Search engine

የፈረንጁን ቋንቋ አብዝተው ለማይደፍሩ ኢትዮዽያውያን ፈተናቸውን ሊያቀልላቸው ይችላል የተባለውና በአማርኛና በሌሎች የሀገራችን ቋንቋዎች የተዘጋጀ የኦንላይን መዝገበ ቃላት ለአገልግሎት ሊበቃ መቃረቡን ሰምተናል። ይህ መዝገበ ቃላት የኦንላይን መረጃ ፍለጋን በተመለከተ አዲስ በር ከፋች መሆኑ እየተነገረ ይገኛል። መዝገቡ ሀይሉ ያሰናዳው ዘገባ ዝርዝሩን ይዟል፣ አድምጡት

 

በኢንተርኔት ዓለም መረጃ የማግኘት እና በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥናት ማድረግ የተለመደ ጉዳይ እየኾነ መጥቱዋል። በዚህ ዘመን ጉግልን የመሰሉ ግኝቶች በህይወታችን ውስጥ ያላቸው ተጽእኖ ከጉግል በፊት የኖርነውን ኑሮ ማሰብ ራሱ አስገራሚ ጉዳይ አድርጎታል። የኢንተርኔት መረጃ ለብዙዎች ቅርብ እየኾነም ሄዶ ከኢንተርኔት ጋር በቁዋንቁዋችን የምንግባባበት ፍንጭም እየታየ ነው። ከእለት ወደ እለት አማርኛን በመሰሉ የኢትዮጵያ ቁዋንቁዋዎችም ኢንተርኔትን የመጠቀሙ ዘዴ እያደገ ሲመጣ ይታያል። እንደቀድሞው ስለ አንድ ጉዳይ ለማወቅ ሩቅ ርቀት መሄድም ኾነ ወፍራም ጥራዝ ያላቸው መጽሐፍት ማገላበጥ ጊዜው ያለፈበት በሚመስለው በዚህ ወቅት የኢነተርኔት መረጃን በተለያዩ ቁዋንቁዋዎች የማድረሱም ተግባር የዚያኑ ያህል እየተፋጠነ ሲሄድ ይታያል።
ባለንበት ዘመን ጉግል እና ሌሎች ብዙ የኢንተርኔት መረጃዎች በተለያዩ ቁዋንቁዋዎች መገኘታቸው እንግሊዘኛን ወይም ሌሎች የምእራብ ዓለም ቁዋንቁዋዎች አለማወቅ ከኢንተርኔት ተጠቃሚነት አያግድም። አማርኛችንም ይህ እድል ደርሶት በአማርኛ መረጃ መፈለግም መልእክት መለዋወጥም የተለመደ ጉዳይ እየኾነ ነው።

 

በኢንተርኔት የመረጃ ቁዋት የተከማቹ ዜናዎች፣ የትምህርት መርጃዎች እና መዝናኛዎች በቁዋንቁዋችን በቅጽበት እጃችን ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርጉ ፈጠራዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸው ይታያል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚኾነው የአማርኛ እና የሌሎች የኢትዮጵያ ቁዋንቁዋዎች መዝገበቃላት መታየት መጀመራቸው ነው።
ለዚህ አይነት ፈጠራዎች እውን መኾን ምክንያት እንደኾነ የሚነገርለት ቴክኖሎጂ Artificial Intelligence ወይም የሰውሰራሽ እውቀት በስፋት ጥቅም ላይ መዋል እንደኾነም ይነገራል።

 

ይህም ሰው ሰራሽ እውቀት ከዚህ በፊት በሰው ልጆች የአእምሮ ችሎታ ብቻ ይደረጉ የነበሩና የሰውን ልጅ ቀጥተኛ አስተዋጽዖ የሚጠይቁ ነገሮችን ኮምፒውተሮች እና ሌሎች ሮቦት መሰል ፈጠራዎች እንዲሰሩት የማስለመድ ሳይንስ ነው። ልዩ ልዩ መረጃን ይህን ለመሰሉ ማሽኖች በማስተማር ከተቀበሉት መረጃ የተነሳ የሰውን አጋዥነት ሳይፈልጉ በተጫነላቸው እውቀት መሰረት ተግባራቸውን የሚከውኑት ማሽኖች የሰውን ለጅ ቁዋንቁዋም የመማር ብቃታቸው እያደገ መጥቱዋል።

 

ለመጻፍ ያሰብነውን ነገር ገና ጽፈን ሳንጨርስ ምን ለማለት እንደፈለግን የሚገምተው የኢንተርኔት መረጃ መፈለጊያ የሚሰራውም እንዲሁ ነው። ከዚህ በፊት በብዛት ሲፈለጉ የነበሩ ጉዳዮችን በመደርደር ይህን ማለት ፈልገው ይኾን በሚል ጥያቄ ስህተት እንዳንሰራ የሚያርመንም የኮምፒውተር ችሎታም የሚመጣውም ከዚሁ የሰውን ልጅ ቁዋንቁዋ ከመማር ችሎታው ነው።
ይህን የመሰለው ግኝት ያገዘው አማርኛችንም በአማርኛ ቁዋንቁዋ በኢንተርኔት የመረጃ ቁዋት ውስጥ ቀድሞ ከተከማቸው የእውቀት ክምችት መካከል ፈልፍሎ በማውጣት በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ ወደምንፈልገው ይመራናል። ምስጢሩ ያለው የምንፈልገውን ነገር ኢንተርኔቱ ቀድሞን ማወቁ ላይ ነው።
የመዝገበ ቃላቱም ድካምና ጥንካሬ የሚወሰነው በዚሁ በመረጃ ቁዋቱ ውስጥ ቀድሞ በተከማቸው የመረጃና የእውቀት ልክ ነው። እኛ ያልሰጠነውን ከየትም ሊያመጣ የማይችለው ኢንተርኔት አሁንም ብዙ ማደግ የሚጠበቅበትን የመረጃና የእውቀት ውሱንነት ማንጸባረቁ የማይቀር ጉዳይ ነው። ለዘመናችን አንባቢ የቀለሉ እና ወቅታዊ መዝገበቃላት የመስራት ልምዳችን ማነስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ርዳታ ስንፈልግ በግልጽ ይታያል። አሁንም የአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌን ወይም የደስታ ተክለወልድን እና ታዬ ገብረማርያምን ጥንታዊ መዝገበቃላት እንደ ዋቢ ይጠቅስልናል። ሊገኝ የሚችለው የነዚሁ ጥንታዊ ሊቃውንት ሥራ በመኾኑ ከነድካማቸው እና ጥንካሬያቸው እንድንጠቀምባቸው እንገደዳለን። ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ ወይም ከአማርኛ ወደ እንግሊዘኛ የሚተረጉሙት መዝገበቃላትም ቢኾኑ ያላቸው የቃል መጠን ጥቂት መኾን እንዲሁም ከአማርኛ ቁዋንቁዋ የሰዋሰው ቅርጽ የሚነሱ ብዙ ችግሮች ይስተዋሉበታል። በዚህ ላይ ተመሳሳይ ድምጽ ያላቸው ሆሄያት የመኖራቸው ጉዳይ ሲጨመርበት ጉዳዩን የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል።
በአማርኛ ቁዋንቁዋ የሚሰሩ የምርምር እና ሳይንሳዊ ጥናቶች ብዙም አለመኖራቸው የአማርኛ መረጃ ፍለጋውን ያሰናክለዋል። ጥቂት የዊኪፒዲያ ጽሑፎች መኖራቸው ፈላጊውን ባዶ እጁን እንዳይመለስ ቢያደርጉትም እነኚህ መረጃዎችም ቢኾኑ አስተማማኝ አይደሉም። ዜናዎቻችንና መዝናኛዎቻችንም ከነድካማቸው ባሉበት ኹኔታ ይገኛሉ። የዚህ ሁሉ ድምር ስለኛው ጉዳይ መረጃ ለማግኘት ወደ ምእራባውያኑ ቁዋንቁዋ መሄድ ለብዙዎች ተመራጭ እንዲኾን ያደርገዋል። ይህም ሁሉ ኾኖ ጅምሩ ተስፋ ፈንጣቂ መኾኑ ግልጽ ነው። እኛ ወደቴክኖሎጂው ከምናደርገው ርምጃ ይልቅ ቴክኖሎጂው ወደኛ የሚመጣበት ፍጥነት ጎልቶ በመታየቱም በጥቂት ጊዜ ውስጥ ቴክኖሎጂው የኛን ቁዋንቁዋና ባህል ተምሮ የመረጃ ቁዋቱ እየሰፋ ለብዙዎች የሚጠቅም እንደሚኾን መገመት አይከብድም።
Artificial Intelligence ወይም ሰው ሰራሽ እውቀት ላይ የሚደረጉ ምርምሮች በኢትዮጵያም ውስጥ እየተጀመሩ እንደኾነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሰማም ነው። icog labs የሚባለው ድርጅት በተወሰኑ የምርምር ዘርፎች ይህን እውቀት ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት እየሰራ እንዳለም ይታያል። የአምስት ኪሎው የቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩትም በማስተርስ ደረጃ ትምህርት ለመስጠት እየተዘጋጀም እንደኾነ ይፋ አድርጉዋል። እነኚህ ሁሉ ጅምሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ ጉዳይ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን ሥራ ጨምሮ በቁዋንቁዋችን እና በሌሎች የሳይንስ ዘርፎች ላይ የሚያመጣውን አዎንታዊ ውጤትም እንደ ተስፋ ሰጪ ጅማሬ የሚጠብቁትም አሉ። እነኚህ ምርምሮች በሌሎች አገሮች ከሚደረጉ ሙከራዎች ይልቅ ከኢትዮጵያ እና ከወቅታዊ ችግሮቹዋ ጋር የሚዛመዱ ውጤቶችን ያመጡ ይኾናል የሚል ተስፋም ሲነገር ይሰማል።