Development Bank of Ethiopia- FILE
  • በስድስት ወራት ውስጥ ያገኘው ትርፍ የእቅዱን 3.4 በመቶ ሲሆን ተጨማሪ 100 ሚሊየን ብርም የተበላሸ ብድር ውስጥ ገብቷል

ዋዜማ ራዲዮ- ከበርካታ ዓመታት ብልሹ አሰራርና የኪሳራ ጉዞ ተላቆ  ባለፈው አመት ከፍተኛ የተባለውን 3.4 ቢሊየን ብር ትርፍ አስመዝግቦ የነበረው ልማት ባንክ የዚህ በጀት አመት የመጀመርያ ስድስት ወራት አፈጻሙ ከፍተኛ ማሽቆልቆል እንደገጠመው ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ መረዳት ችላለች።

የልማት ባንኩ በ2014 አ.ም በጀት አመት የመጀመርያ ስድስት ወራት ከታክስ በፊት 1.3 ቢሊየን ብርን ለማትረፍ አቅዶ ተንቀሳቅሷል። ሆኖም በተጠቀሰው ጊዜ ባንኩ ማትረፍ የቻለው 47 ሚሊየን ብር ብቻ ነው። በመቶኛ ሲቀመጥም የእቅዱን 3.4 በመቶ ብቻ ነው ማትረፍ የቻለው። ይህም በበጀት አመቱ መጨረሻ ላይ የሚኖረው አፈጻጸም ስኬታማ ስለመሆኑ ከወዲሁ አጠራጣሪ አድርጎታል።

የመረጃ ምንጮቻችን እንደነገሩን ከሆነ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጀት አመቱን ሲጀመር በመበላሸት ላይ ያለ ወይንም መመለሱ አጠራጣሪ የሆነ ብድር መጠኑ 20.8 ቢሊየን ብር የነበረ ሲሆን በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ውስጥም የተበላሸ ብድር መጠኑን ወደ 12 ቢሊየን ብር ዝቅ ለማድረግ ዕቅድ ነበረው። 

ሆኖም የተበላሸ ወይንም መመለሱ አጠራጣሪ የሆነው የባንኩ ብድር መጠን ከመቀነስ ይልቅ ጨምሮ ታይቷል። የልማት ባንኩ የተበላሸ ብድር መጠንም አሁን ላይ 20.9 ቢሊየን ብር የደረሰ ሲሆን ከአጠቃላይ ዕቅዱ የ100 ሚሊየን ብር ጭማሪ አሳይቷል።

ሆኖም የባንኩን እንቅስቃሴ በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች እንደነገሩን ሀገሪቱ ከነበረችበት ሁኔታ አንጻር 47 ሚሊየን ብር ትርፍ መገኘቱም በክፉ የሚነሳ አይደለም።  ካለፈው አመት ሀምሌ ወር እስከዚህ አመት ታህሳስ ወር ድረስ የሰሜኑ ጦርነት ከትግራይ ወጥቶ ሰሜን ሸዋ መድረሱ የልማት ባንኩን ብድር የማይመልሱ ተበዳሪዎችን ቀጥር በመጨመሩ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። 

ሆኖም የትግራይ እና የአማራ ክልል ተቀንሶ ሲታይ የልማት ባንኩ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ አፈጻጸም እንዳለው መረዳት ችለናል። እንዲሁም በ2014 አ.ም ጅማሬ ላይ መንግስት ሀገሪቱ ላይ የኢኮኖሚ አሻጥር እየተሰራ ነው በሚል ባንኮች ብድር እንዲያቆሙ ማዘዙ የባንኩ ተበዳሪዎች ተጨማሪ ካፒታል አግኝተው ምርት አምርተው በመሸጥ ብድር እንዳይከፍሉ ማድረጉም ሌላው ለባንኩ አፈጻጸም መወረድ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ልማት በቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት ዮሀንስ አያሌው (ፒ ኤች ዴ) መመራት ከጀመረ አንስቶ ከፍተኛ መሻሻሎችን አሳይቶ ቆይቷል። በተለይ ባለፈው አመት ባንኩ የነበሩበትን የተለያዩ ውዝፍ ስራዎች በመስራት እንዲሁም የአንዳንድ ከፍተኛ ተበዳሪ ኩባንያዎችን  ችግር አቃሎ ወደ ብድር ከፋይነት በማስገባት 3.4 ቢሊየን ብር ማትረፍ ችሏል። ይህም ብቻ ሳይሆን ባንኩ አበድሮት ከነበረው ከ40 ቢሊየን ብር በላይ የተበላሸ የነበረውን 51 በመቶ የብድር ምጣኔ ወደ 20 በመቶ ለማስገባት ተችሎ ነበር። [ዋዜማ ራዲዮ]