስ የቀረበባቸው 300 ዳኞች ላይ የቀረቡት ክሶች ጉቦና ጥቅማጥቅም መጠየቅ፣ የመዝግብ መጥፋት፣ ሙስና፣ አለአግባብ ስልጣንን መጠቀምና ደንበኞች ላይ በደል ማድረስ፣ በራስ አስተያየት መወሰን፣ የገለልተኝነት ችግር፣ ማስረጃን በአግባቡ አለመመርመርና መሰል ጉዳዮች ለፌደራል ዳኞች አስተዳድር ጉባዔ ቀርቧል።

ህዝቡ ተቸገርኩ ብሎ ክስ ያነሳባቸው ዳኞች ሳይጠየቁ አሁንም ተከሳሾቹ በስራ ላይ መሆናቸውን አግባብ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዳኞቹን ተጠያቂ ማድረግ ያልተቻለው የፍርድ ቤቶች የውስጥ ምርመራ ቡድኖች ጠንካራ አደረጃጀት ሰለሌላቸው ሲሆን በሌላ በኩል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ደግሞ ይህኛው ስራ የትርፍ ጊዜ ስራ በመሆኑ ጉዳዩን ተከታትሎ ማስፈፀም ባለመቻሉ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

የፍርድቤት ስራ ነጻ ነው ተብሎ በህገ-መንግስቱ ሲቀመጥ ከተሰጠው ነፃነት ልክ ተጠያቂነት አለበት የሚሉት ጥናት አቅራቢው ይህ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ የሚችለው አንድም በተቋማት  የውስጥ ምርመራን ወይንም በፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በኩል  ብቻ እንደሆነ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጅ ከባድ እና ቀላል የሥነ ምግባር ጥሰት ክስ ጉዳዮችን ለማጣራትና ውሳኔ ለመስጠት ኃላፊነት የተጣለበት የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በጉዳዩ ላይ መፍትሄ ለመስጠት ባለመቻሉ ተከሳሽ ዳኞቹ አሁንም በስራ ላይ  መሆናቸውን አቶ ሙሉ ዓለም ተናግረዋል፡፡

አንድ ዳኛ ክስ ቀርቦበት ጥፋት መፈጸሙን የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ሲያረጋግጥና ተፈጻሚነት ያለው በልዩ ሁኔታ ሊታይ የሚችል የቅጣት ማቅለያ ካልተገኘ፣ የዳኛው የይግባኝ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ ወዲያውኑ ከዳኝነት ኃላፊነት እንዲሰናበት ጉባዔው ለተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ እንደሚያቀርብ በ2013 ዓ.ም በወጣው የፌደራል ዳኞች የሥነ-ምግባርና የዲስፕሊን ክስ ሥነ-ሥርዓት ደንብ ተደንግጓል፡፡

መሰረታዊ አገርዓቀፍና ዓለምዐቀፍ የፍርድቤት አገልግቶች መለኪየዎችን መሰረት በማድረግ ለ አምስት ወራት እንደተካደ የተገለፀው ይህ ጥናት፣ በአጠቃላይ  በፍርድ ቤቶች ውስጥ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያሳየ ሲሆን፣ በርካታ  የፍርድቤት ሰራተኞች በቅርቡ በፍትህ ተቋማት ተካሄደ የተባለውን የለውጥ (reform) ስራና በተቋማት ውስጥ የሚከናወኑ ስራዎችን በተመለከተ ሲጠየቁ ስለጉዳዩ ምንም መረጃ እንደሌላቸው በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

በዚሁ ጥናት ይፋ በተደረገበት ቀን ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከከፍተኛ ፍርደቤት፣ ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የመጡ ከፍተኛ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን ከቀናት በፊት በጠቅላይ ሚንስትር አብይ (ዶ.ር) አህመድ “አንደኛ ደረጃ ሌቦች ዳኞች ናቸው” በሚል ያቀረቡት ንግግር በተመለከተ በመድረኩ ምንም አይነት ነገር አልተነሳም፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]