20526874_1397450073709355_329291626_nዋዜማ ራዲዮ- እስከዛሬ ወደባህር ማዶ ተጉዘው ትዕይንት ካቀረቡት መስል የኪነጥበብ ስራዎች ጋር ሲነፃፀር በተከታታይና በበርካታ ከተሞች በመቅረብ ክብረወሰኑን ይዟል። እያዩ ፈንገሰ ፌስታሌን የሰንብት ትዕይንት በመጪው እሁድ ለዋሽንግተን ዲሲና አቅራቢያው ታዳሚዎች ይቀርባል።

“እንዳትገረሙ!
ከአቅጣጫችን በፊት ጉዞው በመቅደሙ
እንደዚያ ነው ግብሩ በምላስ ለቆሙ።

“በጨረቃ ችሎት ፀሐይን በመክሰስ
በሞቅታ አንቀጽ ፍርድን በማድበስበስ
እመነኘኝ ወዳጄ አትድንም ከመፍረስ!”

የቁምነገሩን አጀንዳ ይዛ የጠፋችበት ፌስታሉን ፍለጋ ተነስቶ አገሩን እያሰሰ እና ፈጣሪውን እየሞገተ የሚጓዘው “እያዩ ፈንገስ” በሰሜን አሜሪካ ለመጨረሻ ጊዜ የመድረክ ዝግጅቱን ሊያደርግ ነው።

ቁምነገርን በሳቅ እያዋዛ፣ እያለሳለሰ እና እያባባለ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበረ ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችንን የሚቃኘውና የሚተቸው፣ ኅብረተሰቡን እና አኗኗሩን ሁሉ የሚፈትሸው፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአንድ ሰው የመድረክ ቴአትር የዛሬ ሁለት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ተመርቆ ሲታይ ከሰነበተ በኋላ፣ የዛሬ ዘጠኝ ወር ገደማ ደግሞ ቴአትሩን ከነመድረኩ፣ ከነለዛው፣ ከነሸንቋጭነቱ እና ከነግርማ ሞገሱ ሸክፎ በአሜሪካ እና በካናዳ 32 መድረኮች ሽርሽር እያለ፣ የተመልካቾቹን ልቦች እያንኳኳ ሰንብቷል።

የሰዉም አቀባበል ደራሲውን “ባህር እንዲህ ከፍሎንም እንባችንና ሳቃችን አንድ መኾኑ ገርሞኛል።” ያሰኘ፣ እጅግ የተለየ ነበር። በርግጥም የኪነጥበብን ከዘመን ዘመን፣ በዘመን መካከል፣ ከጉዳይ ጉዳይ፣ እንዲሁም በአገራት መካከል ድልድይ ሆኖ የመኖሩን ያህል፥ እያዩ ፈንገስ ይህንን እውነታ ፍንትው አድርጎ ማሳያ ሆኗል። በዘመነ ሉልነት እና የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ዘመን ሲመዘን ደግሞ ተጽህኖው ከፍ ይላል።

በገጣሚ እና ደራሲ በረከት በላይነህ ተደርሶ በግሩም ዘነበ የተተወነው “እያዩ ፈንገስ | ፌስታሌን”፣ የጠፋች ፌስታሉን ተከትሎ “ፌስታሌን” እያለ፣ በየሰዉ ቤት እና ልብ ሰርስሮ እየገባ እየበረበረ “የሆዱን ሲነግሩት የኮረኮሩት ያህል ይስቃልን” እያስተረተ በሳቅ እያፈረሰ፣ ሲያዝንም ልቡ እስኪጠፋ ድረስ አብሮት እያዘነ፣ ተመልካቹን ለ2 ሰዓት ተኩል ያህል በአስደናቂ ብቃት ተቆጣጥሮ ይዞ፣ ብዙ ተጉዞ፥ እነሆ

“ነው ወይ ልንለያይ በቃ ልንበታተን
ዳግመኛ ለመምጣት ተስፋ እንኳን ሳይኖረን” አስብሎ ሊያስዘምር፣ ለስንብት ዋሽንግተን ዲሲ (7701 16th Street NW) ለኦገስት 13 ቀን ቀጠሮ ይዟል።

በዋቢ ሸበሌ እና ራስ ሆቴል በየወሩ ይቀርብ የነበረው የግጥምን በጃዝ ምሽቶች ላይ በተለያዩ ክፍሎች እየተቆራረጠ ለ2 ዓመታት ያህል ቀርቦ የነበረው እና፣ ወደ ሙሉ ሰዓት ቴአትርነት ተዘጋጅቶ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲቀርብ የነበረው እያዩ ፈንገስ፥ ባለፈው ህዳር ነበር ጉዞውን ወደ ሰሜን አሜሪካ ያደረገውና አዲሳባ የጠፋች ፌስታሉን በተመልካች ልብ ውስጥ አብሮ እየተጓዘ ሲፈልግ የከረመው።

በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢው 2 ጊዜ፣ በሲያትል 2 ጊዜ፣ በአትላንታ 3 ጊዜ፣ በላስቬጋስ 2 ጊዜ፣ በሳንዲያጎ 2 ጊዜ፣ በሻርለት 2 ጊዜ፣ በሜኒሶታ 2 ጊዜ፣ በሎስአንጀለስ 2 ጊዜ፣ በዴንቨር 2 ጊዜ፣ እንዲሁም በዳላስ፣ በኦስቲን፣ በሂውስተን፣ በኦክላንድ፣ በፊኒክስ፣ በኒውዮርክ፣ በቶሮንቶ፣ በኦቶዋ፣ በዊኒፔግ፣ በካልጋሪ እና በኤድመንተን አንዳንድ ጊዜ ለመድረክ በቅቷል።

ተውኔቱ ቀጣይ ጉዞውን ወደ አውሮፓና አውስትራሊያ እንዲሁም መካከለኛው ምስራቅ ለማድረግ እየተዘጋጀ ነው።
በአሜሪካ ቆይታው ከመጥፎ አየር ሁኔታና ከሌሎች የኢትዮጵያውያን ዝግጅቶች ጋር አንድ ሁለቴ ከመገጣጠም ውጪ የጎላ ችግር ስይገጥመው ተካሂዷል ይላሉ አዘጋጆቹ።

ለቴአትሩ ማጀቢያ የሚሆነውን ሙዚቃ፥ አንጋፋዎቹ ጆርጋ መስፍን፣ አበጋዙ ክብረወርቅ ሽዮታ እና ግሩም መዝሙር ናቸው የሰሩት። ግጥሙን በረከት በላይነህ፣ ዜማ መድረሱን እና ሙዚቃውን ፕሮዲዩስ በማድረግ ዓለማየሁ ደመቀ፣ እንዲሁም በድምጽ በዛወርቅ አስፋው እና ግዛቸው ተሾመ ተጫውተውታል።