Mesfin Araya Ethiopia National Dialogue commissioner-FILE

ዋዜማ- በሀገራዊ የምክክር መድረኩ ላይ አንሳተፈም በሚል ያፈነገጡ 13 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማግባባት ባለፉት ስድስት ወራት ሲደረገ የነበረው የሽምግልና ጥረት እስካሁን ውጤታማ መሆን እንዳልቻለ ዋዜማ ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ካላቸው ምንጮች ሰምታለች። 

ወደ ምክክር መድረኩ አንገባም ያሉትና “ቡድን 13”  በመባል የሚጠሩት  13 የፖለቲካ ፓርቲዎች በዋናነት የሀገር ዓቀፍ ምክክር ኮምሽኑ ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ ያነሳሉ። የኮምሽነሮችን አሿሿምም ይቃወማሉ። 

ካፈነገጡት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣  የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፣ ገዳ ፓርቲ፣ የአፋር ህዝብ ፓርቲ፥ የአፋር ህዝብ ለፍትሕ እና ዲሞክራሲ፥ የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ፥ የአገው ሸንጎ ፓርቲ፥ ህብር ኢትዮጽያ ፥ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ይገኙበታል።

እንዲሁም የዶንጋ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር፥ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፥ የሞቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፥የዎላይታ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር፥ አረና ትግራይና ትብብር ለሕብረ ብሔር ዲሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም በዚህ የምክክር ሂደት ለመሳተፍ  ምቹ ሁኔታ የለም እያሉ ነው።

ሀገራዊ ምክክሩ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የበለጠ በማህበረሰቡ የሚደረጉ ምክክሮች ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ሲሆን በተለያዩ አደረጃጀቶች ማህበረሰቡን አግኝቶ ማወያየት የሚችልበትን ስልት እያሰናዳ ይገኛል። 

እነዚህን ያፈነገጡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመመለስ በዋናነት  የሽምግልና ጥረት እያደረገ ያለው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ነው። 

ምክር ቤቱ ከጥቅምት ጀምሮ ልዩነቶችን የማጥበብ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ዋና ሰብሳቢው መብራቱ አለሙ (ዶ/ር) ለዋዜማ ነግረዋል።

እስካሁንም እነዚሁ የፓለቲካ ሀይሎች በዚያው ርቀው ስለመቅረታቸውም አልያም ወደ ሂደቱ  መመለሳቸውን በሚመለከት ያሳወቁት ግልፅ ያለ ውሳኔ የለም።

በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የፍትሕ ሚንስትሩ ጌዲዎን ጢሞቲዎስ ቅሬታ ያላቸውን የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከፓርቲዎች ምክር ቤት ጋር በጋራ ውይይት ተደርጎ ቅሬታ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክክሩ ለመቀጠልና ላለመቀጠል የመጨረሻ ሀሳባቸውን ይዘው እንዲመለሱ በመወሰን ተጠናቆ ነበር። 

ባለፈው ሳምንት መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረገ ስብሰባ አፈንጋጮቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመጨረሻ አቋማቸውን ያሳውቃሉ ተብሎ ቢጠበቅም “ቡድን-13”  አቋማቸውን ሳያሳውቁ ቀርተዋል። 

የ ”ቡድን -13”  አባል የሆኑት የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር ሙላት ገመቹ  “ ኮሚሽኑ የገዥው ፓርቲ ተፅኖ ያለበት ነው” ሲሉ ይከሳሉ ።

“በሀገሪቱ ውስጥ ላለው ችግር ገለልተኛ ሆኖ መፍትሔ ማምጣት አይችልም።  ራሳችሁን ለምን አገለላችሁ ተብለን ስንጠየቅ መልሳችን ይህ ነው”  ብለውናል።

የምክክሩ  የኮሚሽን ዋና  ኮሚሽነር  መስፍን አርዓያ ለዋዜማ እንደነገሩት በሂደቱ ውስጥ ማንኛውም ኢትዮጰያዊ በሀገር ቤትም ይሁን በውጩ ዓለም ያሉ ኢትዮጰያዊያን እንዲሳተፉ እንደሚደነግግ ጠቅሰው ከህዝቡ ቀጥሎ የውይይቱ ሂደት ዋነኛ ባለድርሻ አካላት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው ብለዋል። 

ኮሚሽኑ ወደ ስራው ገፍቶ እየገባ ባለበት በዚህ ወቅት እነዚሁ ፓርቲዎች የእነሱን ደጋፊዎች በማደራጀት እና ወደ ምክክሩ ሂደት እንዲመጡ ማድረግ እንዲሁም  የኮሚሽኑን ገለልተኛነት በመቆጣጠርና በማረጋገጥ ሊረዱ ይችላሉ ፤ በራቁ ቁጥር ይህን ያጎድላሉ  ይላሉ መስፍን።

“አዋጁን በሚመለከት ጥያቄ እንደሚያሱ እናውቃለን። ነገር ግን  ኮሚሽኑ በአዋጁ ዙሪያ አይመለከተውም፤ አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ የተሰጠን ነው ከዚያ መለስ ባለው ሂደት ግን ኑ እንነጋገር እያልን ነው ፤ በዚህ መሠረትም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ተነጋግረናል “ ይላሉ ኮምሽነር መስፍን።

ችግሮች እያሉም ቢሆን የሀገር ጉዳይ ነውና ከሂደቱ ማንም የፖለቲካ ሀይል እንዳይቀር ጥረት ሲያደርግ መምጣቱን አሸማጋይ ሆኖ የከረመው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ሰብሳቢ መብራት አለሙ ለዋዜማ ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላም ቢሆን ም/ቤቱ እስከመጨረሻው ሂደት ድረስ የሚገፋበት ቢሆንም ከዚህ ቀደም ያደርግ በነበረው መጠን ግን እንደማይሆን ነው የገለጸው። [ዋዜማ]