Copy Right- Yohannes Bayou
Copy Right- Yohannes Bayou

በኢትዮጵያውያን ሰዓልያን የተሠሩ ሥራዎችን የያዘው የድረገጽ ጋለሪ 19 ሰዓልያን የተሰሩ የስዕል ሥራዎችን ለሽያጭ አቀረበ።ለረጅም ጊዜ ልዩ የኾነውን የአገሬን ገጽታ በማያቋርጥ ሒደት ውስጥ ካለው የኢንተርኔት ዓለም ጋር የሚያገናኝ አንድ ነገር ለማድረግ ስሻ ቆይቼ ነበርበምትለው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሶፍያ ይልማ ማርቲን የተቋቋመው The Next Canvas. com የሚባለው ድረ ገጽ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ስራቸውን ለዓለም የሚያቀርቡበት አዲስ መድረክ ፈጥሯል።

ይህ እንደ ድረ ገጽ ጋለሪ የሚያገለግለው የኢንተርኔት መድረክ እስካሁን 19 ወጣት ሰዓልያን የተሰሩ የሥዕል ሥራዎችን ይዟል።ሶፍያ በድረገጹ የማስተዋወቂያ መልዕክቷ እንደጻፈችው፤ ኢትዮጵያ ብዙ ልዩ የሚያድርጓት ነገሮች ያሏት አገር ናት። ከነዚህም ልዩ የኾኑ ነገሮች አንዱ የሥነ ጥበብ ሥራዎቿ ናችው። በኢትዮጵያውያን ሰዓልያን የሚሰሩት የሥነ ጥበብ ሥራዎች ከዚሁ የተለየ ማንነትና ባሕል የሚመነጭ ልዩ ባሕርይ አላቸው። ሥዕልን እንደ ታሪክ መንገሪያ ለሚወስዱትም ሰዎች እነዚህ ሥዕሎች የሚትርኩልን ልዩ ታሪክ አላቸው። 

(መዝገቡ ሀይሉ ዝርዝር ዘገባ አለው አድምጡት)

 

ድረ ገጹን ለሚጎበኝ ማንም ሰው በድረ ገጹ ያሉትን የሥዕል ስብስቦች ማየት የሚፈጥረው ልዩ ስሜት አለ። በውብ ቀለማት የደመቀውን እና ከማንነታችን ጋር በጣም የተቆራኘውን የሰዓልያኑን ዕይታ በአዕምሯችን ካለው የትዝታችን ስዕል ጋር እያገናኘን እንድንደነቅ የሚያደርግ አዲስ አጋጣሚ አዲስ መላ ፈጥሮ በኮምፒውተራችን መስኮት ካለንበት መጥቷል። 

የደብረ ብርሃን ብርድ ልብስ፣ የጠጅ ቤት ሁካታ፣ የተመላለስንባቸው የአዲስ አበባ መንገዶች፣ ታክሲዎችና አውቶብሶች፣ የቤተክርስቲያን አጸድና ቅዳሴ፣ በዘንቢል የታጠሩ የዓመት በዓል ዶሮዎች፣ ገበያውና ሙዚቃው ሁሉ የለመድነው የሕይወት ውጣ ውረድ በለመድነው የሕይወት ቀለም ነፍስ ዘርቶ ለዕይታ ቀርቦልናል። አቀራረቡ ሥዕሎቹን በኮምፒውተር ስክሪን ማየት ብቻ ከሚፈጥረው ደስታ በተጨማሪ አቀራረቡ ብዙዎቹን የመግዛትና የራስ የማድረግ ምኞትንም ይፈጥራል። የሥዕሎቹም ዋጋ ያን ያህል ውድ የሚባል አይደለም። 150 እስከ 1 ሺህ ስምንት መቶ የአሜሪካ ዶላር የሚሸጡት እነዚህ ስዕሎች ብዙዎቹ የተሸጡ መኾናቸውን የሚገልጽ ምልክት ተደርጎባቸዋል።

copyright-KIDIST BIRHANE
copyright-KIDIST BIRHANE

ኢትዮጵያውያን ከአገራቸው ርቀው ቢሔዱም ሊላቀቁት የማይችሉትና ይዘውት የሚሔዱት የማንነታቸው መገለጫ ብዙ ነው። ብዙውን ጊዜ ይህንን ናፍቆት የመወጣት ሙከራው የሚያዘነብለው ከአገር ቤት ይዘውት በሚወጡት የምግብና የባሕል ልብስ ላይ ነው። ወደ ሥነጥበብ የሚጠጋ ሙከራም ከተደረገ የሙዚቃ ድግስ ማዘጋጀት ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዝ ነገር ነው። ኮሜዲም በመጠኑ ወደዚሁ መድረክ እየመጣ መታየት ጀምሯል። 

ከሥነ ጥበብ ዘርፎች መካከል ሥዕልንና ቅርጻ ቅርጽን ከአገር ውጭ ወዳሉ ኢትዮጵያውያንም ይኹን የሌላው ዓለም የጥበብ አፍቃርያን ለማድረስ የተደረጉ ሙከራዎች ሲጠቀሱ አይሰማም። እነዚህን ሥራዎች አጓጉዞ የሥዕል ኤግዚቢሽን ማሳየት ፈታኝ መኾኑ የሥነ ጥበብ ሥራዎቹን ከአገር ቤት እንዳይወጡ እንቅፋት ሳይኾንባቸው አልቀረም።

ይህ ሶፍያ ማርቲን የጀመረችው የኢንተርኔት ጋለሪ ይህን ችግር ሊፈታ የሚችል የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያገዘው አስፈላጊ ሙከራ ነው። ሶፍያ መርጣ በድረ ገጿ ላይ የምታሳያቸው ሥራዎች 19 ወጣት ሰዓልያን የተገኙ ሥራዎችን ብቻ ነው። የኢትዮጵያ አርቲስቶች በብዛትም ይኹን ባላቸው የሥነጥበብ ዝንባሌ ልዩነት በዚህ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም። ይህ የሶፍያ ጅማሬ ምናልባት የወደፊቱን የኢትዮጵያን ሥነጥበብ የማስተዋወቂያ መንገድ እንደ አንድ ፈር ቀዳጅ እና ትልቅ ተስፋ ሰጭ  ርምጃ መውሰድ ይቻላል።