(ምሽት 4:00 ስዓት የተጠናቀረ)

ዋዜማ ራዲዮ-በኦሮምያና በአማራ ክልል በተደረጉት ስልፎች በርካታ ሰዎች መገደላቸው ሲረጋገጥ የኮምንኬሽን መቋረጥ ምክን ያት በሰልፉ ሳቢያ ስለደረሰው አጠቃላይ ጉዳት ያገኘነው መረጃ ውሱን ነው። ምሽቱን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሺ የሚቆጠሩ ስዎች መታሰራቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። መንግስት ስልፉ በውጪ ሀይሎች የተደገፈና የእስልምና አክራሪዎችና የኢትዮዽያ ጠላቶች የተሳተፉበት ነው ብሏል።

(ከቀኑ 7 ሰዓት የተጠናቀረ)
ኦሮሚያ በጸረ መንግሥት ሰልፎች ተሰንጋ ዋለች። በርካታ የክልሉ አካባቢዎች ዛሬ ጠዋትና ረፋዱን ሰልፍ ተካሂዶባቸዋል። ከዚህ ቀደም እንደሆነውም የመንግሥት ሃይሎች በሰነዘሩት ጥቃት ሰላማዊ ሰልፈኞች መገደላቸውና በብዛት መታሰራቸው እየተዘገበ ነው። በተወሰኑ የአማራ ክልል አካባቢዎችም ትናንት እና ሌሊቱን ሰልፎች ተካሂደዋል፣ በመሣሪያ የተደገፉ ግጭቶች እንደነበሩ ተዘግቧል። በዚህኛውም ክልል ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
በመላው ኦሮምያ ለዛሬ የተጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ በአዲስ አበባ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ታስረዋል። በዝናብ ጨፍግጋ በነበረችው ከተማ ሰልፈኞቹ ወደ መስቀል አደባባይ የወጡት ወደ ረፋድ አራት ሰዓት ግድም እንድነበር የአካባቢው እማኞች ተናግረዋል። ብዙም ሳይቆይ ግን ስልፈኞቹ በአካባቢው በነበሩ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊሶች ተሳደዋል፣ ብዙዎቹም ታስረዋል። በተመሳሳይም በየሰፈሩ ሕዝብ ሊቀሰቅሱ ይችላሉ የተባሉ ወጣቶች እየተለቀሙ መሆናቸውን የዋዜማ ምንጮች ገልጸዋል።
በመስቀል አደባባይ ለተቃውሞ የወጡት ሰልፈኞች አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው። መፈክር የተጻፈባቸው ባነሮችን ይዘው የነበር ሲሆን ፖሊስ ብተናና ማሰሩን ከጀመረ በኋል በኋላ ባነሮቹ ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት አቅራቢያ ባለው የመስቀል አደባባይ ክፍል በአንድ ቦታ ተከማችተው ይታያሉ። በአጠገባቸውም የወለቁ ጫማዎች እና ጌጣጌጦች እዚህም እዚያም ተበታትነው እንደሚታዩ እማኞች ገልጸዋል። ከባነሮቹ ፊት ለፊት ስደስ ወጣቶች በፖሊስ ተይዘው ሲመረመሩ ይታዩ ነበር።
ከቀኑ 5 ተኩል ሲሆን 40 የሚሆኑ ወጣቶች በታጠቁ ፖሊሶች ታጅበው በቀድሞ “የሰላምና ጸጥታ ጥናት ኢንስቲትዩት” ቢሮ ጀርባ ሲወሰዱ ታይቷል። በተመሳሳይ “ሃዲያ ሱፐር ማርኬት” አጠገብ 15 የሚሆኑ ወጣቶች ተይዘው እንደነበር እማኞች ተናግረዋል። እስሩ በአደባባዩ ሁሉም አቀጣጫዎች ሲካሄደ ስለነበር የተያዙትን ሰለፈኞች ትክክለኛ ቁጥር ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ሆኖም በመኪና እየተጫኑ ሲወሰዱ የታዩተነ መነሻ በማድረግ በሞቶዎች የሚቆጠሩ ሳይታፈሱ እንዳልቀሩ የዋዜማ ምንጮች ግልጸዋል።
መስቀል አደባባይ እስከ ቀኑ 6:30 ድረስ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ቆይታለች። በኤግዚቢሽን ማዕከል የሚካሄደው የአድማስ ኮሌጅ ምረቃ ቢኖርም አድባባዩ ከወትሮው በተለየ በሰዎች ተሞልቶ ነበር። በሰለፉ ለመሳተፍ ወይም ለመታዘብ የመጡ በርካታ ወጣቶችም በዙሪያው ይታዩ ነበር።
የዚያኑ ያህልም አደባባዩ መሣሪያ በታጠቁ ፌዴራል ፖሊሶች ተወሮ ነበር። ፖሊሶቹም በአካባቢው ያገኙትን ሰው መታወቂያ ሲጠይቁና ሲፈትሹ ታይተዋል። ዓላማቸውም ሰለፈኞቹን መበትን ብቻ ሳይሆን ማስፈራራትም ሆኖ እንደተሰማቸው በአካባቢው የነበሩና ሲተላላፉ የነበሩ እማኞች ለዋዜማ ገለጸዋል። በእርግጥም መስቀል አደባባይ በሚገኘው የመድኅን ድርጅት ቢሮ አጠገብ፣ እንዲሁም በክፍት (ፒክ አብ)መኪናዎች ላይ የተደገኑ መትረየሶች ይታዩ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ሲቪል የለበሱና የታጠቁ በርካታ የፖሊስና የስለላ ሠራተኞችን መመልከታቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል። እንዚሁ ሲቪል ለባሾች የተያዙ ወጣቶችን ሲጠይቁና ሲመረምሩ፣ የሚጠረጥሯቸውን ሰዎች ሲከታተሉ፣ ለፖሊስ እየጠቆሙ ሲያሲዙ በግልጽ ይታዩ እንደነበር ዋዜማ ያነጋገረቻቸው እማኞች ገልጸዋል። በአደባባዩ ዙሪያ የነበረው ፍተሻና እስር እስከ ቀኑ 6:30 ቀጥሏል። ፖሊሶች ሰልፈኞችን እያሳደዱ ሲደበድቡና ሲያስሩ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማኅበራዊ ገጾች ተለቀዋል።
የዋዜማ ሬዲዮ የኦሮምኛ ፕሮግራም ክፍል እንደዘገበውበሌሎች የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ተቃውሞ ሰልፉ ተጥናክሮ ቀጥሏል። እስካሁን በደረሰን መረጃ መሰረት ቢያንስ በሻሸመኔ፥ ዶዶላ፥ አሳሳ፥ አምቦ፥ ቡሌ ሆራ፥ አወዳይ፥ ደምቢዶሎ፥ ሮቤ፥ ኮፈሌ፥ አዳማ፥ ጊምቢ፥ ባሌ ሮቢ፥ ሆሌታ፥ ቦርደዴና በድሬዳዋ የተቃውሞ ሰልፎች እየተደረጉ ነው።