ዋዜማ ራዲዮ- ጥር 24/ 2012 ዓም ከደንቢ ደሎ ዩንቨርስቲ የታገትን ተማሪዎች እኛ ነን በማለት የተሳሳተ የሀሰት ወሬ አውርተዋል ተብለው ተጠርጥረው የካቲት 3 ከባህርዳር ከተማ ተይዘው ለፌደራል ፖሊስ ተላልፈው የተሰጡት ና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በእስር ላይ የሚገኙት የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ 2 ሴት ተማሪዎች ቅድስት በጋሻው እና ሸዋዬ ጌትነት ለ 3 ጊዜ በአራዳ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው የ10 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተሰጠ።


የካቲት 25 ረፋድ ላይ በአራዳ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው “ፖሊስ ምርመራዬን አልጨረስኩም፣ የምስክር ቃል እቀበላለው፣ተባባሪዎቻቸውን የነበሩትን መያዝ አለብኝ ፣የስልክ ምርመራ እንዲሰጠኝ ወደ ኢንሳ ደብዳቤ ልኬ መልስ እየጠበኩ ስለሆነ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ” ሲል ችሎቱን ጠይቋል።


ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ ልጆቹን ከተረከበበት ቀን ጀምሮ ተመሳሳይ ስራዎችን ነው እየሰራ ያለው ስለዚ የጠየቀው የምርመራ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ደንበኞቻችንን አስሮ ለማቆየት ነው። ፖሊስ በቂ ስራ አልሰራም ስለዚ የጠየቀው የምርመራ ጊዜ መሰጠት የለበትም ሲሉ የተከራክረዋል አክውም ፖሊስ ተጨማሪ ስራ ይቀረኛል የሚል ከሆነ ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና ወተው ክሳቸውን ይከታተሉ ሲሉ ተከራክረዋል።


የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ችሎት የፖሊስ የምርመራ መዝገብ አይቶ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 27 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቶ ነበር ።
ዛሬ ረፋድ ላይ አራዳ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የፖሊስ መዝገብን ተመልክቶ ከጉዳዩ ውስብስብነት ና ክብደት አንፃር ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና ቢወጡ ተመልሰው ይመጣሉ ብለን ስለማንገምት 10 ተጨማሪ የምርመራ ግዜ ለፖሊስ በመስጠት ለመጋቢት 7/ 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰቷል።


ተጠርጣሪዎቹ ለ3 ጊዜ በአራዳ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የቀርቡ ሲሆን የመጀመሪያ ችሎታቸውን የካቲት 4/ 2012 ቀርበው 11ቀን የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ የተፈቀደ ሲሆን በሁለተኛ የጊዜ ቀጠሮ የካቲት 15/ 2012 ፖሊስ ምርመራዬን አልጨረስኩም በማለቱ ችሎቱ ተጨማሪ የ8 ቀን የምርመራ ጊዜ ሰቶ ለየካቲት 25 2012 ተለዋጭ ቀጠሮ እንደተሰጠ የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ ያስረዳል። [ዋዜማ ራዲዮ]