ዋዜማ ራዲዮ- ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ዞን አንድ ማምለጣቸውን ምንጮች ለዋዜማ ተናገሩ ፡፡ በነፍስ ግድያ ጥፈተኛ ተብለው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የነበሩት 2 ታራሚዎች አሸናፊ መለሰ ፤ሳሙኤል መካ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ. ም ከረፋዱ 3 እስከ 4 ባለው ሰአት ውስጥ ከማረሚያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ያመለጡ ሲሆን፤ ኤፍሬም ገ/ ጊዩርጊስ የተባለ ሌላ እስረኛ ደግሞ ለህክምና ወደ ሆስፒታል ሲወሰድ ከመኪና ላይ ዘሎ ማምለጡን ምንጮች ተናግረዋል ፡፡


ማረሚያ ቤቱ የሁለቱ የታራሚዎቹን ማምለጥ ማታ በቆጠራ ሰአት እንዳወቀ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ማረሚያ ቤቱ በእስረኞች ላይ ቁጥጥሩን ማጥበቁን ስምተናል።


“እንደሚያመልጡ ታውቁ ነበር” ፣ “ያያችሁት ነገር አለ” በሚል ታራሚዎች ላይ ከፍተኛ ወከባ እየደረሰ እንደሆነ የታራሚ ቤተሰቦች ተናግረዋል። እስረኞች የጣት ቀለበትና የአንገት ሀብልም እንዲያወልቁ መደረጋቸው አግባብ አይደለም ይላሉ።


የእስረኞቹን እንዴት አንዳመለጡ እና አሁንስ በቁጥጥር ስር ውለዋል ወይ? ብለን ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ ማረሚያ ቤቶች የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ገረመው አያሌው ስልክ የደወልንላቸው ሲሆን ከጠየቅናቸው በኃላ “የማይመች ቦታ ነኝ መልሼ ልደውል” በማለት የእጅ ስልካቸውን ዘግተውታል ፣ በተደጋጋሚ ብንደውልም ሊሰራልን አልቻለም፡፡