Gambella Rural residents-FILE

[ዋዜማ ራዲዮ] የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( ኦዴፓ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የሚመሯቸው ክልል ተወላጅ ባለሀብቶች በጋምቤላ ክልል ለጊዜው እየተሰራባቸው ያልሆኑ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ለመውሰድ በቅርቡ ሰፊ ጥረት ሲያደርጉ እንደቆዩ ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።


ከ2003 አ.ም ጀምሮ የጋምቤላን ክልል ጨምሮ በአራት ክልሎች ለሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ይሆናል ተብሎ ከሶስት ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በፌዴራል መንግስት ቋት ውስጥ ሲገባ ጋምቤላ ብቻውን ከአንድ ሚሊየን በላይ ሄክታር መሬት ገቢ አድርጓል።


የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰፋፊ እርሻ እንዲያለሙ ብድር ካቀረበላቸው 472 ተበዳሪዎች 126ቱ በዚህ ክልል የተሰማሩ ናቸው። ልማት ባንኩ በመላው ሀገሪቱ ለእርሻ ኢንቨስተሮች ከለቀቀው ዋና ብድር 6.01 ቢሊየን ብር : እስከ ወለዱ አሁን ሰባት ቢሊየን ብር እንደሚደርስ ይገመታል። ከዚህ ውስጥ 1.64 ቢሊየን ብሩን ጋምቤላ ክልል እንሰማራለን ላሉ ተበዳሪዎች ነው ያቀረበው።ይሄም ቢሆን ወለዱ ሲጨመር ሁለት ቢሊየን ብርን እንደሚያልፍ የባንኩ የስራ ሀላፊዎች ይናገራሉ።


 ታድያ አሁን ላይ በጋምቤላ ያሉ የሰፋፊ እርሻ መሬቶች በዚህ ደረጃ ለምን የኦዴፓና አዴፓ ከፍተኛ ሹሞት ትኩረት ሆነ የሚል ጥያቄን ለታማኝ ምንጮቻችን አቅርበናል።
እንደሚታወቀው ጋምቤላ ክልል ለሰፋፊ እርሻ ተብሎ ከተሰጠው መሬት ውስጥ አብዛኛው ስራ ላይ አልዋለም ። በዚህም ምክንያት በልማት ባንክ በዚህ ክልል ቅርንጫፍ የተሰጠው ብድር ሁሉም የተበለሸ ወይንም ሊመለስ የማይችል ሆኗል።
ይሄን ተከትሎም የፌዴራል መንግስትን በዋነኝነት እየመሩ ያሉት ኦዴፓና አዴፓ የየክልሎቻቸው ተወላጅ ባለሀብቶች  ከስራ ውጭ ናቸው የተባሉ የሰፋፊ የእርሻ መሬቶች እንዲሰጧቸው ከክልሉ አመራሮች ጋር ንግግርን ሲያደርጉ ነበር።


አንድ ታማኝ ምንጫችን እንደነገሩን ከሆነ መጀመርያ ላይ በክልሉ በሚፈለገው ደረጃና በተለያዩ ምክንያቶች ለአልሚዎች ተሰጥተው ብድርም ተወስዶባቸው ነገር ግን እንደተፈለገው ያለሙ መሬቶችን ለአማራና ኦሮምያ ክልል ተወላጅ ባለሀብቶች የማስተላለፍ ፍላጎት ነበረ። ሆኖም ኦዴፓና አዴፓ በተለያዩ ምክንያቶች መካከላቸው ቅራኔ እየተፈጠ ሲመጣ የኦዴፓ ሀላፊዎች በተናጠል ለክልል ባለሀብቶቻቸው የጋምቤላ ሳይለሙ የቆዩ መሬቶችን ለማሰጠት ሰፊ ጥረት ማድረግ ጀመሩ።


  በዚህ ሂደት ውስጥ በፌዴራልም ሆነ በክልል በከፍተኛ ስልጣን ላይ ያሉ የኦዴፓ ባለስልጣናት የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ኦሙድ ኡጁሉን ጨምሮ ሌሎች የካቢኔ አባሎቻቸውን አነጋግረዋቸው ነበር።


በውይይታቸውም የሰፋፊ እርሻ ቦታዎቹን ለማስተላፍ ዝግጁ እንዲሆኑና በኦዴፓ በኩል ለሰፋፊ እርሻዎቹ የሚያስፈልጉ ሂደቶች እንዲሟሉ እንዲሁም የተበላሹ ብድሮች የሚሸፈኑበት መንገድ እንደሚፈጠር ገልጸውላቸዋል። ለባለሀብቶቹ የሚውለውን ፋይናንስ በራሳቸው ባለሀብቶች ወይንስ ሌላ ብድር ሊመቻችላቸው ይሁን ግን የጠራ ማስረጃ አላገኘንም።


ነገር ግን አጠቃላይ ጥያቄው ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ዕለት ድረስ በጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንትም ሆነ ካቢኔያቸው ተቀባይነት አላገኘም። ይህ የሆነበት ምክንያት በጋምቤላ ያሉ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ለጊዜው እየለሙ አይሁን እንጂ ባለቤት ያላቸው አሉ። በዚህ ክልል ስራ ያቆሙ ኢንቨስተሮች አንዳንዶቹ በጸጥታ ሌሎቹ ደግሞ የልማት ባንክ የሚያስፈልጋቸውን የስራ ማስኬጃ ገንዘብ ስላልሰጣቸው መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣሉ።ባለሀብቶቹም ይህንን ቅሬታቸውን ለመንግስት ማሰማታቸውን ይገልጻሉ። ይህም የነባሮቹ ባለሀብቶች ጉዳይ ገና አለመጠናቀቁን ያሳያል። በዚህ ሁኔታ ላይ ጣጣቸው ያላለቁ መሬቶችን ለሌሎች አልሚዎች ማስተላለፉ ሌላ ችግር ማስከተሉ አይቀርም የሚል መከራከሪያ ከጋምቤላ ክልል በኩል ይቀርባል።


 ከዚህ ቀደም ህወሀት መራሹ ኢህአዴግ መንግስት በተመሳሳይ ለክልሉ ተወላጅ ባለሀብቶች በጋምቤላ በሰፋፊ እርሻ እንዲሳተፉ መሬትም ሆነ ብድር እንዲመቻች አድርጓል ፤ በክልሉ ሳይለሙ የተቀመጡ መሬቶችም ሆኑ የተበላሹ ብድሮች በአንድ ክልል ተወላጆች ምክንያት የመጣ ነው መባሉ ከፍተኛ ውዝግብና ትችት አስከትሎ ቆይቷል።
እርግጥ 27 ሺህ ሄክታር መሬት ወስዶ የነበረው የህንዱ ቢኤችኦ እንደጠፋ ይታወቃል ; ሌላኛው የህንዱ ካራቱሪም 100 ሺህ ሄክታር ወስዶ ማልማት አቅቶት እንደተቀማም የሚታወስ ነው። በብድርም አኳያ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ የተለያዩ አካባቢ ተወላጆች ወስደው የተበላሸ ተበዳሪ ውስጥ ገብተዋል።


የጋምቤላ ክልል ከሌሎች ክልሎች ለሚነሳለት የ “መሬት ስጥ” ጥያቄ እንደከዚህ ቀደሙ በቀላሉ እጅ ይሰጣል ማለት ከባድ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በነበሩበት ጊዜ ለሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ከክልሎች ከሶስት ሚሊየን በላይ ሄክታር መሬት ሲለይ መሬቱንም በመመሪያ በመጣ ውክልና ወስዶ የፌዴራል መንግስቱ ነበር ለባለሀብቶች የሚያከፋፍለው።


ይህ አካሄድ ኢ-ህገመንግስታዊ ቢሆንም የፌዴራል መንግስት አስገድዶ ግን ሲያስተገብረው እንደነበር ይታወቃል። በ2009 አ.ም ግን የፌዴራል መንግስት የክልል መሬቶችን በውክልና እንዲያስተዳድር ይሰራበት የነበረው መመሪያ እንዲቀር ተደርጓል። [ዋዜማ ራዲዮ]