ዋዜማ ራዲዮ- በሰሜን ወሎ የሕወሓት አማፅያን የከፈቱትን ማጥቃት ተከትሎ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ወደ በደሴ ከተማና ጊዜያዊ መጠለያዎች ሸሽተው የሚገኙ ነዋሪዎች ሁለት መቶ ሰባ ሺ ሶስት መቶ ያህል መድረሳቸውን የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ አበበ ገብረመስቀል ለዋዜማ ተናግረዋል።


በ12 የመንግስት ትምህርት ቤቶች ስድስት ሺ ስድስት መቶ ሀያ ዘጠኝ ሰዎች እንዳሉ የተናገሩት አቶ አበበ የተቀሩት በዘመድ ቤት እንዲሁም ቤት ተከራተው እየኖሩ ነው ብለዋል ፡፡


ለተረጂዎች በፈቃደኝነት ድጋፍ እያሰባሰቡ ያሉ ግለሰቦችና የመብት ተሟጋቾች “ መንግስት ለተረጂዎች ድጋፍ እያቀረበ አይደለም” ፣ “ ተፈናቃዮች ተረስተዋል” ሲሉ የመረረ ቅሬታቸውን ለዋዜማ ሪፖርተር ተናግረዋል። አሁን በደሴ ከደረሰው ረሀብ በተጨማሪ የትራኮማ በሽታ ወረርሽኝ መከሰቱንም የከተማዋ በጎ ፈቃደኞች ያስረዳሉ። የተረጂዎች ቁጥርም ከአራት መቶ ሺህ በላይ መሆኑን ተሟጋቾቹ ይናገራሉ።


ተፈናቅለው ደሴ ከተማ የተጠለሉት ዜጎች ለከፋ የምግብ ዕጥረት መጋለጣቸውን ያልሸሸጉት የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ አበበ ገብረመስቀል ለችግሩ ተጠያቂ መሆን ያለበት ነዋሪዎቹን ከቀዬቸው ያፈናቀለው ሕወሓት ነው ባይ ናቸው።


መንግስትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እስካሁን ለ178 ሺ ተፈናቃዮች ዕርዳታ አድርሰዋል። የአለም የምግብ ፕሮግራምም አስቸኳይ ዕርዳታ ዕደላ በመጀመሩ በርከት ያሉ ተፈናቃዮች ድጋፍ እንደሚያገኙ አቶ አበበ ያስረዳሉ።


መንግስት ዕርዳታ በማቅረብ በኩል የመሪነቱን ድርሻ ይዞ እየሰራ ነው የሚሉት ምክትል ከንቲባው ከተለየዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ ለተጎጂዎች መድረስ ጀምሯል ብለዋል።


ከተረጂዎች ቁጥር አንፃር እርዳታው በቂ አለመሆኑንና ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አቶ አበበ አሳስበዋል።
የትራኮማ ወረርሽኝ ተከስቷል ስለመባሉ መረጃ እንደሌላቸው ለዋዜማ የተናገሩት አቶ አበበ በመጠለያ ጣቢያዎቹ የተመደቡ የጤና ባለሙያዎች ስላሉ መረጃው በነሱ በኩል ተጣርቶ የምንመለከተው ይሆናል ብለዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]