Photo Credit -DW

ዋዜማ ራዲዮ- የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) አመራርሮች መካከል እየተካረረ የመጣው ልዩነት የፓርቲውን ቀጣይነት አደጋ ላይ መጣሉን ዋዜማ ካነጋገረቻቸው የድርጅቱ አመራር አባላት ተረድታለች።


ኦፌኮ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር ስትራቴጂካዊ ጥምረት መፍጠሩን ተከትሎ እየበረታ የመጣው የፓርቲ አባላት አለመግባባት በቅርቡ ኦፌኮ ከኦነግ “የኦሮሞ የሽግግር መንግስት” መስርተናል በሚል ያወጡት መግለጫ የድርጅቱን አንዳንድ አመራሮች ከሀላፊነት አስከመልቀቅ እንዳደረሳቸው ተረድተናል።


በቅርቡ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ(ኦፌኮ) እና በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ከምርጫ ራሳቸውን ለማግለል መወሰናቸውን ተከትሎ “የኦሮሚያ የሽግግር መንግስትን” ማቋቋማቸውን የሚጠቅስ መግለጫን ማውጣታቸው በፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የሚመራው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት መካከል ቅሬታ ማስከተሉንና ችግሩን ለመፍታት ከድርጅቱ ሊቀመንበር በኩል እምብዛም ፍላጎት አለመታየቱን አባላቱ ይናገራሉ።


ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የስራ አስፈጻሚ አባል እንዳሉንም በኦፌኮ ስም ግዙፍ ትርጉም ያለው መግለጫ ሲወጣ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ምክክር እንዳልተደረገ እና መግለጫውን ከህዝብ ጋር በሚድያ መስማታቸውን ይናገራሉ።
በኦፌኮ ስም መግለጫው ይውጣ እንጂ ሽግግር መንግስትን ያክል ክብደት ያለውና በህግም ተቀባይነት የሌለው መግለጫው የኦፌኮ ነው ብለው እንደማያምኑም የስራ አስፈጻሚ አባሉ ገልጸዋል።


“የኦሮሚያ የሽግግር መንግስት” መግለጫን ፓርቲያቸው የማያወቀውና ያልመከረበት ከሆነ ለምን ፓርቲው በጽሁፍ መግለጫ አላስተባበለም? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ የተወሰኑ የፓርቲው አባላት በተጠየቁባቸው መገናኛ ብዙሀን መግለጫው የኦፌኮ አቋም አለመሆኑን ለህዝብ ለማስረዳት መሞከራቸውን የጋራ መግለጫ ለማውጣት ግን የጋራ ስብሰባ ማድረግ ባለመቻላችን እስካሁን እውነቱን ለህዝብ ለማድረስ አልቻልንም ብለዋል።


ሌላኛው የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ለዋዜማ ራዲዮ እንደተናገሩት ኦፌኮ ከዳውድ ኢብሳ ኦነግ ጋር “የኦሮሞ የሽግግር መንግስት” ስለመቋቋሙ የወጣውን መግለጫ በጽሁፍ እንዳይስተባበል የከለከሉት የፓርቲው ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና መሆናቸውን እና የከለከሉበት ምክንያትም ግልጽ እንዳልሆነላቸው ነግረውናል። ነገር ግን መግለጫው በመውጣቱ እና ሊስተባበል ባለመቻሉ መግለጫው የእኛ አቋም አይደለም በሚል የለቀቁ የቆዩ የፓርቲ አባላት መኖራቸውንም ጠቁመውናል።


ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ አመራር አባላት መካከል በትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ልዩነት እየታየ ነው።ልዩነቶች ጎልተው መታየት የጀመሩት አሁን በእስር ላይ ሆኖ የህግ ጉዳዩን እየተከታተለ ያለው የኦሮሞ መብት ተሟጋች ጃዋር መሀመድ ፓርቲውን ከተቀላቀለ ወዲህ እንደሆነ ይነገራል።


በ2012 አ.ም አጠቃላይ ምርጫ መደረግ አለበት ካልተካሄደም ከመስከረም 30 ቀን 2013 አ.ም በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ህጋዊነት የለውም የሚል አቋም በጃዋር መሀመድ እና በሌሎች የኦፌኮ አባላት ይንጸባረቅ ነበር። ነገር ግን በዚሁ ፓርቲ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ መራዘሙን እና ምርጫው እስኪደረግ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ህጋዊ ሆኖ መቀጠሉን የሚደግፉ ነበሩ።


ከጦርነቱ መጀመር አስቀድሞ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ሕወሓት ወደ መቀሌ ጥሪ ሲያደረግላቸው ወደዚያው መጓዛቸውን የሚቃወሙ አመራሮች ነበሩ። አሁን በእስር ላይ ያሉት የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር በቀለ ገርባ እና እና አቶ ሙላቱ ገመቹ ሕወሓት ጥሪ ሲያቀርብላችው መቀሌ ተገኝተው በስብሰባዎች ተሳትፈዋል። በመቀሌ ሕወሓት በሚጠራቸው ስብሰባዎች የሚንጸባረቁ ሀሳቦች ተገቢ አለመሆናቸውን በማንሳት ኦፌኮን ወክለው የሚሳተፉትን ከፍተኛ አመራሮች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እንዲያደርጓቸው ለሊቀ መንበሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ጥያቄን ያቀረቡ የፓርቲው አመራሮች ነበሩ። ሆኖም ፕሮፌሰር መረራ ጉዳዩን ቸል ማለት እንደመረጡ አባላቱ ነግረውናል።


የፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ለችግሮች ምላሽ ለመስጠት አለመፈለግና የድርጅቱ አባላትን ጥያቄዎች በውይይት ለመፍታት አለመሞከር አንዳንድ አባላት ድርጅቱን ለቀው እንዲወጡ እያደረገ ነው።


አሁን በሰሜን አሜሪካ የፖለቲካ ድጋፍ ለማሰባሰብ በዘመቻ ላይ የሚገኙት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ስለጉዳዩ ለዋዜማ ምላሽ እንዲሰጡን ባለፉት አራት ቀናት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።


ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት በነበረ የድጋፍ ስብሰባ ላይ መረራ ጉዲና የኦሮሞ የትግል ጉዞን ዘለግ አድርገው ካብራሩ በኋላ ኦሮሞ በታሪክ በተጋጋሚ ያገኘውን ስልጣን ተነጥቋል። ከዚህ በኋላ ይህ ታሪክ እንዳይደገም ትግላችን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። ኢትዮጵያ አሁን ከገባችበት ቀውስ በቀላሉ ትወጣለች ብለው እንደማይተማመኑ ያወሱት መረራ ኦሮሞ ለቀጣዩ ምዕራፍ ይዘጋጅ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]