FILE

ዋዜማ ራዲዮ- ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ለድርጅቱ አመራሮች ባሰራጨውና ውይይት ባደረገበት ሰነድ ላይ እንዳመለከተው ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ አዲስ መንግስት ካቋቋሙ በኋላ በቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ የፖለቲካ ኀይሎች ጋር ድርድርና ውይይት ለማድረግ ተዘጋጅተዋል ብሏል።

የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን በኢትዮጵያ ለመገንባት በሚያዚያ 2010 ዓ. ም. ለውጥ ቃል በተገባው መሰረት ሁለት ረድፍ ያለው የተሀድሶ ፕሮግራም ለማድረግ ብልፅግና መዘጋጀቱን ዋዜማ በተመለከተችው ሰነድ ይጠቁማል። አንዱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ለማስፋት የሚወሰደው እርምጃ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን አዲስ በሚመሰረተው የፌደራልና የአካባቢ መንግስታት መዋቅር ውስጥ በማካተት ተሳትፏቸውን ማሳደግ የዲሞክራሲ ልምምድን ማድረግ ነው።

ሌላው እርምጃ በሀገሪቱ ያለመግባባትና የግጭት ጭምር ምክንያት በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፖለቲካ ድርጅቶች ሲቪል ማህበራት ምሁራንና መገናኛ ብዙሀን የተሳተፉበት የብሄራዊ መግባባት ውይይት መጀመር ነው። በዚህ ውይይት ሕገመንግስቱን ጨምሮ ሰንደቅ አላማ ፣ብሄራዊ መዝሙር፣ ብሄራዊ በዓላት እና ሌሎችም ጉዳዮች ተነስተው መግባባት ላይ የሚደረሰበት ነው።

ሕገመንግስቱ ከቀዳሚ አጀንዳዎች መካከል እንደሚሆን ነገር ግን አጀንዳዎችን የመምረጥና ቅደም ተከተል የማስያዙ ስራ የድርድሩ አንድ አካል እንደሚሆን በሰነዱ ተብራርቷል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በአዲሱ መንግስት ለማሳተፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተፈለገው መጠን ማሳተፍ እንደማይቻልና ሌሎች ተሳትፎን ለማሳደግ የሚረዱ መድረኮች እንደሚመቻቹ የብልፅግና ሰነድ ያትታል።
ሰነዱ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲደርስ መደረጉን ዋዜማ ከምንጮቿ ተረድታለች።

” ምንም እንኳን ምርጫው ውጤታማ በሆነ መልኩ ቢካሄድም የተጀመረው ዴሞክራሲያዊ ሽጝርን የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጨማሪ እርምዎች መወሰድ አለባቸው፡፡ በርካታ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለፌደራልና ክልል ም/ቤቶች እጩ ማቅረብ ቢችሉም፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምክር ቤቶች ያላቸው ውክልና አነስተኛ ሆኗል፡፡ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ዝቅ ያለ ውጤት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕብረት አለመፍጠራቸውና ገዢው ፓርቲ በሥልጣን ላይ መሆኑ የሚሰጠው ጥቅም ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ገዢው ብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ሽግግሩን ከማጠናከር አኳያ በተለያዩ መንገዶች የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ከፍ ማለት እንዳለበት ከልብ ተቀብሎታል” ይላል ሰነዱ

በሰሞኑ የክልል ምክር ቤቶች ምስረታ ላይ አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መቀመጫና የተለያዩ ሹመቶችን እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን በመጪው ሰኞ በሚመሰረተው የፌደራል መንግስት ውስጥም የተወሰኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እንደሚደለደሉ ዋዜማ ያላት መረጃ ያመለክታል።

በመንግስት ምስረታ ማግስት እንደሚደረግ በሚጠበቀው የብሄራዊ መግባባት ድርድር ከመንግስት ጋር ጦርነት የገጠመው ሕወሓት ይሳተፍ እንደሆነ ስነዱ ያብራራው ነገር የለም።


” አገራዊ መግባባት እና የተሳካ አገረ፡መንግሥት ግንባታ ሁሉም ፖለቲካ ኃይሎች (ሰላማዊ የትግል ስልት የሚከተሉ) በጋራ ተቀራርበው መስራት የሚጠይቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው፡፡ የአንድ ዘመን ትውልድ ስራ ብቻም ሳይሆን ዘመን ተሻጋሪ በትውልዶች ቅብብሎሽ የሚሰራ ታላቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ በአገራዊ መግባባት ዙሪያ የሚሰራው ተግባር በውስን ኃይሎች ዙሪያ ሳይታጠር አካታች እና ሁሉ አቀፍ በሆነ መንገድ መከወን ይገባል” ሲል ያብራራል የፓርቲም ምክረ ሀሳብ ሰነድ። [ዋዜማ ራዲዮ]