ዋዜማ ራዲዮ- ቁጥራቸው ከ30 በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በሀሰተኛ ሰነድ ከሀገር ለመውጣት ሲዘጋጁ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዋዜማ ከምንጮቻ አረጋግጣለች፡፡

ግለሰቦቹ ለሀጂ እና ኡምራ ጉዞ ወደ ሳውዲ አረቢ ለመጓዝ ሲሞክሩ ነው አርብ ግንቦት 30/2011 ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ የተያዙት፡፡
ተጠርጣዎቹ የያዙት ሰነድ ህገወጥ መሆኑን እንደማያውቁ እና ትክክለኛ ሰነድ ነው በማለት ይናገሩ እነደነበር ለማወቅ ተችላል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተሸከርካሪዎች ከተጫኑ በሃላም ጥቁር አንበሳ አካባቢ ወደሚገኘው የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች መስሪያ ቤት መወሰዳቸውን ለማወቅ ተችላል፡፡


ሀይማኖታዊ ስርአትን ለመፈጸም ወደ ሳውዲ በሚደረገው በዚህ ሃይማኖተዊ ጉዞ ቀድሞም ቢሆን ብዙ አይነት ችግሮች እንደነበሩበት የዋዜማ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የሀሰተኛ ሰነድን በማዘጋጀት ህጋዊ መስሎ ወደ ሳውዲ መጓዝ አንዱ የተለመደ አሰራር እንደሆነ ይሰማል፡፡ ለስራ ፍለጋ ወደ ሳውዲ አረቢያ መጓዝ የሚፈልጉ ዜጎች ይህንኑ መንገድ ሲጠቀሙበት እንደቆዩ የመንግስት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡


በቅርቡ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሀጂ እና ኡምራ ጉዞ ላይ ይታዩ የነበሩ መሰናክሎችን በመቅረፍ የጉዞ ሂደቱን ለማቅለል ሰፊ ስራ መስራቱን አስታውቆ ነበር፡፡


ይህንን የሃጃጅ ሃይማኖታዊ ስርአት ለመፈጸም ጥሪታቸውን አሟጠው የእርሻ መሬታቸውን ሳይቀር በመሸጥ የሚጓዙ መኖራቸው ይነገራል፡፡ ለአውሮፕላን ትኬት ጨምሮ በሳውዲ ላለው መስተንግዶ እስከ 100 ሺህ ብር እንደሚያወጡም ተጓዦቹ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና በሳውዲ አረቢያ የሚጠብቃቸው መስተንግዶ የማረፊያ ቦታ ከሚያወጡት ወጪ ጋር ፈጽሞ እንደማይመጣጠን በማንሳት ይህ ሀይማኖታዊ ጉዞ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይታል፡፡


ምናልባትም በትናትናው እለት ከነሀሰተኛ የጉዞ ሰነዶቻቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት መንገደኞችም በአቅም ማነስ ምክንያት የወሰዱት አማራጭ ወይም ደግሞ በአነስተኛ ዋጋ የጉዞ ጉዳዮቻችሁን እንጨርስላቹሃለን በሚሉ ህገወጥ ደላሎች ተጭበርብረው ሊሆን እንደሚችል የኣኢምግሬሽን ስራተኞች ግምታቸውን ይናገራሉ፡፡ ፖሊስ ከዚህ የህገወጥ የጉዞ ሰነድ ጀርባ የተዘረጋ የወንጀል ሰንሰለት አለ ብሎ በማመኑም አሁን ሰፊ ምርመራ መጀመሩን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች፡፡

ተጨማሪ የዋዜማን ዝርዝር ዘገባ ከታች በድምፅ ያገኙታል

https://youtu.be/5IZHBgJUzj0