Addis Ababa Deputy Mayor Takele Uma Benti- FILE

ዋዜማ ራዲዮ- ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን በአዲስ አበባና ዙሪያዋ በቋሚነት ለማስፈር በየከተማው ቦታዎች እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።

በ2009 አ.ም መጨረሻና በ2010 አ.ም መጀመርያ በኦሮምያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተነሳ ግጭት ሳብያ ከሁለቱም ወገኖች በርካቶች መሞታቸው ይታወቃል። በተለይ ከኦሮምያ በኩል ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው። በሁለቱ ክልል አስተዳደሮች በኩል እርቅን በማውረድ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ስለመመለስ ስምምነት መደረጉም ይታወሳል።ነገር ግን የኦሮሞ ተፈናቃዮችን ወደየአካባቢያቸው ከመመለስ ይልቅ በአማራጭነት የተወሰደው በአዲስ አበባና በከተማዋ ዙሪያ ጊዜያዊ መጠለያዎችን ሰርቶ ማስፈር ነው።


     በአቃቂ ፣ በለገጣፎና የተለያዩ አካባቢዎች የቆርቆሮ ማረፍያዎችን ሰርቶ በርካታ ተፈናቃዮችን የማስፈሩ ስራ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በተገኙበት ስነ ስርአት ባለፈው ዓመት ተከናውኖ ነበር።


ዋዜማ ራዲዮ እንዳረጋገጠችው የኦሮሞ ተወላጅ ተፈናቃዮችን ለጊዜያዊ በሚል በአዲስ አበባ በሰፈሩባቸው አካባቢዎች ቋሚ መኖርያ የመገንባት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።በአዲስ አበባ አቃቂ አካባቢ ባለው ኮየ ፈጬ ኮንዶሚኒየም አቅራቢያ ወይንም ዋልያ አደባባይ ከፍ ብሎ ባለው ቦታ ላይ ለተፈናቃዮች በሚል ቋሚ መኖርያዎች እየተሰሩ ነው። ዋዜማ ራዲዮ በዚህ አካባቢ የተለያዩ ተቋራጮች በ48/48 ካሬ ሜትር ላይ መኖርያ እንዲሰሩ ውል እንደተሰጣቸው ተረድታለች። ከ 50 እስከ 200 ቤቶችን እንዲገነቡ ኮንትራት ያገኙ ተቋራጮችም መኖራቸውን አረጋግጠናል። በኮዬ ፈጬ ብቻ ሳይሆን በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማም ተመሳሳይ ዕቅድ እንዳለ ሰምተናል።


ከመጪው ምርጫ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ የህዝብ አሰፋፈር ለውጥ ይደረጋል ተብሎ በስፋት አስተዳደሩ ላይ ጥርጣሬዎች በሚነሱበት በዚህ ጊዜ እንዲህ አይነት ውሳኔ ላይ ደርሶ ድርጊቶች መፈጸማቸው አነጋጋሪ ሆኗል።


“እርምጃውን ከስብዓዊነት ጋር ብቻ ማየት ይገባል፣ ከአጠቃላይ ተፈናቃዮቹ በአዲስ አበባና አካባቢው ቤት የማግኘት ዕድል ያላቸው በቁጥር ትንሽ ስለሆኑ ለነገሩ ፖለቲካዊ ገፅታ ማላበስ ተገቢ አይደለም” ብለውናል ስሜ አይነገር ያሉ የኦሮምያ ክልል የካቢኔ ሹም።

ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆችን አዲስ አበባ ቤት ለመገንባት ሲታሰብ በከተማው ያሉ በርካታ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ ) ካድሬዎች መሬት ለኛም ይገባናል የሚል ጠበቅ ያለ ጥያቄ ለአስተዳደሩ አንስተው እንደነበር አውቀናል። ሆኖም የተሰጣቸው ምላሽ ለእናንተ ቅድሚያ አይሰጥም የሚል ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]