የዞን ዘጠኝ ጦማርያን መፈታትን ተከትሎ በኢትዮዽያ ውህኒ የሚማቅቁ ሌሎች ጋዜጠኞች ጉዳይ ተገቢውን ትኩረትና ድጋፍ እንዳላገኘ የሚያመላክቱ ፍንጮች እየታዩ ነው። አለም አቀፍ ተቋማትም ሆኑ የመብት ተቆርቋሪ ወዳጆች ስለ ቀሪዎቹ ታሳሪዎች አስታዋሽ የሚፈልጉ ይመስላሉ።

(መዝገቡ ሀይሉ ያሰናዳውን የድምፅ ዘገባ እዚህ ያገኙታል)

በኢትዮጵያ መንግስት የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች አያያዝ ኹኔታ እየከፋ መምጣቱን ከታሳሪዎቹ ቤተሰቦች በሚሰሙ ቅሬታዎች እየተተገለጹ ነው። ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የጋዜጠኛው ተመስገን ደሳለኝ ቤተሰቦች ተመስገን ከጤናው መታወክ በተጨማሪ በቤተሰቦቹ እንዳይጎበኝና ምግብ እንዳይገባለት በመደረጉ ያለበትን እስር የከፋ ደረጃ ላይ እንዳደረሰው ተናግረዋል። ቤተሰቦቹ ከሚኖሩበት 165 ኪሜ ርቀት ላይ በሚገኘውየዝዋይ እስር ቤት የታሰረው ተመስገን ይህን ያህል ርቀት እየተመላለሱ እንዲጠይቁትና ስንቅ እንዲያቀብሉት በተገደዱት የቤተሰቡ አባላት ላይ የተጣለው እገዳ ተጨማሪ መንገላታት እንዳመጣባቸው ይናገራሉ።

ተመስገን ደሳለኝ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ

Temesgen ከጥቅምት 3/2007 ዓ.ም ጀምሮ የመንግስትን ስም ማጥፋት፣ ህዝብን ማነሳሳትና የህዝብን አመለካከት ማናወጥ በሚሉ ሶስት ክሶች፣ የቅጣት ርዝመት 3 አመት ጽኑ እስራት

ይህን የመሰለው ድርብ ቅጣት በተመስገን ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች ይህን የመሰለ ችግር እየደረሰባቸው እንደኾነ ሲነገር ቆይቷል። ሌላው ታሳሪ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም ይህን የመሰለድርብርብ ቅጣት እንደተጣለበትም ይነገራል። በሽብርተኝነት ሴራ ተካፍለሃል በሚል ሰበብ የ18 ዓመት እስር የተፈረደበት እስክንድር በተመሳሳይ ኹኔታ በቤተሰቡና በጓደኞቹ እንዳይጎበኝ ከመደረጉም በተጨማሪየሚያነበው መጽሐፍ እንዳይገባለትና ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዳይገናኝ ማዕቀብ ሲጣልበት መቆየቱም ሲዘገብ ነበር። ከዚህም በላይ በተደጋጋሚ በጭለማ እስር ቤት ውስጥ እንዲቆይ ሲደረግ ቆይቷል።

መታሰሩ በራሱ የከፋ የመብት ጥሰትና በደል ሆኖ ሳለ ስለምን ነውረኝነት የተቀላቀለበትና የበቀል አያያዝ በጋዜጠኞች ላይ ይበረታል?  የሚለው ጥያቄ – መልሱ ……የኢህአዴግ መንግስት ለዜጉቹ ባለው ዝቅ ያለ አመለካካትና ጥቂቶች ለስልጣናቸው ባላቸው ስስት ሳቢያ ነው።

እስክንድር ነጋ
ሳተናው፣ ወንጭፍ እና ምኒልክ የተባሉ ጋዜጦች አዘጋጅEskinder Nega with his Son Nafkot
ጥፋተኛ የተባለበት ወነጀል ከአሸባሪነት ጨምሮ 23 ወንጀሎች
የቅጣት ውሳኔ የተሰጠበት ጊዜ ሐምሌ 6/2004 የኢትዮጵያ ፌዴራል ፍርድ ቤት
የቅጣት ርዝመት ለ18 ዓመታት

የውብሽት ደሳለኝ አያያዝም ከዚህ የተለየ አይደለም። ዘላለም ወርቃአገኘሁ፣ ዮናታን ተስፋዬና ባህሩ ደጉ በኢንተርኔት ደህንነት ዙሪያ ስልጠና ይሰጣል የሚል መረጃ ደርሷቸው፣ በስልጠናው ለመወዳደር ማመልከቻ በመፃፋቸው የአሸባሪነት ክስ ቀርቦባቸው ከአንድ አመት በላይ ወህኒ እየተንገላቱ ነው።
“የፖለቲካ እስረኞች የሉም፣ ማንም ሰው በሚጽፈው ነገር ምክንያት ወይም ባለው የፖለቲካ አመለካከት ሰበብ አልታሰረም”  እያለ የሚክደው የኢትዮጵያ መንግስት ይህን የመሰለውን ተደራራቢ ቅጣት በእነኚህና በሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች ላይ መፈፀሙ ሰለሀገሪቱና ስለዜጎቹ ያለውን ዝቅ ያለ አመለካከት ያንፀባርቃል።

በእስረኞቹ ላይ ይህን በቀለ መሰል ተደራራቢ ቅጣት መፈጸሙ ለብዙዎች በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚቀርበው ክስ ፖቲካዊ ለመኾኑማረጋገጫ ነው። እነዚህን ታሳሪዎችም ከሌሎች እስረኞች በተለየ አደገኛ ናቸው ብሎም እንደሚሰጋ የሚያሳይ ድርጊት እንደሚፈጸምባቸው ማሳያ እንደኾንም ለብዙዎች የማያከራክር ጉዳይ ነው።

ውብሸት ታዬ
የአውራምባ ታይምስ ምክትል-ዋና አዘጋጅWubshet
የታሰረው ሰኔ 2003 አ.ም
ጥፋተኛ የተባለበት ወንጀል በሽብርተኝነት ክስ
የጥፋተኝት ፍርድ የተሰጠበት ጊዜ ጥር 2004
የቅጣት ርዝመት 14 አመት ፡፡

የዞን 9 ጦማርያንና አብረዋቸው ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞች ጉዳይ ባልተጠበቀ ኹኔታ መንግስት የቀረበባቸውን ክስ በመተው ከክሱ ነጻ ናቸው የሚል ብያኔ ተሰጥቶ ከእስር ከመፈታታቸው በፊት ይህንኑ መሰል የተለየበደል ሲፈጸምባቸው እንደነበረ ሲነገር ቆይቷል። በቅርቡ የዞን 9 ጦማርያንና የጋዜጠኞቹን መፈታት እንደ ተስፋ ሰጪ በጎ ጅምር አድርገው የተመለከቱት ቢኖሩም እስካሁን ድረስ ሌሎቹ የፖለቲካ እስረኞችእንደሚፈቱ የሚያሳይ ፍንጭ የለም። በእስር ላይ ያሉበትም ኹኔታ ከቀድሞው በምንም ያልተለየ እንዲያውም እየባሰ መምጣቱን የችግሩ የቅርብ ገፈት ቀማሽ የኾኑት ቤተሰቦቻቸው እየተናገሩ ነው።

ዘላለም ወርቃገኘሁ ፣ ዮናታን ወልዴ ፣አብረሃም ሰለሞን እና ባህሩ ደጉZelalem Workagegnehu
ጥፋት የኢንተርኔት ደህንነት ስልጣና ለመካፈል ማመልከት
ክስ ሽብር ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኘነት
የታሰሩት ሀምሌ 2006

 

 

የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና አብረዋቸው ታስረው የነበሩት 3 ጋዜጠኞች ባልተጠበቀ ኹኔታ የመፈታት ጉዳይ አንዳንድ ተንታኞች ዘንድ በገዥው ፓርቲ ውስጥ በተፈጠረ ድንገተኛ ለውጥ ምክንያት የተወሰደ ርምጃ ሊኾን እንደሚችል ግምት አሳድሮ ነበር። ይኹንና ይህን የመሰለ የአቋም ለውጥ መምጣቱን የሚያሳይ ቀጣይ ርምጃ ሲወሰድ አልታየም። ብዙዎችን የሚያስማማው ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት በዞን 9 ጦማርያንና በተፈቱት ሌሎች ጋዜጠኞች ባቀረበው ክስ ምክንያት የደረሰበትን ዓለማቀፋዊ ተጽዕኖ ለማርግብ ሲል ብቻ ይህን ያልተጠበቀ ውሳኔ ማሳለፉ ነው። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጉብኝትም ይህንኑ ዓለማቀፋዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ደረጃ ላይ አድርሶት እንደነበረ ይጠቀሳል።

ለዚህ ዓለማቀፋዊ ተጽዕኖ ምክንያት የነበረው ከሌሎች የፖለቲካ እስረኞች በተለየ ለዞን 9 ጦማርያን  ይደረግ የነበረው ዘመቻ #Freezone9bloggers በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በዓለማቀፍ ደረጃም ሲወዳደር ብዙ ተሳታፊዎች የነበሩት እና ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት የሳብም ነበር።

በአገር ውስጥ ካለው ስም ይልቅ በውጪው ዓለም ላለው ገጽታው የሚፈራ የሚመስለው የኢትዮጵያ መንግስት እያንዳንዱ የፍርድ ሂደት እየተመዘነ የፈጠራ ክሶቹ ለስላቅ በመዳረጋቸው ባልጠበቀው ተጽዕኖ ስር መውደቁ ይህን ከባህርይው ውጪ የኾነ ውሳኔ እንዲወስን ያስገደደው ይመስላል።

በተመሳሳይ ክስ ወንጀለኞች የተደረጉት ዘላለም ወርቅአግኘሁና ሌሎች 3 ጓደኞቹ አለመፈታታቸውም በመንግስት በኩል የተደረገ የአቋም ለውጥ አለመኖሩን ማሳያም ተደርጎ ይቀርባል።
ዘላለም ወርቅአግኘሁና ጓደኞቹ የቀረበባቸው ክስ የኢንተርኔት ደኅንነት (Internet Security) ስልጠና ለመውሰድ ማመልከታቸው ነው። ይህንንም መሰል ክስ በዞን 9 ጦማርያን ላይ ቀርቦ የነበረና መንግስትንም ለከፍተኛ ትችት ያጋለጠው መከራክርያው ነበር።

ይህን ስልጠና መውሰድም ይኹን ተግባራዊ ማድረግ ከማንኛውም ኢንተርኔት ተጠቃሚ ግለሰብ የሚጠበቅና የኢሜይል መልዕክቶችንም ይኹን በኢንተርኔት የሚደረጉ ማንኛውንም የመረጃ ልውውጦች በጠላፊ ወይም ሀከር እንዳይጠቃ የመጠበቅ የኢንተርኔት ሀ ሁ ነው። ብዙ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይህን ስልጠና ለጋዜጠኞችና ሰበአዊ መብት ተሟጋቾች ቢሰጡትም እንደ ወንጀል ሲቀርብ የታየው ግን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን አይቀርም። ዘላለም ወርቅአገኘሁና ጓደኞቹም ይህን ስልጠና ለማግኘት ያላቸው ምኞት ብቻ ከወንጀል ተቆጥሮ ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ላይ እንዲቆዩ አድርጓቸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ሐሳብን በነፃነት መግለጽንና የፈለጉትን የፖለቲካ አቋም መደገፍን ወንጀል አድርጎ እንደሚቆጥር በተደጋጋሚ ቢከሰስም የዞን 9 ጦማርያንን በተመለከተ የተደረገውን ዓይነት ውጤታማ ዘመቻ ተደርጎበት አያውቅም።

አሁን በተመስገን፣ በእስክንድርና በነዘላለም ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ሲገልጹ የሚታዩት በዋነኝነት የቤተሰቦቻቸው አባላትና የቅርብ ጓደኞቻቸው ናቸው። ዓለማቀፍ የመብት ተሟጋች ቡድኖችም ችግሩ በዞን 9 ተጀምሮ በእነርሱ መፈታት ያቆመ ይመስል ድምጻቸውን ብዙም አያሰሙም። አንዳንድዕቹ የድረገጽ መረጃዎቻቸውን እንኳን ወቅቱን በጠበቀ መረጃ አላስተካከሉትም።

የእነዚህ እስረኞች ጉዳይ የቤተሰቦብቻቸው ችግር ብቻ ተደርጎ መተዉም ጉዳዩን በአገር ደረጃ ካለው የለውጥ ጥያቄ የነጠለው ይመስላል። በዚህ ወቅት ለዞን 9 ጦማርያን የተደረገውን ውጤታማ ዘመቻ ለመቃኘትና ለመብት መከበር ብለው ዋጋ እየከፈሉ ላሉ ጋዜጠኞች፣ ጦማርያን፣ የመብት ተሟጋቾችና የፖለቲካና የሐይማኖት መሪዎች አዲስ ዘመቻ የሚጀመርበት እንጂ ጉዳዩ የተደመደመ አይመስልም።

 

የአዘጋጁ መልዕክት፡ ይህን ዘገባ ካጠናቀርን በኋላ ፍሪደም ሀውስ በተባለው የመብት ተቆርቋሪ ድርጅት በኩን የዞን ፱ ጦማርያን መፈታት በኢትዮዽያ ያለው የፍት ህ ችግር ማብቂያ አለመሆኑን የሚገልፅ ፅሁፍ አውጥቷል። በዚህ ማስፈንጠሪያ ልታነቡት ትችላላችሁ- https://freedomhouse.org/blog/ethiopia-acquittal-bloggers-has-not-ended-repression